Get Mystery Box with random crypto!

ባለትዳር ለሆነች የስራ ባልደረባው ያቀረበውን የፍቅር ጥያቄ ባለመቀበሏ የገደላት ግለሰብ በዕድሜ ል | Skyline media

ባለትዳር ለሆነች የስራ ባልደረባው ያቀረበውን የፍቅር ጥያቄ ባለመቀበሏ የገደላት ግለሰብ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት

የዐቃቤ ህግ መዝገብ ላይ እንደተገለጸው ጌታቸው አለምፀሃይ ክፍሉ የተባለው ተከሳሽ ጥር 2/2011ዓ.ም ከረፋዱ 5፡30 በንፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ሳባ ህንፃ ውስጥ በሚገኘው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ 01 ፋይናንስ ቢሮ ውስጥ የስራ ባልደረባው የነበረችውን ሟች ወ/ሮ መዓዛ ካሳ የፍቅር ጥያቄ አቅርቦላት ባለትዳር እንደሆነች ብትገልፅለትም የግድ አብረው መሆን እንዳለባቸው ቢወተውታትም ፈቃደኛ ባለመሆኑዋ ምክንያት በስራ ገበታዋ ላይ እያለች በቢላ እያባረረና ለማምለጥ ከቢሮ ስትሮጥ በወደቀችበት በቀኝና በግራ ሆድዋ ላይ ደጋግሞ በመውጋት የሆድ ዕቃዋ ወደ ውጪ ወጥቶ ህይወትዋ እንዲያልፍ በማድረጉ በፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ክስ ተመስርቶበታል።

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶበት በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በከባድ የሰው መግደል ወንጀል በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በዐቃቤ ህግ ክስ ቀርቦበታል ነገር ግን ተከሳሽ በምርመራ ላይ እያለ ከእስር በማምለጡ ምክንያት ክሱ በሌለበት እንዲታይ ተደርጎል፡፡

ተከሳሹ ሆነ ብሎ የተሰወረ በመሆኑ ዐቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ በሚያሰማበት ጊዜ የዐቃቤ ህግን ማስረጃ የመጠየቅ እና የመመርመር መብቱ ታልፎ ፍ/ቤቱ በዐቃቤ ህግ የቀረበው ማስረጃ በበቂ ሁኔታ ተከሳሹ ድርጊቱን የፈጸመ መሆኑን ያስረዳ በመሆኑ እንዲሁም መብቱን ጠብቆ የዐቃቤ ህግን ክስ እና ማስረጃ ያላስተባበለ በመሆኑ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት ነሀሴ 4/2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል።

ጌታቸው አለምፀሃይ ክፍሉ ከላይ በምስሉ ላይ ያለው ሰው ሲሆን በምርመራ ወቅት ከእስር አምልጦ ተደብቆ ይገኛል፡፡

ስለሆነም ያለበት አድራሻ የሚያውቅ ካለ ጥቆማውን ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወይም ለፍትህ ሚኒስቴር እንዲያሳውቅ ተጠይቋል፡፡
@wolaitatimes