Get Mystery Box with random crypto!

†ስንክሳር ነሐሴ 23 † እንኳን ለሰላሳ ሺ ግብጻውያን ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል | ስንክሳር በየቀኑ

†ስንክሳር ነሐሴ 23 †

እንኳን ለሰላሳ ሺ ግብጻውያን ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ሠለስቱ እልፍ ሰማዕታት †††

† ዘመነ ሰማዕታት አርባ ሰባት ሚሊየን ክርስቲያኖችን በአርባ ዓመታት ከበላ በኋላ በ305 (312) ዓ/ም ቢጠናቀቅም ስለ ሃይማኖት መሞት ግን እስከ ምጽዓት ድረስ ይቀጥላል:: ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ከሚቀርቡ ፈተናዎች ሁሉ እጅግ ከባዱ ይሔው ሰማዕትነት ነውና ሊቀበለው ያለው (ያደለው) ይቀበለዋል::

ቤተ ክርስቲያን በባሕር ላይ ያለች መርከብ ናትና ዘወትር በፈተና ውስጥ መኖሯ የሚጠበቅ ነው:: ዘመነ ሰማዕታትን ተከትሎ የመጣው የመናፍቃን ዘመን ሲሆን ለመቶ ሃምሳ ዓመታት ያህል መናፍቃን እንደ አሸን ፈልተዋል:: በዚያው ልክ ከዋክብት ቅዱሳን ሊቃውንት ነበሩና በየጊዜው ጉባኤያትን እየሠሩ: መናፍቃንን አሳፍረዋል:: ምዕመናንንም አጽንተዋል::

በ451 ዓ/ም የተፈጸመው ድርጊት ግን ዛሬም ድረስ ጠባሳው የሚለቅ አልሃነም:: ንጉሡ መርቅያንና ጳጳሱ ልዮን የንስጥሮስን ትምሕርት አለባብሰው ሊያስተምሩ ሲሞክሩ ግጭት በመፈጠሩ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሁለት ተከፈለች::

በጉባኤው የነበሩ ስድስት መቶ ሰላሳ ስድስት ጳጳሳት ስቃይና ሞትን ፈርተው በኑፋቄ መጽሐፍ ላይ በመፈረማቸው "መለካውያን" (ከእግዚአብሔር ይልቅ ለንጉሥ የሚታዘዙ) ተባሉ:: ጉባኤውም "ጉባኤ ከለባት" (የውሾች ስብሰባ): "ጉባኤ አብዳን" (የሰነፎች ጉባኤ) ተብሏል::

የወቅቱ የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ግን "በኑፋቄው ላይ አልፈርምም::" ከማለቱ አልፎ መናፍቃኑን አወገዛቸው:: በዚህ ምክንያት ጽሕሙን ነጭተው: ጥርሱንም አርግፈው: ወደ ጋግራ ደሴት ከሰባት ደቀ መዛሙርቱ ጋር አሳደዱት::
በዚያም ለሦስት ዓመታት ቆይቶ በ454 ዓ/ም ዐረፈ::

እግዚአብሔር ፈርዶባቸው ንጉሡ መርቅያን እና ንግሥቲቱ ብርክልያ (ክፉ ሴት ናት) ድንገት ሞቱ:: ፈተናው ግን በዚህ አላበቃም:: በዙፋኑ የተተካው ሌላኛው ጨካኝ ልዮን ነበር:: መንፈሳዊውን አርበኛ አባ ዲዮስቆሮስን በሞት ያጡት የግብጽ ክርስቲያኖች ደቀ መዝሙሩን "አባ ጢሞቴዎስን እንሾማለን::" ቢሉ ንጉሡ ከለከለ::

የሚሾመው መለካዊ ነው ብሎ አብሩታርዮስ የሚባል መናፍቅ ጳጳስ በላያቸው ላይ ሾመባቸው:: ይህንን መታገስ ለሕዝቡና ለካህናቱ ከባድ ነበር:: ተኩላ እንኳን በበጐች ላይ በይፋ ተሹሞ: ተደብቆም ቢሆን እየነጠቀ መብላት ልማዱ ነው:: መናፍቁ ጳጳስ በተለያየ መንገድ ሕዝቡን ለመሳብ ሞክሮ ነበር::

ለምሳሌ አውጣኪን (የክርስቶስን ሰው መሆን ምትሐት የሚል 'የቱሳሔ' አስተማሪ መናፍቅ ነው::) አወገዘው:: እነሱ ግን ተረድተውታልና ቦታ አልሰጡትም:: ምክንያቱም አውጣኪ ከቀድሞም የተወገዘ መናፍቅ ነውና:: የሚገርመው ከሕዝቡ አንድስ እንኳ ከመናፍቁ ጳጳስ የሚባረክ አልነበረም:: ሥጋውን ደሙንም ከእውነተኛ ካህናት በድብቅ ይቀበሉ ነበር::

አንድ ቀን ግን መናፍቁ ጳጳስ አብሩታርዮስ ተገድሎ ተገኘ:: (መልአክ ቀሥፎት ነው የሚሉ አሉ:: እስካሁን ድረስ የገዳዩ ማንነት አልታወቀም::) ግብጻውያን ክርስቲያኖች ግን የእርሱን ሞት ሲሰሙ ደጉን እረኛ አባ ጢሞቴዎስን ሾሙ:: ችግሩ የመጣው ከዚህ በኋላ ነው::

የመናፍቁ ተከታዮች ለንጉሡ ልዮን "አንተን ንቀው: የሾምከውን ገደሉ:: ሌላ ጳጳስም ሾሙ::" ብለው መልዕክት ላኩለት:: በዚህ የተበሳጨው ልዮን ኦርቶዶክሳውያንን ባገኛችሁበት ሁሉ ግደሉ የሚል አዋጅ አወጣ:: ይህን አዋጅ ተከትሎ ሰላሳ ሺ ሰዎች በእስክንድርያ ከተማ ተጨፈጨፉ::

ገዳዮቹ ወንድ: ሴት: ሕፃን: ሽማግሌ ሳይመርጡ የክርስቲያኖችን ደም አፈሰሱ:: ለሦስት ቀናትም ግድያው ቀጥሎ እንደ ነበር ይነገራል::
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት "ወኀጥኡ ዘይቀብሮሙ" እንዳለ ቀባሪም አጡ::

ገዳዮቹ ቀጥለውም አባ ጢሞቴዎስን አስረው አጋዙት:: ለአሥር ዓመታትም አሰቃዩት:: ከእነዚህ ዓመታት በኋላ ግን ንጉሡ ተጸጽቶ አባ ጢሞቴዎስን ወደ መንበሩ መልሶታል:: ወገኖቻችን የግብጽ ክርስቲያኖች እንኳን ያኔ ዛሬም በጽናታቸው አብነት ልናርጋቸው የሚገቡ ናቸው::

† አምላከ ሰማዕታት በቸርነቱ ይጠብቀን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

††† ነሐሴ 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ሰላሳ ሺ የእስክንድርያ (ግብጽ) ሰማዕታት
2.ቅዱስ ድምያኖስ ሰማዕት

† ወርኀዊ በዓላት
1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
3.ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እሥራኤል)
4.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
5.ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
6.አባ ሳሙኤል
7.አባ ስምዖን
8.አባ ገብርኤል

† "በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብጹዓን ናችሁ:: ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ: አትናወጡም:: ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት:: በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ:: ነገር ግን በየውሃነትና በፍርሃት ይሁን::" †††
(፩ጴጥ. ፫፥፲፫-፲፮)


† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †


ቤተሰብ ይሁኑ

https://t.me/Sinksar
https://t.me/Sinksar
https://t.me/Sinksar