Get Mystery Box with random crypto!

ሰዎች የነዱት ሰው ጸጸት “ሌሎች ሰዎች ከእኔ የሚጠብቁብኝን ሳይሆን እኔው ራሴ ያመንኩበትን ሕይወ | Agape Love❤

ሰዎች የነዱት ሰው ጸጸት

“ሌሎች ሰዎች ከእኔ የሚጠብቁብኝን ሳይሆን እኔው ራሴ ያመንኩበትን ሕይወት የመኖር ድፍረት ኖሮኝ ቢሆን ኖሮ!”

ብሮኒ በመጀመሪያ የምትተርከው ግሬስ ስለምትባል በታላቅ ጸጸት ውስጥ ስላለች ሴት ነው፡፡ ግሬስ ከሃምሳ አመታት በላይ በጋብቻ ሕይወት አሳልፋለች፡፡ ግሬስ ከልቧ ከምትወዳቸው ልጆቿ ከምታገኘው ደስታ ባሻገር “የአስራዎቹ” አመታት ወጣት የልጅ ልጆች ማግኘቷ የማይጠገብ የደስታ ምንጭ ሆኖላታል፡፡ ሆኖም፣ ይህ ደስታዋ ሙሉ እንዳይሆን ያደረገባት አንድ ጥቁር ነጥብ ግን በሕይወቷ ነበር፡፡ ይህም ሁኔታ የባለቤቷ ጉዳይ ነበር፡፡

አምባ ገነንና ጨካኝ የሆነው ባለቤቷ ባሳለፉት አመታት ውስጥ ጋብቻን አስቸጋሪ ያደረገባት ሰው ነበር፡፡ ወደጋብቻ ከመጡበት እለት ጀምሮ የቅስም ሰባሪ ቃላትና የተለያዩ የክፉ ተግባሮች ሰለባ አድርጓታል፡፡ ይህንንም ሁኔታውን ለማስተካከል መውሰድ የነበረባት እርምጃዎች እንዳሉ ብታውቅም፣ አንዱንም ምርጫ ለመውሰድ ድፍረቱ ሳይኖራት ለአመታት ተቀጥቅጣ ኖራለች፡፡ የባለቤቷ አስቸጋሪነት እጅግ ከመክፋቱ የተነሳ ከጥቂት አመታት በፊት ከእርጅና የተነሳ በአረጋውያን መጦሪያ ማእከል በመግባቱ እርሷ ብቻ ሳትሆን ሁኔታውን የሚያወቁ ሰዎች ሁሉ ደስተኛ ነበሩ፡፡

ግሬስ በትዳር አመታቶቿ በሙሉ አንድ ቀን ከባሏ ክፉ ተጽእኖና ጨካኝ ሁኔታ ውጪ ሆና ደስተኛ ሕይወትን ለብቻዋ የምታጣጥምበትን ቀን እንደናፈቀች ኖራለች፡፡ አሁን በሰማኒያዎች አመታት ውስጥ ብትሆንም፣ ለእድሜዋ የሚመጥን መጠነኛ ጤንነትና የአካል ብቃት ነበራት፡፡ ወደማእከሉ ስትመጣ ወዲህ ወዲያ ለማለት የሚያበቃት አቅም ነበራት፡፡

እድሜዋን በሙሉ “በድብደባ” ያሳለፈው አእምሮዋ አሁን ለዚህ ሁኔታ ከዳረጋት ባለቤቷ በመለየቷ ምክንያት የእረፍትን ጭላንጭል ያየ ይመስላል፡፡ ለብዙ ዘመናት የጠበቀችውን ይህንን ለብቻ የመሆንና ካለምንም የውጪ ሰው ተጽእኖ የማሰብ “ነጻነት” ባገኘች በአጭር ጊዜ ውስጥ በድንገት በጽኑ መታመም ጀመረች፡፡ ሕመሙ ከተሰማት ከጥቂት ቀናት በኋላ ብዙም እድሜ እንደማይኖራት የሚጠቁም ምልክት ተገኘባት፡፡ ሁኔታውን እጅግ ልብን የሚሰብር ያደረገባት፣ የህመሙ መንስኤ ለብዙ አመታት ባለቤቷ በቤት ውስጥ ሲያጨስ ከነበረው የሲጃራ ጭስ እንደሆነም ማወቋ ነው፡፡ የበሽታው ደረጃ እጅግ ከመክፋቱ የተነሳ በአንድ ወር ውስጥ አቅሟን ሁሉ አጥታ የአልጋ ቁራኛ ሆነች፡፡

“ለምን ያንን ዘመን ሁሉ እኔ ያመንኩበትንና የፈለግሁትን ነገር አላደረኩም? ለምን እንደፈለገ እንዲገዛኝና እንዲያንገላታኝ ፈቀድኩለት?” የሚሉት ጥያቄዎች ካለማቋረጥ ከግሬስ አንደበት ሲወጣ ይደመጥ ነበር፡፡ ያመነችበትን ትክክለኛ ሕይወት ለመኖር ድፍረት ሳይኖራት ዘመኗ በማለፉ ምክንያት በራሷ ላይ እጅግ በጣም ትበሳጭ ነበር፡፡ ልጆቿም ቢሆኑ እንደፈለገ ባደረጋትና ባደረገባት ባሏ ምክንያት ስላሳለፈችው ከባድ ሕይወት በግልጽ ይመሰክሩ ነበር፡፡

“አንቺ ማድረግ የምትፈልጊውን ትክክለኛ ነገር ከማድረግ ማንም ሰው እንዲከለክልሽ አትፍቀጂለት” በማለት ለተንከባካቢዋ ለብሮኒ ደጋግማ ትነግራት ነበር፡፡ “እባክሽን ይህንን እኔ የሰራሁትን ስህተት እንዳትሰሪ ቃል ግቢልኝ” በማለት ታሳስባት ነበር፡፡ አንድ ቀን ግሬስ ይህንኑ ምክር ደግማ ከነገረቻት በኋላ፣ ብሮኒ በእሺታ ምክሯን ተቀብላ እንደምትተገብረው ቃል በመግባት፣ “ራስን የመቻልና ያመኑበትን ትክክለኛ ነገር የማድረግን ትምህርት ያስተማረችኝ እናት ስለነበረችኝ እድለኛ ነኝ” በማለት ለግሬስ ነገረቻት፡፡

“አሁን ያለሁበትን ሁኔታ ተመልከችው” አለች፣ ግሬስ በመቀጠል፡፡ “በመሞት ላይ ነኝ፡፡ በሞት አፋፍ! እንዴት ቢሆን ነው እነዚያን አመታት ሁሉ ነጻና ራሴን የቻልኩ ሆኜ ለመሆን ስጠብቅ ኖሬ፣ አሁን እዚያ የተመኘሁበት የሕይወት ምእራፍ ላይ የደረስኩ ሲመስለኝ ጊዜው ያለፈብኝ?” እነዚህን መራራ ቃላት የሰማችው ብሮኒ የግሬስ ሁኔታና ጸጸት እንድታስብ ያነሳሳትን እውነታ ማሰላሰል ጀመረች፡፡

የደረሰችበትም ድምዳሜ፣ “ማንኛውም ሰው የራሱን አመለካከት ማወቅ፣ ትክክለኛውን መንገድ መለየትና ያንንም ያመነበትን ትክክለኛ ጎዳና መከተል አለበት” የሚል ነበር፡፡

ግሬስ በውስጧ የምታምንበትንና የሚሰማትን ስሜት ሳይሆን የዚያን ተቃራኒ ገጽታን በውጪ እያንጸባረቀች ዘመኗን አባከነች፡፡ እድሜዋን በሙሉ እርሷ ያመነችበትንና ከነበረባት የጭካኔ ሰለባ የሚያወጣትን ሕይወት ሳይሆን ሌሎች ሰዎች ከእርሷ የሚጠብቁባትን አይነት ሕይወት ስትኖር ካሳለፈች በኋላ፣ አሁን በመጨረሻዎቹ አመቶቿ ምርጫው የእርሷ እንደነበርና፣ ፍርሃት ከትክክለኛው ምርጫ እንደገታት ተገነዘበች፡፡ ራሷን ይቅር የማለት አስፈላጊነት ቢነገራትም እንኳን አሁን ሌላ ምርጫ ያለውን ሕይወት ለመኖር ጊዜው ያለፈባት መሆኑን ስታስብ ከአቅሟ በላይ የሆነ ስሜት ይወርሳታል፡፡

ብሮኒ በሞት አፋፍ ላይ ያሉ ሰዎች በሚኖሩበት ማእከል ውስጥ ስትሰራ ካጠናቻቸው የሰዎች ጸጸቶች ይህኛው፣ “ሌሎች ሰዎች ከእኔ የሚጠብቁብኝን ሳይሆን እኔው ራሴ ያመንኩበትን ሕይወት የመኖር ድፍረት ኖሮኝ ቢሆን ኖሮ!” የሚለው ጸጸት አብዛኛዎቹን ሰዎች የሚያጠቃውና ቀንደኛው ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የሕልማቸውን ግማሽ እንኳን ሳያጣጥሙ ዘመናቸው የሚያልፈው ያመኑበትን ትክክለኛ የሕይወት አቅጣጫ ለመከተል ምርጫ እንዳላቸው ካለማወቅና ወይም ትክክለኛውን ምርጫ እያወቁ ያንን ምርጫ ለመከተል ጉልበት ከማጣት የተነሳ ነው፡፡
@Kibirenaw