ተዘግቶ የቆየው የማዕድን ግልፅነት ጽሕፈት ቤት እንዲከፈት ተጠየቀ።
ከአሥር ዓመታት በፊት በማዕድን ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ማዕድን ኢንዱስትሪ ግልፅነት ኢንሼቲቭ ጽሕፈት ቤት መዘጋት ክፍተት እየፈጠረ ነው በማለት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ኅብረት (ኢሰመድኅ) እንዲከፈት ጠይቋል፡፡ ኅብረቱ የማዕድን ቁፋሮና ማውጣት ዘርፍ ላይ ጥናት ካደረገ በኋላ ነው በድጋሚ ፅህፈት ቤቱ እንዲደራጅ የጠየቀው፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪዎች ግልጽነት ኢኒሼቲቭ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ፣ ጋዝና ማዕድን ሀብት መልካም አስተዳደርን የሚያሰፍን እንዲሁም በዘርፉ ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚንቀሳቀስ ኢኒሼቲቭ መሆኑን ጥናቱ ያመላከተ ሲሆን መንግሥት ይህንን ጽሕፈት ቤት በድጋሚ እንዲያደራጅ እንዲሁም የሲቪል ማኅበራት ተሳትፎ እንዲጨምር ማድረግ እንደሚገባው ኅብረቱ ይፋ ባደረገው ጥናት ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን ኢኒሼቲቭ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ አብራ በመሆን የተቀላቀለች ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ያለውን ብሔራዊ ኢንሺቴቭ ጽሕፈት ቤት የማዕድን አውጪዎችን ተጠያቂነት በማስፈን፣ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ፣ የማዕድን ሚኒስቴር የኢኒሼቲቩን የማረጋገጫ ሪፖርት በማዘጋጀት የባለድርሻ አካላት ውይይትና መረጃ የማሠራጨት ሥራዎችን ይሠራ እንደነበር ሪፖርተር ፅፏል፡፡