Get Mystery Box with random crypto!

‍ ‍ ዐቂቃ ሌላ ለመውሊድ ሌላ! ~ ~ ~ ~ ~ ~~~~ ~ ከዚህ ቀደም እንደገለፅኩት የመውሊድ ጨ | አል አዝካር AL AZKAR

‍ ‍ ዐቂቃ ሌላ ለመውሊድ ሌላ!
~ ~ ~ ~ ~ ~~~~ ~
ከዚህ ቀደም እንደገለፅኩት የመውሊድ ጨፋሪዎች የማይገናኘውን ሁሉ ለዚህ የቢድዐ ድግስ ማስረጃ ለማድረግ ሲውተረተሩ ማየት የተለመደ ነው። በዚህ ረገድ ክሚያነሷቸው ከሸረሪት ድር የደከሙ ብዥታዎች ውስጥ አንዱ ነብዩ ﷺ ከነብይነታቸው በኋላ ለራሳቸው “ዐቂቃ አድርገዋል” የሚል ነው። “ህፃን እያሉ አቡ ጧሊብ ዐቂቃ እንዳደረጉላቸው ስለሚታወቅ ይህኛው ልደታቸውን በማስመልከት አላህን ለማመስገንና ለተከታዮቻቸውም ይህንኑ ለማስተማር ያደረጉት እንደሆነ ይታሰባል” ይላሉ በድፍረት።

መልስ፡-

1. በመጀመሪያ ሐዲሡ ብዙሃን ዑለማእ ዘንድ ደካማ ነው። ይህንንም በርካታ ዑለማዎች አስረግጠው ጠቁመዋል። ለምሳሌ፦

1.1. የሐዲሡ ዘጋቢ የሆኑት በይሀቂ እራሳቸው ስለ ሐዲሡም ስለ ሰውየውም እንዲህ ብለዋል፡- “ዐብዱረዛቅ እንዲህ ብሏል፡ ዐብዱላህ ብኑ ሙሐረርን የተውት በዚህ ሐዲሥ ሁኔታ ነው። በርግጥ በሌላ በኩል ከቀታዳ ይዞ፣ በሌላ ደግሞ ከአነስ ዘግቦታል። ነገር ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ውድቅ የሆነ ሐዲሥ ነው።” [አሱነኑል ኩብራ፡ 9/300] ተመልከቱ እንግዲህ ዘጋቢው እራሳቸው በዚህ መልኩ ያጣጣሉትን ጉዳይ ቁም ነገር አርገው የሚጠቅሱት። አንዳንዶቹማ አይናቸውን በጨው አጥበው በይሀቂ ይህንን ሐዲሥ ለመውሊድ ማስረጃ አድርገው ጠቅሰውታል ብለዋል። ይሄ የለየለት ቅጥፈት ነው።
1.2. ሐዲሡን ኢማሙ ማሊክም ደካማ እንዳሉት ኢብኑ ሩሽድ ገልፀዋል። [አልሙቀደማቱል ሙመሂዳት፡ 15/2]
1.3. ኢማሙ አሕመድ ይህንን ሐዲሥ ሙንከር እንዳሉት፣ ሰውየውንም ደካማ እንዳሉት ኢብኑል ቀዪም ገልፀዋል። [ቱሕፈቱል መውዱድ፡ 57]
1.4. ቡኻሪም ሰውየውን “የተተወ ነው” ብለውታል። [ፈትሑል ባሪ፡ 3/348]
1.5. አልበዛርም ሰውየው ደካማ እንደሆነ ገልፀዋል። [ከሽፉል አስታር ሚን ዘዋኢዲል በዛር]
1.6. ነወዊም “(ባጢል) ውድቅ የሆነ ሐዲሥ ነው” ብለዋል። [አልመጅሙዕ ሸርሑል ሙሀዘብ፡ 8/412]
1.7. ዘሀቢም የሐዲሡን አስተላላፊ ዐብዱላህ ብን ሙሐረርን በከባዱ ያብጠለጠሉ ሙሐዲሦችን ከዘረዘሩ በኋላ “ከጥፋቶቹ ውስጥ ከቀታዳ ከአነስ ብኑ ማሊክ ብሎ ነብዩ ﷺ ከተላኩ በኋላ ለራሳቸው ዐቂቃ አድርገዋል ማለቱ ነው።” ይላሉ፡- [ሚዛኑል ኢዕቲዳል፡ 2/500]
1.8. ኢብኑ ዐብዲል ሃዲ ደካማ እንደሆነ ገልፀዋል። [ሪሳለቱን ለጢፋህ፡ 54]
1.9. ኢብኑ ሐጀርም ሐዲሡ ደካማ እንደሆነ ገልፀዋል። [ፈትሑል ባሪ፡ 9/509]
1.10. ኢብኑል ሙለቀንም “ሐዲሡ በጣም ደካማ ነው ምክንያቱም ይሄ ዐብደላህ በምሁራን ኢጅማዕ በጣም ደካማ ነውና” ይላሉ። [አልበድሩ ልሙኒር፡ 9/339]
1.11. ሸውካኢም ዶዒፍነቱን ጠቁመዋል። [ነይሉል አውጣር፡ 5/228]
1.12. አልሙባረክፑሪም እንዲሁ ሐዲሡ ሶሒሕ እንዳልሆነ ገልፀዋል። [ቱሕፈቱል አሕወዚ፡ 5/97]
ይህ ሁሉ ሂስ ከመሰንዘሩም ጋር ሐዲሡን የተወሰነ ዋጋ የሰጡት አጋጥመዋል። ለምሳሌ ሸይኹል አልባኒ።

2. ነገር ግን ሶሒሕ ነው ብንል እንኳን ዛሬ ለሚፈፀመው የቢድዐ መውሊድ ፈፅሞ መረጃ መሆን አይችልም። ምክንያቱም በሐዲሡ የተጠቀሰው ዐቂቃ እንጂ መውሊድ አይደለምና!! ቃል በቃል ሐዲሡ ውስጥ የተጠቀሰውን ጥሎ ያለ ተጨባጭ መረጃ በሌለበት “ድሮ አያታቸው ዐቂቃ ስላወጡላቸው ይሄኛው መውሊድ ነው” ማለት ከንፁህ ጥናት ያፈነገጠ ስሜት የተጫነው ድምዳሜ ነው። ከጥንት ጀምሮ ዑለማዎች ይህንን ሐዲሥ ያሰፈሩትና ያጠኑት ቀድሞ ዐቂቃ ያልወጣለት ሰው ኋላ በራሱ መፈፀም ይችላል ወይስ አይችልም በሚል ጉዳይ ላይ እንጂ ፈፅሞ ለመውሊድ አይደለም።

3. የሰነዱ አጠያያቂነት እንዳለ ሆኖ እሳቸው የፈፀሙት በህይወታቸው አንዴ ብቻ ነው። እናንተ መውሊድ ብላቸሁ የምትሰባሰቡት በያመቱ ነው። ምኑን ከምኑ ነው የምታገናኙት?

4. ደግሞስ ዐቂቃ የልደት በዓል ነውንዴ? ሰዎቹ ዐቂቃና መውሊድ አይለዩም ማለት ነው? ዐቂቃኮ አቅሙ የሚችልን ሙስሊም ሁሉ የሚመለከት እርድ እንጂ በነብዩ ﷺ ላይ የተገደበ አይደለም። ለመሆኑ ለህፃናት የሚታረደውን ዐቂቃ መውሊድ ብላችሁ ነው እንዴ የምትጠሩት? ዐቂቃውን የልጆቹን የልደት ቀናቸውን እየጠበቃችሁስ ነው የምትፈፅሙት? አንዴ ካረዳችሁ በኋላ በያመቱስ ነውንዴ የምታከብሩት?

5. ደግሞስ ነብዩ ﷺ ዐቂቃውን የፈፀሙት በልደት ቀናቸው ነው ወይም ረቢዑል አወል 12 ነው የሚለውን ከየት ነው ያመጣችሁት? እንዲህ አይነት ጥቆማ በሌለበት በምን ስሌት ነው ለመውሊድ ማስረጃ የሚሆነው?

6. እውነት እንደምትሉት ነብዩ ﷺ ዐቂቃውን ያደረጉት ተከታዮቻቸው መውሊድን እንዲያከብሩ ለማስተማር ከሆነ ምነው ታዲያ ሶሐቦች እርድ እየፈፀሙ በያመቱ መውሊዳቸውን ሳያከብሩት ቀሩ? መቼም እንደ ሺዐዎች ስላፈነገጡ ነው እንደማትሉ ተስፋ እናደርጋለን። ስላልተመቻቸው ነው ማለት የለየለት ቅጥፈት ነው። ከነብዩ ﷺ ሞት በኋላኮ አንድና ሁለት አመት አይደለም የኖሩት!! ያን ሁሉ ዘመን ሁሉም ሶሐባ አልተመቸውም ይባላል። ሁለቱን ዒዶች ሲያከብሩ አልነበር? ሌሎች ዲናዊ ተግባራትን ሲያከናውኑ አልነበር? እነሱም፣ ታቢዒዮቹም፣ አትባዑ ታቢዒንም፣ የሐዲሥ ምሁራንም፣ አራቱ ኣኢማዎችም አለማክበራቸው ምንድነው የሚያሳየው? “አክብረውትስ ቢሆን ምን አሳወቀን?” እንዳትሉ በነዚያ ነብዩ ﷺ ምርጥነታቸውን በመሰከሩላቸው ትውልዶች ዘመን መውሊድ የሚባል እንዳልነበረ ኢብኑ ሐጀር፣ ሰኻዊ፣ ሲዩጢ፣ ዒራቂ፣ ተዝመንቲ፣... መናገራቸውን አሳልፌያለሁ። ፈርተው ነው ያልፈፀሙት ማለትም አይን ያወጥዐ ቅጥፈት ነው። ምክንያቱ አንድና አንድ ብቻ ነው። መውሊድ የሸሪዐ መሰረት ስለሌለው ብቻ! ይህ ነው እነሱ ጋር የነበረው ግንዛቤ!! እንጂ የሸሪዐ መሰረት ቢኖረው ኖሮ ለእምነታቸው ሲሉ አገር ንብረታቸውን ጥለው የተሰደዱ፣ ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ፣ ከስጋ ዘመዶቻቸው ጋር የተሞሻለቁ፣ በሕቅ ላይ የወቃሽን ወቀሳ የማይፈሩ፣ የጀኝነት፣ የቆራጥነት፣ የተቅዋ፣ ... ተምሳሌቶች ናቸው። ለነብዩ ﷺ የነበራቸውም ወዴታ ወደር አልነበረውም። በጭፈራ ሳይሆን በተግባር የሚገለፅ ነበር። ከሳቸው በመከላከል ለነፍሶቻቸው ሳይሰስቱ እራሳቸውን ፊዳ በማድረግ ደረታቸውን ለቀስት የሚሰጡ የተመረጡ ትውልዶች ናቸው። ይልቅ በተዘዋዋሪም ቢሆን አጉል ከነሱ በላይ ነብዩን ﷺ እንወዳለን ከሚመስል እብሪት ብትርቁ ይሻላችኋል።
~~

ኢብኑ ሙነወር
የቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/alazkare
https://t.me/alazkare