Get Mystery Box with random crypto!

መውሊድ በማን ተጀመረ? በሙዞፈር ወይስ በ“ፋጢሚያ” ሺዐ? ~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~ | አል አዝካር AL AZKAR

መውሊድ በማን ተጀመረ? በሙዞፈር ወይስ በ“ፋጢሚያ” ሺዐ?
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
ሰሞኑን አሕባሾች መውሊድን በማስተዋወቅ ላይ ተጠምደው እያየን ነው። ከሚያነሷቸው ነጥቦች አንዱ መውሊድ “ታላቅ ዓሊም፣ ተቂይ፣ ሷሊሕና ጀግና በነበሩት” ንጉስ ሙዞፈር ነው የተጀመረው የሚል ነው። ሙዞፈር የሞተው ከ812 አመት በፊት በ630 ሂጅሪያ ነው። ሰዎቹ ሙዞፈር ላይ ችክ የሚሉት እጅግ አፈንጋጭ በሆኑት “ፋጢሚያ” ሺዐዎች ነው የተጀመረው የሚለውን ለመሸሽ ነው። እርግጥ ነው መውሊድ የተጀመረው በሙዞፈር ነው ያሉ አሉ። ሌሎች ደግሞ የለም ትንሽ ቀደም ብሎ በሸይኽ ዑመር አልመላ (571 ሂ.) ነው የሚሉም አሉ። ሁለቱም ሃሳቦች ግን በማንም - እደግመዋለሁ - በማንም ቢጠቀሱ ፈፅሞ ስህተት ናቸው፡፡ ምክንያቱም ከዚያ በፊት በአፈንጋጭ ሺዐዎች እንደተጀመረ የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች አሉና፡፡ ማስረጃ ከቀረበ በኋላ ለማንም ሙግት እጅ አንሰጥም፡፡ ለሐቅ እጅ ለሚሰጡ፣ ከመንጋዊ አስተሳሰብ አግልለው ህሊናቸውን ለሚያከብሩ ሰዎች ብቻ ማስረጃዎቹን አሰፍራለሁ።

1. ኢብኑል መእሙን (587 ሂ.):—

በታሪክ ድርሳናት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መውሊድ ተጠቅሶ የተገኘው በኢብኑል መእሙን ስራ ነው። የኢብኑል መእሙን አባት የ“ፋጢሚያ” ንጉስ ከፍተኛ ባለሟል ነበር። የታሪክ ፀሐፊው አልመቅሪዚ (845 ሂ.) ኢብኑል መእሙንን በማጣቀስ በ517 ሂጅሪያ የተካሄደውን መውሊድ አስመልክተው እንዲህ የሚል መረጃ አስፍረዋል፡-
“የ‘ፊጢሚያ’ ገዢዎች በዓላትና ለተገዢዎቻቸው ነገሮችን ሰፋ የሚያደርጉባቸው እንዲሁም ችሮታ የሚበዘባቸው ዓውደ-አመታት” ካሉ በኋላ እንዲህ ይላሉ፡- ለፋጢሚያ ገዢዎች በአመቱ ውስጥ በዓላትና ዓውደ አመታት አሏቸው። እነሱም … የዓሹራእ ቀን፣ የነብዩ - ﷺ - ልደት (#መውሊድ) ቀን፣ የዐሊይ ብኑ አቢ ጧሊብ ረዲየላሁ ዐንሁ ልደት ቀን፣ የሐሰን የልደት ቀንና የሑሰይን የልደት ቀን (ሰላም በነሱ ላይ ይሁንና)፣ የፋጢመቱ ዘህራእ ዐለይሃ ሰላም ልደት ቀን፣ ስልጣን ላይ ያለው ገዢ የልደት ቀን፣ … የገዲር ዒድ (የሺዐዎች ነው)” እያሉ ይዘረዝራሉ። ከውስጣቸው የፋርስ መጁሳዎች፣ የሺዐና ከክርስትና ደግሞ እንደ ገና እና ትንሳኤ ያሉ በዓላት የተካተቱበት ሲሆን ባጠቃላይ 28 በዓላት ናቸው የተዘረዘሩት። [አልኺጦጥ፡ 1/436]
መውሊድ ከምን አይነት በዓላት ጋር እንደተጀመረ ተመልከቱ። በሌላ ኪታባቸው ላይም “በረቢዐል አወል ላይ (የ“ፋጢሚዮቹ” ንጉስ) ሌሊት ላይ በጎዳናዎችና መንገዶች ላይ ጧፎች እንዲበሩ ያስገድድ ነበር” ይላሉ። [ኢቲዒዙል ሑነፋእ፡ 2/48] ሌላ ቦታ ደግሞ “ረቢዐል አወል ላይ የነብዩን - ﷺ - ክቡር ልደት መፈፀም ብሄራዊ ልምድ ሆኖ ቀጠለ” ይላል። [ኢቲዒዙል ሑነፋእ፡ 3/101] ልብ በሉ! ይህንን መረጃ የሰጠን ኢብኑል መእሙን የሞተው መውሊድን ጀመረ የሚባለው ንጉስ ሙዞፈር ገና በተሾመ በአመቱ ነው፡፡ እያስተዋላችሁ!!

2. ኢብኑ ጡወይር (617 ሂ.):—

ሌላኛው መውሊድን ከ“ፋጢሚዮች” ጋር በማያያዝ የጠቀሰው ጥንታዊ የታሪክ ፀሐፊ ኢብኑ ጡወይር ነው። ኢብኑ ጡወይር ለነዚህ “ለፋጢሚያ” መንግስት ፀሐፊ ሆኖ አገልግሏል። ኋላ በሶላሑዲን አልአዩቢ ሲደመሰሱም በአይኑ ተመልክቷል። በዚህኛው ስርኣትም ውስጥ ዳግም አገልግሏል። በ“ፋጢሚያዎች” መንግስት ስለሚዘጋጀው መውሊድና ስለተትረፈረፈ ምግቡ “ኑዝሀቱል ሙቅለተይን ፊ አኽባሪ ደውለተይን” በተባለ ኪታቡ ላይ በዝርዝር አትቷል። “ማን ያውራ የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ” ይላል ያገራችን ሰው። ለናሙና ያክል ቀንጨብ ላድርገው፡-
ذكر جلوس الخليفة في الموالد الستة في تواريخ مختلفة، وما يطلق فيها، وهي مولد النبي صلى الله عليه وسلم، ومولد أمير المؤمنين علي بن أبي طالب، ومولد فاطمة عليها السلام، ومولد الحسن، ومولد الحسين عليهما السلام، ومولد الخليفة الحاضر
“ኸሊፋው በተለያዩ ጊዜያት በስድስቱ መውሊዶች ላይ የሚያደርጋቸውን መስሰየምና ምን ተብለው እንደሚታወቁ ማውሳት፡- እነሱም የነብዩ- ﷺ - መውሊድ፣ የአሚረል ሙእሚኒን ዐሊይ ብኑ አቢ ጧሊብ መውሊድ፣ የፋጢማ ዐለይሃ ሰላም መውሊድ፣ የሐሰን መውሊድ፣ የሑሰይን - ዐለይሂመ ሰላም - መውሊድና የዘመኑ ኸሊፋ መውሊድ ናቸው፡፡ …” [ኑዝሀቱል ሙቅለተይን፡ 217-219]

3. አሕመድ ብኑ ዐሊይ አልቀልቀሸንዲ (821 ሂ.):—

ስለ “ፋጢሚያ” መሪዎች ጉባዔ ሲያወሩ “ሶስተኛው ጉባዔ በረቢዐል አወል ወር 12ኛ ቀን ላይ በነብዩ - ﷺ - መውሊድ ላይ የሚኖረው ጉባዔ ነው” ካሉ በኋላ ዝርዝር አፈፃፀሙን ይተርካሉ፡፡ [ሱብሑል አዕሻ፡ 3/576]

ስናጠቃልል የመውሊድ በዓል ጀማሪዎች “ፋጢሚያ” ሺዐዎች እንደነበሩ ለጥርጣሬ ቀዳዳ የማይሰጡ መረጃዎች አሉን ማለት ነው፡፡ ልብ በሉ! የመጨረሻው የ“ፋጢሚዮች” ንጉስ አልዓዲድ ሊዲኒላህ የሞተው በ 567 ሂጅሪያ ነው፡፡ ሱፍዮች “መውሊድ ጀመረ” የሚሉት ሙዞፈር የተሾመው ደግሞ ከ 19 ዓመታት በኋላ በ586 ሂ. ነው፡፡ ይህንን ተጨባጭ ታሪካዊ መረጃ እያየ “አይኔን ግንባር ያርገው” የሚል ካለ የለየለት ቂላቂል ነው፡፡ መውሊድ በሺዐዎች እንደተጀመረ የሚጠቁሙ ግልፅ ማስረጃዎች እየቀረቡ እያዩ “እከሌ እንዲህ ብለዋል” “እንቶኔ እንዲህ ብለዋል” እያሉ ነገር መዘብዘብ እራስን መሸወድ ብቻ ነው፡፡
“ሙዞፈር ነው የጀመረው” ያሉት እንደ ሲዩጢ ያሉ የኋለኛው ዘመን ሰዎች ከመሆናቸውም በላይ ያጣቀሱት ተጨባጭ ማስረጃ የለም፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ መውሊድ በሙዞፈር ነው የተጀመረው የሚሉ አካላት ኢብኑ ከሢርን ሲያጣቅሱ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ኢብኑ ከሢር የሙዞፈርን መውሊድ ከመጥቀሳቸው ውጭ “ጀማሪ ነው” አላሉም፡፡
መቅሪዚ እንደጠቀሱት እነዚህ የሺዐዎቹ መውሊዶች ኋላ ላይ ለተወሰኑ ጊዜያት ተቋርጠው ነበር፡፡ [አልመዋዒዝ ወልኢዕቲባር፡ 1/432] ኋላ ላይ በተተካው የ“ፊጢሚዮቹ” ንጉስ አልኣሚር ቢአሕካሚላህ (524 ሂ.) ነው የተጀመሩት፡፡ ልብ በሉ! ይህ ዳግም የተጀመረው መውሊድ እራሱ ከሙዞፈር መውሊድ በዓል ብቻ ሳይሆን ከራሱ ሙዞፈር መወለድም የቀደመ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ሱፍዮች መውሊድን ጀመረ የሚሉትን ሙዞፈርን ቅዱስ አድርገው የሚጠቅሱት ወይ ታማኞች ስላልሆኑ ነው፡፡ ወይ ደግሞ በሰውየው ላይ የቀረቡ ሂሶችን ያልተመለከቱ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ የሚያደርጉት ለገበያቸው የሚሆናቸውን እየመረጡ ማቅረብ ነው፡፡ ንጉሱ በከፊል የታሪክ ፀሐፊዎች ከመወደሱም ጋር የሰላ ሂስ የሰነዘሩበትም አሉ፡፡ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡-
ያቁት አልሐመዊ ይባላሉ፡፡ በ626 ሂ. የሞቱ ታዋቂ የታሪክ ምሁር ናቸው፡፡ ሙዞፈርን አስመልክተው እንዲህ ይላሉ፡-
“የዚህ ሰውየ ባህሪ እርስ በርሱ የሚቃረን ነው፡፡ እሱ ሲበዛ በዳይ፣ ህዝቦቹ ላይ ጨካኝ እንዲሁም አግባብ ባልሆነ መልኩ ገንዘቦችን የሚወስድ ነበር፡፡ ይህ ከመሆኑ ጋር ለድሃዎች የሚቸርና ለእንግዶች በብዛት የሚሰድቅ ነበር፡፡ እጅግ በርካታ ገንዘቦችን አፍስሶ ከከሃዲዎች እጅ ምርኮኞችን ነፃ ያወጣ ነበር፡፡ በዚህ ላይ ባለቅኔው እንዲህ ይላል፡-

‘ልክ እንደዚያች ወጥ ረገጥ
በብልቷ ነግዳ ለበጎ ስራ የምትሮጥ
መስሚያ ካለሽ ወዮ ላንቺ!
ምፅዋትሽ ይቅር ይልቅ አትዘሙቺ፡፡’ ” [ሙዕጀሙዑል ቡልዳን፡ 1/138]