Get Mystery Box with random crypto!

AB PHOTOGRAPHY & GRAPHIC DESIGN #እግር_በእግር አን | ከመጻሕፍት ዓለም 🇪🇹

AB PHOTOGRAPHY & GRAPHIC DESIGN

#እግር_በእግር

አንድ ቀን ሰይጣን በመንደሩ ወደሚፈሩት እና ወደ ሚከበሩት አስር አለቃ ደባልቄ ግዛው ቤት ሔደና ቀዳሚሚ ተከታይም ሳያደርግ "ደባልቄ!!" ብሎ በስማቸው ጠራቸው፡፡

አስር አለቃ ፊታቸውን በቁጣና በግርምት አኮማትረው ድምፁን ወደሰሙበት ዞር ቢሉ በአካባቢው ሰው የሚባል የለም፡፡ እዚህ ሰፈር አንድም ሰው የአስር አለቅነትን ማዕረጋቸው ሳያስቀድም የአባቻቸውን ስም ሳያስከትል እንዲህ ንፋስ እንዳነሳው ፌስታል ስማቸውን ለብቻው አንጠልጥሎ የሚነሳ ሰው የለም፡፡

እንኳን ሰው የዚህ ሰፈር ሰይጣን ቢሆን ራሱ እንደዚህ አስር አለቃን አቃሎ እና አበሻቅጦ ይጠራቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ እንዴት ሆኖ! ምን ሲደረግ...!

እንግዲህ አስር አለቃ የተጣሉ ባልና ሚስት አስታርቀው ገና መመለሳቸው ነበር፡፡ ልክ በራቸው ላይ ሲደርሱ ነው ሰይጣን የጠራቸው፡፡ ምን ይጠራቸዋል ያዋረዳቸው እንጂ! ቢሆንም 'ጆሮዬ ነው' ብለው ወደ ቤታቸው ግቢ ሊገቡ ርምጃ ሲጀምሩ፣

"አንተ ደባልቄ ! የሚደባልቅ ይደባልቅህ! ሲጠሩ አትሰማም!? ደንቆሮ!!" ብሏቸው እርፍ፡፡ በዚህ ቢበቃማ ጥሩ ነበር "ምን ያራሩጥሃል? ያቺ መንሽ እግር ሚስትህ እንደሆነች የትም አትሔድብህ ተወዝፋ ነው የምትጠብቅህ" ሲል ዘለፋቸው፡፡

አስር አለቃ መጀመሪያ በተናጋሪው ድፍረት ግርርርርርርርርምምምምምም አላቸው ቀጥሎ የንግግሩ ትርጉም አዕምሮአቸው ውስጥ ሲተረጎም ደማቸው ፈላ፡፡ ላለፉት አርባ ዓመታት እንዲህ ተንቀውም እንዲህ ደማቸው ፈልቶም አያውቅም፡፡ ከዘራቸውን ጠበቅ አድርገው ጨበጡና ድምፁን ወደሰሙበት ፎክረው ዞሩ፡፡

"ያንበሳው ግልገል!" በአካባቢው የሰው ዘር የለም!!

"እንኳን ፊቴ ያላገኘሁት ደመ ከልብ አድርጌው ዘብጥያ መውረዴ ነበር፡፡" አሉና ከዘራቸውን ወደ ግራ እጃቸው አጋብቸው ከዘራ በያዙበት እጃቸው አማተቡ፡፡

"ሂሂሂሂሂሂሂሂሂሂሂሂሂሂሂሂሂሂሂ..." የሰይጣን የሚያበሳጭ እና የሚሰቀጥጥ ሳቅ ጆሮአቸው ሥር ተቅለጨለጨ.......

" ድሮም ከእግዜራችሁ በፊት ዱላችሁ ነው ትዝ የሚላችሁ....ነውጠኛ ሁሉ.... #የምትዠልጠው_ስታጣ_ታማትባለህ? አይሸፋፋው አስር አለቃ....ሂሂሂሂሂ ሁሁሁሁ ቂቂቂቂቂ..." አለ ሰይጣን ግቢ ግቢያቸው ውስጥ ቀድሞ ገብቶ #ካሉበት_አርባ_ክንድ_ርቆ ከቆመ በኀላ፡፡

አስር አለቃ ግራ ተጋቡ፡፡ ንዴታቸውን ዋጥ አድርገው እየተጣደፉ በቁጣ ወደ ቤታቸው በር ገሰገሱ፡፡

አስር አለቃ አቋማቸው እንደሰምበሌጥ ቀጥ ያለ ስፖርተኛ አቋም ነው፡፡ ሰው ሁሉ "አቤት ቁመና!!" ይላቸው፡፡ ሰይጣን ግን ወደ ቤታቸው ሲጣደፉ የሚያበሽቅ ንግግር

"ሸፋፋ ..ሸፋፋ ትላለህ! ሲራመዱ አይተህ...ደግሞ ወታደር ነኘ ይላል እንዴ? ይሄን ደጋን የመሰለ እግር ይዞ ሂሂሂሂሂሂ...እንኳን አገር ልትጠብቅ በዚህ ሸፋፋ እግርህ ሚስትህንም አትጠብቅ ተመልከት የእግርህን ክፍተት በልጅነትህ ፀሐይ አላሞቀችልህም ያቺ ጨብራራ እናትህ!!! ኪኪኪኪኪ..."

አስር አለቃ ከሳቸው አልፎ እናታቸው ማዋረዱ ቢያንገበግባቸውም የተናጋሪው ማንነት ስለገባቸው እንደገና አማተቡና

"የማርያምን ብቅል ፈጭቻለሁ ቱ! ቱ! ቱ! አንተ ፖለቲከኛ ሰይጣን!" ብለው ወደ መሬት አንዴ ወደሰማይ ትፍ! ትፍ! ቀጠል አድርገውም " አንተ ክፋ አውቄኻለው እንዲ አቅልሎ የሚጠራኘ እንዳንተ ያለው ቀላል እንጂ ሌላ እንደማይሆን መች አጣሁት?" ካሉ በኀላ ቆይ ላግኘህ ሚመስል ዛቻ ከዘራቸውን ነቀነቁና ነጠቅ ነጠቅ ብለው በመራመድ ወደቤታቸው ገቡ፡፡

ሰይጣንም አጀንዳውን ከፍቶ "አስር አለቃ ደባልቄ" በሚለው ፊት ለፊት በቀይ እስኪሪቢቶ 'ራይት' አደረገ፡፡ መንገዱንም ቀጠለ! እየሳቀ እና እያፏጨ...! ይሄ ሸፋፋ ለዛሬ ይበቃዋል ሲበሳጭ ይደር፡፡ ነገ ደሞ በተመቸኘ ሰዓት ብቅ ብዬ ነጅሼው እሔዳለሁ፡፡ አለና እየሳቀ መንገዱን ቀጠለ፡፡

አስር አለቃ ቤት ግራና ቀኘ ባሉት ጫት ቤቶች ተኮልኩለው ጫት የሚቅሙትን ወጣቶች በኩራት እየተመለከተ
"ርስቴ እየተስፋፋ ነው!" ብሎ እየኮራ ቁልቁቅል ወደ ወንዙ!

በእርግጥም ሰይጣን እንዳሰበው አስር አለቃ ሌሊቱን እንቅልፍ በዓይናቸው ሳይዞር ነበር ያደረው፡፡ እንደዛ ያበሻቀጣቸው ሰይጣን ነው ለማለት ጥርጣሬ ገባቸው "እኔ የትኛው ቅድስና ኖሮኘ ሊፈትነኘ ይመጣል?"
አሉ ለራሳቸው፡፡ እንደውም አንዱ ጎረቤታቸው ተደብቆ እንደሰደባቸው ጠረጠሩ፡፡ "ማን ሊሆን ይችላል? ሌሊቱን ሙሉ ተብሰለሰሉ ፡፡

"ይች ጎረቤቴ የትነበርሽ ትሆን እንዴ? የለም ድምፁ የወንድ ነው፡፡ ግንበኛው አሰፋ መሆን አለበት እሱ ለካ ለሥራ ክፍለሃገር ከሄደ ሁለት ወሩ... እና ማናባቱ ነው...፡፡" ወደ ንጋቱ ላይ አንድ ሃሳብ ብልጭ አለላቸው፡፡ አረጋ!! ድንበር እየገፋ የበጠበጣቸው ጎረቤታቸው!! አረጋ! እሱስ ሚስታቸውን በምኞት ዓይኑ የሚቃኘ ጥጋበኛ ነው ድምፁ መጣላቸው ራሱ ነው!

"አገኘሁት ብለው ዘለው ከአልጋቸው ተነሱ፡፡ ሚስታቸው እማማ የውብዳር በአስር አለቃ አነሳስ ደንግጠው

"በስማም ምን ሆኑ? ሲሉ ጠየቁ

"ዝም በይ ሸፋፋ!" ሲሉ ሚስታቸውን ሰደቧቸው ከሰይጣን በተዋሷት ያደረች ስድብ፡፡ አስር አለቃ ከዛ በፊት ሚስታቸው ሰድበው አያውቁም ነበር፡፡ ልብሳቸውን ለባብሰው እየተጣደፉ ሲወጡ ሚስታቸው አልጋው ላይ ሆነው አሰቡ

"ይሔን ሁሉ ዘመን ዓይቶት የማያውቀውን የእግሬን መንሻፈፍ ዛሬ እንዴት ታየው? ምናልባት ወጣት ሴት ዓይቶ ይሆን? ማን ያውቃል ...? ባላቸውን ካገቧቸው ጀምሮ ዛሬ ገና ተጠራጠሩ፡፡

ልጃቸው ስንቄ እንደ ሁልጊዜው ከመኘታዋ ተነስታ እያንጎራገረች ነበር፡፡ ለሙዚቃ ከፍተኛ ፍቅር ያላት ስንቄ በተለይ የአስቴርን አወቀን ዘፈኖች ስትዘፍን ታስደምማለች፡፡ ዛሬ ግን እናቷ ድንገት አንባረቁባት

"ወዲያ ዝም በይ! ምን በጧቱ ታንቋርሪብኛለሽ!"

ስንቄ በእናቷ ንግግር ክፉኛ ተበሳጨች፡፡ እስከዛሬ ሲያንቋርር ነበር "የኔ ልጅ ድምጿ ብቻ የወፍ ዘር የሚያረግፍ..." እያሉ ዛሬ ታዲያ ምን ነካቸው? ስታምሰለስል ድንገት ጓደኛዋ ሊበን ደወለ፡፡

ዛሬ "ሰርፕራይዝ" ሊያደርጋት ጓደኞቹን አዘጋጅቶ እየጠበቃት ነው፡፡ እንድታገባው ሊጠይቃት ወስኗል ጓደኞቹ ጋር ቤቱ ቅልብጭ ያለ ፕሮግራም አዘጋችቶ ድንገት ሊነግራት የቃል ኪዳን ቀለበቱን አዘጋጅቶ በጉጉት እየጠበቃት ነው፡፡

"ሄሎ!" አለች እንደከፋት

"ሄሎ...! ምነው ድምፅሽ?" አላት እንባ ተናንቋት ስለተናገረች ድምጿ በእርግጥም ድክም ብሎ ነበር፡፡

"ድምፄ ምን ሆነ? ስትል ጠየቀችው፡፡

"ተንቋረረ ልበል?" አላት ፈገግ ብሎ፡፡ ስልኩን ጆሮው ላይ ጠረቀመችበት፡፡

ዘፋኘነትም ከዚህ በኀላ ዋጋ እንደሌለው ገባት፡፡ አርፋ የፀሀፊነት ሥራዋን ለመስራት ወሰነች፡፡ "አንቋራሪ ድምፅ " ያውም በእናቷና በምቶደው ፍቅረኛዋ የተመሰከረበት...፡፡ እስከዛሬ ሰው ፊት 'ስታንቋርር' ሁሌም ሲታዘባት በሹክሹክታ ሲቀልድባት እነንደኖረች ተሰማትና አፈረች!!

###
ኡኡኡኡኡኡኡኡኡ....ከወደውጪ ድምፅ ተሰማ...........

ክፍል ሁለት ይቀጥላል

#ካሉበት_አርባ_ክንድ_ርቆ ከቆመ በኀላ፡፡ እኔ እንደጨመርኩበት ልብ ይሏል

@jahABP ነኘ አስተያየታችሁን አድርሱኘ