Get Mystery Box with random crypto!

የአምላክ እናት በዘይቱን ማርያም ከመጋቢት 24 ጀምሮ ለ3 ዓመታት የተገለጠችበት የበረከት በዓል | መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

የአምላክ እናት በዘይቱን ማርያም ከመጋቢት 24 ጀምሮ ለ3 ዓመታት የተገለጠችበት የበረከት በዓል
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
❖ በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን በእኛ አቈጣጠር ከ1960 ዓ.ም. ላይ ከመጋቢት 24 ጀምሮ በካይሮ ባለችው በዘይቱን ማርያም የብርሃን እናቱ የቅድስት ድንግል ማርያም መገለጥ ይታሰባል። የአምላክ እናት በዘይቱን ማርያም የመጀመሪያው መገለጧ የተደረገው መጋቢት 24 ሲኾን ብርሃንን ለብሳ በጉልላቱ ላይ ተገልጣ በታየች ጊዜ ወደ 250,000 የሚጠጉ የሚያምኑም የማያምኑም ሕዝቦች ተሰብስበው በታላቅ ደስታና ምስጋና ያን አስደናቂ መገለጥ ይመለከቱ ነበር፡፡

❖ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሚያዝያ 1 በድጋሚ በታላቅ ብርሃን ታጅባ በታላቅ ግርማ ተገለጠች፤ ከዚያም በኹለት ሳምንት በሦስት ሳምንት ልዩነት በታላቅ ብርሃን እየታጀበች በመገለጥ እስከ 1963 ዓ.ም. ድረስ ለሦስት ዓመታት ታይታለች፡፡

አስደናቂው የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን በዚህ ሊንክ ይመልከቱ



❖ ንግሥታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ ክርስቲያኑ ጉልላት ላይ ስትገለጥም ለ2 ሰዓታት ከዚያ የበለጠ ሰዓትም ትታያቸው ነበር፤ መላእክትም በአርአያ ብሩሃን አርጋብ ዙሪያዋን ክንፋቸውን ዘርግተው ሲመላለሱ ይታዩ ነበር፤ ሌላው አስደናቂ የነበረው ክስተት እንደ ዕንቊ ፈርጥ የመሰሉ አስደናቂ ብርሃናት በዙሪያዋ ይፈስሱ ነበር።

❖ ይልቁኑ እጅግ አስደናቂ ቀይ ሕብረ ብርሃናማ ደመና በዙሪያዋ ከብቧ ነበር፤ ልዩ መዐዛ ያለው ዕጣንም በእጅጉ ይሸት ነበር፤ የታመሙትም በእንዲኽ ባለ ክብር በምትገለጥ ጊዜ ከሕመማቸው ይፈወሱ ስለነበር ኹሉም የታመመ ይመጣ ነበር፡፡ ይኽ የተገለጸችበት የዘይቱን ማርያም ቤተ ክርስቲያን እመቤታችን ጌታን ይዛ በተሰደደች ጊዜ ያረፈችበት የተቀደሰ ቦታ እንደነበር የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ያስተምራሉ፡፡

❖ በዚያን ጊዜ የነበሩት የግብጽ ፓትርያርክ በቅድስና ሕይወታቸው በጣም የታወቁት አቡነ ቄርሎስ ነበሩና ከብፁዓን አባቶች ጋር የእመቤታችን መገለጽ አማናዊ መኾኑን በዐይናቸው በማየት በጸሎት በሱባዔ በመታገዝ አረጋግጠው ሚያዝያ 26 በይፋ መገለጧን የሚያረጋግጥ ጽሑፍን ጽፈዋል፡፡ ይኽ መገለጧ በመላው ዓለም በመሰማቱ የሮም ቤተ ክርስቲያን ልዑካንን በዚኽ ጉዳይ ወደ እስክንድርያ በመላክ አረጋግጣለች፡፡

❖ ይኽነን በግብጽ በዘይቱን ማርያም የመገለጧን ነገር ምስክርነት በጊዜው የግብጽ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጀማል አብደል ናስር ጭምር ያረጋገጡ ሲኾን በግብጽ ቴሌቭዥን በዜና አውታሮች ኹሉ ሲተላለፍ ነበር፡፡ ይኽነን መገለጧን በሚሊየን የሚቈጠሩ የኮፕቲክ ክርስቲያኖችና ሌሎች የእምነት ተከታዮችና ኢአማንያን ጭምር አይተው ምስክርነታቸው ሰጥተዋል።

❖ የመገለጧን 50ኛ ዓመት ግንቦት 4 2010 ዓ.ም. ላይ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓልን ፓፕ ታዎድሮስ 2ኛ ሥርዐተ ቅዳሴውን ራሳቸው በመምራት ያከበሩ ሲኾን እጅግ ብዙዎች ካህናትና የግብጽ ክርስቲያኖች በዓሉን አድምቀውት ነበር፡፡

በመገለጧ ጊዜ የነበረውን ክስተት በዚኽ የ YouTube ሊንክ ይመልከቱ



❖ ጥንት የነበሩት የኢትዮጵያ ሊቃውንት የእመቤታችንን መገለጥ ይጽፉ ነበር፤ አባ ጽጌ ድንግልም አስቀድማ በደብረ ምጥማቅ በታላቅ ክብር ተገልጻ ለምእመናን የታየችው የአምላክ እናት ለርሱም ትገለጽለት ዘንድ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፉ ላይ፡-

“አመ ትበርቂ በደብረ ምጥማቅ ኀምሰ ዕለታተ
ትእምርተ ገጽኪ ይርአይ እስከ ይትነሣእ ዘሞተ
ሚ መጠነ ማርያም ታሥተፌሥሒ ትፍሥሕተ
ኅድጊሰ ጽጌ ፍቅርኪ በጊዜ ንቃሑ መዓልተ
ብፁዕ ዘርእየኪ በሕልሙ ሌሊተ”
(የፊትሽን መልክ ያይ ዘንድ የሞተ ሰው እስኪነሣ ድረስ በደብረ ምጥማቅ ለዐምስት ቀናት ያኽል በተገለጽሽ ጊዜ ማርያም ምን ያኽል ደስ ታሰኚ ኖሯል! በቀን የታየው የፍቅርሽ አበባ ይቅርና ሌሊት በሕልሙ ያየሽ ምስጉን ነው) በማለት ተማፅኗታል፡፡

❖ የእመቤታችን ታማኝ ወዳጅ አባ ጽጌ ድንግል በተመስጦ በመኾን እጅግ ድንቅ የኾነችውን የአምላክን እናት ሥዕል ካየ በኋላ ይኽነን የምስጋና ቃላት ለርሷ ያቀርባል፡-

“ሥዕልኪ ጽግይተ ላሕይ ዘከመዝ ትኤድም በዓለም
እፎ ይሤኒ በሰማይ ላሕየ ገጽኪ ማርያም
ሐሤተ ትእምርትኪ እጽገብ አስተርእዪኒ በሕልም
እስመ አውዐየኒ ነደ ፍቅርኪ ፍሕም
አጥፍኦቶ ዘኢይክል ዝናም”
(ማርያም ሥዕልሽ በዓለም እንዲኽ የምታበራ ከኾነ በሰማይ የፊትሽ መልክ ምን ያምር! አንቺን ከማየት የሚገኘውን ደስታ እጠግብ ዘንድ በሕልም ተገለጪልኝ፤ ዝናብ ሊያጠፋው የማይቻለው የፍቅርሽ እሳት አንድዶኛልና) ብሏል፡፡

❖ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይኽነን መገለጧን በእንዚራ ስብሐት መጽሐፉ ላይ፡-
“ኦ ንግሥት ይገንዩ ለኪ ነገሥት ወለኪ ንግሥታት ይትቀነያ
ወኪያኪ የአኲታ ወለስምኪ ይገንያ
ወለኪ ይሰግዳ ወለክብርኪ የሐልያ
ጢሮስ ወሲዶና ሰብአ ግብጽ ወኢትዮጵያ
ፊንቂ ወሮምያ ማሮን ወአርማንያ
በሥነ ጸዳልኪ ይትፌሥሓ ወበላሕይኪ ይትሐሠያ”

(ንግሥት ሆይ ነገሥታት ለአንቺ ያገለግላሉ፤ ንግሥታትም አንቺን ያመሰግናሉ፤ አንቺንም ያሞግሳሉ፤ ለስምሽም ያጐነብሳሉ፤ ለአንቺ የጸጋ ስግደትን ይሰግዳሉ፤ ለክብርሽም ምስጋናን ያቀርባሉ፡፡ ጢሮስና ሲዶና የግብጽና የኢትዮጵያ ሰዎች፣ ፊንቄና ሮምያ፣ ማሮንና አርማንያ በወጋገንሽ ውበት ደስ ይሰኛሉ፤ በደም ግባትሽም እሰይ ይላሉ) በማለት ገልጦታል፡፡

❖ የመልክአ ማርያም ደራሲም የአምላኩን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን ፊቷን ለማየት ሽቶ በናፍቆት ኾኖ፡-
“ሰላም ለመልክእኪ ዘተሠርገወ አሜረ
ዘያበርህ ወትረ
ፍቅርትየ አንቲ እንተ ታበድሪ ፍቅረ
አርእዪኒ ገጸ ዚኣኪ ማርያም ምዕረ
ዘኢይሰምዖ ካልእ እንግርኪ ነገረ”
(ኹልጊዜ (ዘወትር) የሚያበራ ፀሓይን ጌጥ ላደረገ መልክሽ ሰላምታ ይገባል፤ ፍቅርን የምትመርጪ (የምታስቀድሚ) አንቺ ፍቅረኛዬ ማርያም ሌላ የማይሰማው ነገርን እነግርሽ ዘንድ አንድ ጊዜ ያንቺን ፊት ግለጪልኝ) በማለት ተማፅኗታል፡፡

❖ የአምላክ እናት ሆይ አስቀድመሽ በደብረ ምጥማቅ በኋላም በዘይቱን ማርያም ተገልጠሽ በረከትን እንዳትረፈረፍሽላቸው ዛሬም ለእኛ ለምንወድሽ ለልጆችሽ ትገለጪልን ዘንድ እንማፀንሻለን፡፡ በዓለም ላይ የመጣውን መቅሠፍት ከልጅሽ አማልደሽ አርቂልን እኛ ልጆችሽንም በቃል ኪዳንሽ ጥላ ከጥፋት ሠውሪን።
[ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ]