Get Mystery Box with random crypto!

የኔ እይታ 28 ሲያገኛት ከአባቷ እና ከወንድሟ ውጭ ማንንም ወንድ እወድሀለሁ ብላ የማታውቅ፣ ሲበ | Reyan Records

የኔ እይታ 28

ሲያገኛት ከአባቷ እና ከወንድሟ ውጭ ማንንም ወንድ እወድሀለሁ ብላ የማታውቅ፣ ሲበዛ ሀያዕ የተላበሰች፣ አጅ ነብይ ወንድ "አሰላሙ አለይኩም "ሲላት ወአለይኩም ሰላም" ለማለት የምታፍር፣እድሜዋ ደርሶ አግቢ ስትባል ነውር መስሏት ያለቀሰች፣ ድንገት አንድ ወንድ ጋር አይን ለአይን ስትገጣጠም በሀፍረት ጉንጮ የሚቀላ፣ ቁጥብ ሴት ነበረች.......አንድ ምሽት ስልኮ ላይ የተላከው የፅሁፍ መልዕክት ሂወቷን ቀየረው።ማንም አድንቋት በማያውቀው ልክ በሚያምሩ ቃላት ውበቷን ሲያደንቅ የተለየ ስሜት ተሰማት፣ "እንደኔ ልጅ በዚህ አለም ቆንጆ የት አለ!" እያለ በየጊዜው ከሚፎክረው አባቷ በላይ የእሱ ለስላሳ ቃላት ልቦን አሸፈተው። ለመጀመሪያ ግዜ ባል ቢኖረኝ ብላ ልታሳልፈው ስለምትችለው የሚያምር ሂወት ማሰብ ጀመረች። ከአንድ ግዜ በላይ አጅ ነብይ ወንድ ማየት የሚፈሩ አይኖቿ የላከላትን ፎቶወች ደጋመው አዩ፤ ለመጀመሪያ ግዜ ከወንድሟ ውጭ ወንድ ጋር መፃፃፍ ጀመረች። ይሄኔ ልቧ አላህን እንዳታምፅ እና ወደ መጥፎ መንገድ እንዳታመራ "ተይ አትፃፊለት"ሲላት ነፍስያዋ ደግሞ ሰው ስንት ነገር ያደርጋል አንቺ መፃፃፍን ታካብጂዋለሽ እንዴ?"ትላታለች። ነፍስያዋ አሸንፋ መፃፃፉ አድጎ ግንኙነታቸው ወደ መደዋወል እና ፎቶ ወደ መላላክ ሲያድግ ቀጣዩ እርምጃዋ አላህ ጋር ሊያጣለት እንደሚችል ብታስብም እምቢ የማለት አቅሞን እና የድሮ ሀያዖን ፍቅር የሚሉት ሀይል አሳጣት። በቅርብ ቀን ሊያገባት እንደወሰነ እና ሊመሰርቱት ላሰቡት የትዳር ሂወት ተገናኝተው ማውራት እንዳለባቸው ሲነግራት "አንድ ሴት እና ወንድ ብቻቸውን አይገለሉም ሶስተኛው ሸይጦን ቢሆን እንጂ" የሚለውን የመልክተኛውን ሀዲስ አስታውሳ አላገኝህም ብትልም ከብዙ ንግግር በኋላ ሰው ባለበት እንደሚገናኙ እና ስለሰርጋቸው ብቻ አውርተው እንደሚለያዩ አሳምኗት ተገናኙ። ልቦ በሚያደርገው ነገር ተረብሾ እንዴት ለቤተሰብ አሳውቀው ቶሎ እንደሚጋቡ በተደጋጋሚ ብትጠይቀውም ከዛ ይልቅ ከተጋቡ በኋላ ስለሚያሳልፉት romance ሂወት እጆን ይዞ እያወራ ደስ የማይል ስሜት ውስጥ ሲያስገባት "ዝሙትን አትቅረቡ እርሱ በእርግጥ መጥፎ ስራ ነው እና። መንገዱም ከፋ!"የሚለውን የጌታዋን ቃል አስታዉሳ ከአጠገቡ ተስፈንጥራ ተነሳች። እንዳይከተላት ነግራው ነፍሶን እየወቀሰች ወደ ቤቷ አቀናች። ለወራት አይኖን ጋርዶ የጌታዋን ትዕዛዝ እንዴት ሲያስጥሳት እንደነበር የተፃፃፉትን መልዕክቶች፣የላከችለትን ፎቶወች እያየች ማልቀስ እና እራሷን መውቀስ ጀመረች። እንዴት ነው ያወራሁት?እንዴትስ ነው ጓደኞቼ ስልክ ላይ እንኳን የለሉ ፎቶወቼን ለእሱ የላኩት? አሞኝ ነበር?አቅሌን ስቼ ነበር?እንዴት ይሄን ሁሉ ሳደርግ አላህ ዝም አለኝ? ለቀናት በፀፀት ተገርፋ አላህን በእምባ እየታጠበች እንዲምራት ለመነችው።በተደጋጋሚ መደወሉ አሰልችቷት ከቀናት በኋላ ስልኩን አንስታ ትወቅሰው ጀመር።
"ምን አድርገኸኝ ነው አንድ ሰው አውርቼ የማላቀውን ያን ሁሉ ጊዜ ሳወራህ ፣ስፅፍልህ፣ፎቶ ስልክልህ የነበረው?ምን ብታስነካኝ ነው ላገኝህ ያለህበት የመጣሁት? አላህ ንፁህነቴን አይቶ ከገባሁበት አፀያፊ ነገር ባያወጣኝ ምን ልታደርገኝ ነበር ሀሳብህ? ጨክነህ ከዚህ በላይ ልታቆሽሸኝ ነበር? እኔ እንኳን ባላሳዝንህ አላህን አትፈራም? እውነት ልታገባኝ ነበር ወይስ አቆሽሸህ ልትተወኝ?" ውስጧ የነበረው ፍቅር ሙሉ ለሙሉ በጥላቻ ተገልብጧል።
"ስለምን ንፁህነት ነው የምታወሪው? ንፁህ ሁነሽ አጊኝቼሽ ይሆናል ግን አሁንም ንፁህ ነኝ ብለሽ አትመፃደቂ። ማንንም አውርቼ አላውቅም አንተንም አላወራም አልሽኝ እኔ ግን ሳታወሪኝ እንዳትውይ አደረኩሽ፣ ፎቶሽን ላኪልኝ ስልሽ አልነሳም አልሽኝ እኔ ግን ከመነሳት አልፎ እንድትልኪልኝ አደረኩሽ፣ማንም ነክቶኝ አያውቅም አልሽኝ እኔ ግን እነዛን ንፁህ እጆችሽን ለደቂቃ ያዝኳቸው። የዛን ቀን ክብርሽን ሳታስነኪ ስለሄድሽ ንፁህ ነሽ ማለት አይደለም! አሁን አንቺ አጅ ነብይ የምትይውን ወንድ ያወራሽ በዛ ወንድ ንፁህ የምትይውን ገላ ያስነካሽ ሴት ነሽ! ቆይ እንዴት ያገባኛል ብለሽ አሰብሽ? እኔ የማገባት ሴት አይደለም ወንድ ማግኘት ቀና ብላ የማታይ እንደሆነች አታውቂም?"አላት እራሷን እንድትጠላ አድርጎ እንደሚፈልገው ሊነጅሳት።
"ባንተ የቆሸሸው ልቤ እና እጄ በተውበት ይጠራል። አንተ ግን አላህን ብትፈራ እና ወደ እሱ ብትመለስ ይሻልሀል! ንፁህ ሴቶችን እየነጀሱ ንፁህ ሴትን መመኘት ቂልነት ነው። ጥሩ ሴቶች ለጥሩ ወንዶች እንጂ ለአንተ አይነቱ ወንድ አይገቡም"ብላ ስልኩን ዘጋችው።

የሰወች ንፅህና የሚያስጎመዣቸው፣ ሰወችን መነጀስ የሚያስደስታቸው፣ ብቻቸውን መቆሸሽ የሚጠሉ፣ እነሱ ቆሽሸው ንፁሆችን የሚመኙ ሰወችን አላህ ከዙሪያችን ያርቅል!

rehima hussen

እንደዚህ አይነት ሰወች አጋጥመዋችሁ ያውቁ ይሆን??



ለአስተያየትዎ