Get Mystery Box with random crypto!

ሁሉም በልክ ሲሆን ያምራል ~ ዑለማዎች የተለያዩ ሃሳቦችን ከማንፀባረቃቸው ጋር ሳይወጋገዙ የተላለፉ | Reyan Records

ሁሉም በልክ ሲሆን ያምራል
~
ዑለማዎች የተለያዩ ሃሳቦችን ከማንፀባረቃቸው ጋር ሳይወጋገዙ የተላለፉባቸው የፊቅህ ርእሶች ብዙ ናቸው። በመሰል ጉዳዮች ላይ ሆደ ሰፊ ልንሆን ይገባል። በንዲህ አይነት ርእሶች ላይ መለያየትና መተላለፍ ጥንትም የነበረ ዛሬም ያለ ወደፊትም የሚቀጥል ሐቅ ነው። የተለያዩ ዓሊሞች ቀርቶ አንድ ዓሊም እንኳ በአንድ ርዕስ ላይ የተለያዩ አቋሞችን የሚያንፀባርቅበት ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። ይሄ ብዙ ምሳሌ የመጣበት ጉዳይ ነው።

የዑለማዎችን ትንታኔዎች የሚከተሉ ተማሪዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ፍቅሃዊ አቋሞችን ሊያንፀባርቁ ይችላሉ። ስለሆነም ከስሜታዊ ዝንባሌ እስከተራቀ ድረስ ትላንት "ይፈቀዳል" ያልነውን ጉዳይ ዛሬ "አይፈቀድም" ብንል፣ ዛሬ "ዋጂብ ነው" ያልነውን ነገ "ሙስተሐብ ነው" ብንል የሚያስወቅስም የሚያስገርምም አይደለም። እንዲያውም እንደዚያ ነው መሆን ያለብን። ትላንት ሚዛን የሚደፋ የመሰለን አቋም ከሆነ ጊዜ በኋላ ልክ እንዳልሆነ ከተሰማን "አንዴ ብያለሁ፣ ሰውስ ምን ይለኛል?" አይባልም። ያለ ምንም ማቅማማት ለደረሱበት መረጃ እጅ መስጠት ይገባል። በዚህ መልኩ የሚከሰቱ የአቋም ልዩነቶችን መነሻ አድርጎ ለትችት የሚነሳ ሰው ወይ አላዋቂ ነው። ወይ ደግሞ "በምን ላጥቃ?" እያለ በጉጉት የሚጠብቅ ቂመኛ ነው። አቡ ሐኒፋህ ረሒመሁላህ "እኛ ዛሬ አንድን አቋም እንመርጥና ነገ ከሱ ልንመለስ እንችላለን" ይላሉ።

እንጂ ከስሜት የፀዳ ፍተሻ እስከተደረገ ድረስ በእንዲህ አይነት ሁኔታ የተለያዩ አቋሞችን ማንፀባረቅ የሚወደስ እንጂ የሚወቀስ አይደለም። ባይሆን በውሳኔዎች ላይ ከማስረጃዎች በተቃራኒ ስሜት ወይም ዝንባሌ ዳኛ ሊሆን አይገባም። የፖለቲካ መስመር ይመስል በቡድን መጓዝም አይገባም። በተጨማሪም በጉዳዩ ላይ ያሉ ማስረጃዎች ፍንትው ያሉ መሆናቸው እየታወቀ አጉል መድረቅረቅ ውስጥ መግባትም አያዋጣም። እንዲሁም መለያየት የማይፈቀድባቸውን መሰረታዊ ጉዳዮችን መሬት ላይ ያለውን መለያየት መነሻ በማድረግ ብቻ እያቃለሉ የኢጅቲሃድ ርእስ ማድረግም ራስን ሸውዶ ሌሎችንም ማታለል ነው የሚሆነው።
ስለዚህ በሁሉም አቅጣጫ በልክ መቆም ይገባል። መተላለፍ በሚቻልበት ጉዳይ "እኛን ካልመሰላችሁ!" እያሉ ማስፈራራት፣ ማጠልሸት፣ አንድነትን መበጥበጥ፣ ህብረትን መናድ አይገባም። ይሄ የብስለት መቅለል ነው። በሌላ በኩል መሰረታዊ የዐቂዳ ጉዳዮችን፣ የማያፈናፍኑ መረጃዎችን በመደፍጠጥ በሐቅ ሂሳብ አንድነትን እናሳካለን ማለትም ዘበት ነው። ይሄ ኢስላማዊ ዐቂዳ ልባቸው ውስጥ የቀለለባቸው ደንታ ቢሶች አካሄድ ነው።
=
Ibnu munewor