Get Mystery Box with random crypto!

ደስታ በግድ ማንቁርቱን ይዘህ የምታመጣው አውራ ዶሮ አይደለም። ደስተኛ ለመሆን ጥረት የሚያሳዩ ሰዎ | አርምሞ🧘🏽‍♂️Official ️ ️️

ደስታ በግድ ማንቁርቱን ይዘህ የምታመጣው አውራ ዶሮ አይደለም። ደስተኛ ለመሆን ጥረት የሚያሳዩ ሰዎች ጥንቸል ላይ የከባድ መኪና ጡሩንባ እያንባረቁ ጥንቸሏ ከእቅፋቸው እንድትገባ የሚናፍቁ ናቸው።

ይህን የሚሉት ተመራማሪዎች ደስተኝነት እየራቃቸው የሚሄዱ ሰዎች ደስተኝነትን አብዝተው የሚያስቡቱ ናቸው ሲሉም ደምድመዋል።

የደስታን ጅራት የጨበጠ እጁን ያውጣ

ለብዙዎች ደስታ የምርጫ ጉዳይ ነው። በእነዚህ ሰዎች አስተሳሰብ ደስተኛነት የጥረት ፍሬ ናት። ደስተኛ ለመሆን የፈለገ ልክ በፈተና እጅግ በጣም ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚታትር ተማሪ ቀን ተሌት መልፋት መድከም አለበት።

ጎበዟ ደራሲ ኤልዛቤት ጊልበርት ከዓመታት በፊት ዓለምን አነጋግሮ በነበረውና "Eat, Pray, Love" በተሰኘው የአንድ ወቅት መጽሐፏ ይህን ብላ ነበር፦

"ደስታ የጥረት ውጤት ነው። ትታገላለህ፣ ትሟሟታለህ፣ አንዳንዴም ተነስተህ ፍለጋ ትወጣለህ፤ አገር፣ አህጉር፣ ባሕር ታቋርጣለህ። በረከትህን ለመቀበል ቁጭ ብለህ አይሆንም፤ መቃረም አለብህ። ልክ የደስታን ጅራት ስትጨብጠው እንዳልትለቀው ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። በሐሴት የተነጠፈ የዋና ውሀ ላይ ለመንሳፈፍ የምትችለውን ሁሉ ማድረግ አለብህ፤ አለበለዚያ ትሰጥማለህ።"

እንዲህ ዓይነቱን "ደስታን በባትሪ ፈልጋት" የሚለው ምክር የብዙዎች ቢሆንም አዳዲስ ጥናቶች ግን "ኧረ በፍጹም" ይላሉ። "ፍለጋ ከወጣህ ባዶ እጅህን ትገባለህ፤ እመኑን ደስታ በፍለጋ አትገኝም" ይላሉ።

ከዚያም አልፈው ደስታ ፍለጋ የወጡ ሰዎች ለጭንቀት፣ ለብቸኝነት፣ ለድብታ እና ለውድቀት ነው የሚዳረጉት ብለዋል።

ይህ ጥናት እግረ መንገዱን በየአውዳመቱ ድብታ ውስጥ ስለሚገቡ ሰዎች አዲስ ፍንጭም ሰጥቷል።

በገና፣ በአዲስ ዓመት፣ በኢድ አንዳንዴም በገዛ የልደት ቀናቸው ከባድ የድብርት ቅርቃር ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ደስታን ካልጨበጥናት ሞተን እንገኛለን ስለሚሉ ነው። ደስታን በትግል፤ ቀን ጠብቀው ሊያገኟት...

"ደስተኛ ሁን!" የሚሉ ብሽቅ መጻሕፍት

በካሊፎርኒያ ባርክሌይ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆነችው አይሪስ ማውስ ስለ ደስታና ደስተኝነት ስታጠና እግረ መንገዷን አነቃቂ መጻሕፍትን ታዝባቸዋለች።

ባለፉት ሁለት አሥርታት በአሜሪካ እነዚህ የንሸጣ መጻሕፍት አገሩን አጥለቅልቀውት ነበር። እነዚህ መጻሕፍት አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ስለደስታ ያላቸው ምልከታ ነው። በሕይወት ለመቆየት ደስታን መጎናጸፍ የግድ ነው ይላሉ።

ሁሉንም ስትገልጣቸው "ደስተኛ ካልሆንክማ ለምን ትኖራለህ? እንዴትም ብለህ እራስህን ደስተኛ ማድረግ አለብህ እንጂ" እያሉ አንድ ሁለት ሲሉ አቋራጭ መንገዶችን ይዘረዝራሉ።

በዚህ የተነሳ ጤነኛ ሰው በሰላም እየኖረ ሳለ ልክ እነዚህን መጻሕፍት ሲያነብ 'አሃ! ለካ ሁልጊዜ ደስተኛ መሆን አለብኝ...' ሲል ማሰብ ይጀምራል። እንደውም አሁን ደስተኛ አይደለሁም "በጣም ደስተኛ መሆን ነው ያለብኝ..." ሲል ከራሱ ጋር አዲስ የቅራኔ ውል ይፈራረማል።

ተመራማሪዋ አይሪስ እንደምትለው አንድ ሰው ራሱን "ምን ያህል ደስተኛ ነኝ ግን?" ብሎ የጠየቀ 'ለታ ከደስታ ጋር ፍቺ ፈጽሟል።

ማነው ታዲያ ደስተኛ?

ይህ የነ አይሪስ ጥናት ብዙ ክፍሎች ነበሩት።

ከመሪር ሃዘን በቅርብ የወጡ ሰዎችን ጭምር አካቶ ይዟል። ፊልም እንዲመለከቱ የተደረጉም ነበሩ። ደስተኛ ስለመሆን የሚያወሱ መጻሕፍትን አንብበው የጨረሱ ሰዎችም ዋንኛ የጥናቱ አካል ተደርገዋል።

በሚገርም ሁኔታ ሌሎች ይዘት ያላቸውን ጽሑፎች ካነበቡት በተለየ አነቃቂ መጻሕፍትን ያነበቡት "ደስተኛማ መሆን አለብኝ" በሚል አዲስ መብሰልሰል ውስጥ ገብተው ተገኝተዋል።

እነዚህ ሰዎች መጻሕፍቱን ካገባደዱ በኋላ ስለ ደስታ የነበራቸው ስሜት በመናሩ ያሉበትን ሁኔታና ሕይወታቸውን መንቀፍ ነበር የያዙት።

ይህ ተመሳሳይ ስሜትና ከፍተኛ ደስታን መሻት ሙሽሮች ላይም ተስተውሏል። ለሰርጋቸው ከፍ ያለ ቦታን በመስጠታቸው፤ በሰርጋቸው ማግስት በደስታ ባሕር እንደሚቀዝፉ በማመናቸው ለበለጠ ድብርት ተዳርገው ተገኝተዋል።

ይህ ስሜት ብዙ ሰዎች ያጋጥማቸዋል፤ ውድ የሽርሽር ቦታ አቅደው የሄዱ ሰዎች በማግስቱ ባዶነት ይሰማቸዋል። ነገር ግን በድንገት ወይም ባልተጠበቀና ባልታቀደ ሁኔታ አንድ ቦታ ብትሄዱ ላቅ ያለ ደስታን ልታገኙ ይቻላችኋል።

የባርክሌይ ዩኒቨርስቲ ጥናት ታዲያ "ይህ የሚነግረን ደስታ በቁፋሮ እንደማትገኝ ነው" ይላል።

ለምን ከተባለ ደስታን ስለማግኘት ቀን ተሌት መጣር ስሜታችንን በአላስፈላጊ ደረጃ ማዳመጥን ያስከትልብናል። ስለራሳችን አብዝተን እንድንጠበብ ያደርገናል። አካባቢያችንን ይጋርድብናል። ተፈጥሮን መገንዘብና ማድነቅ እናቆማለን። ሳር ቅጠሉ ሁሉ ስለኛ መሆን እንዳለበት ያሳስበናል።

ሌላው ተመራማሪ ማግሊዮ ከካናዳ አንድ ተጨማሪ ነጥብ አንስቷል።

ፌስቡክን የመሰሉ የማኅበራዊ ትስስር ድረገጾች ላይ የተጠመዱ ሰዎች ደስተኝነታቸው የሚያሽቆለቁለው የሚያዩት ነገር ስለራሳቸው ስለሚነግራቸው ነው። እኔ እንደ እከሌ ደስተኛ መሆን አለብኝ እያሉ ለማሰብ ይገደዳሉ።

ጥናቱ ረዥም ነው። የጥናቱን ውጤት ግን እንዲህ ብሎ መደምደም ይቻላል።

ደስታን ማሳደድ ማለት ያለበረቱ የተገኘ ቀንዳም በሬን እንደማሳደድ ነው።

@rasnflega