Get Mystery Box with random crypto!

ክፍል ሁለት ...... በአጠቃላይ ለስኬት አንዱ ቁልፍ ግብ ማስቀመጥ ሲሆን ግብ ስናስቀምጥም ከ | ቀለማት

ክፍል ሁለት

...... በአጠቃላይ ለስኬት አንዱ ቁልፍ ግብ ማስቀመጥ ሲሆን ግብ ስናስቀምጥም ከላይ የዘረዘርናቸውን 5 ነገሮች ማካተት አለበት፡፡ ግባችን እነዚህን ነገሮች ሲያሟላ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ግባችንን ከማሳካት ጋር ይሆናል፡፡

እነዚህ ማንኛውም ግብ ሊያሟላቸው የሚገቡ ነገሮች ቢሆኑም የበለጠ ስኬታማ ለመሆን ተጨማሪ በግብ ውስጥ መካተት እንዳለባቸውም የተለያዩ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የተወሠኑትን ለመጥቀስ ያህል ግብ በምናስቀምጥት ጊዜ ግባችን ሰፊ መሆን አለበት፡፡ ግባችን በጣም ትንሽ ከሆነች በቁርጠኝነት እንድንሠራ እያደረገንም፡፡ የመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥረን ለመስራት ብናቅድ ይህን እንዳሣካን ባለንበት ቀጥ ብለን ነው የምንቀረው፡፡ ስለዚህ ግባችን ሠፊ መሆን አለበት። ሌላው ግባችን ማካተት ያለበት ነገር ደግሞ ዉጣ ውረድ የሚጠይቅ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ስኬት የዉጣ ውረድ ውጤት ነው፡፡ ነገሮች አልጋ በአልጋ ከሆኑልን ብዙም ውጤታማ አንሆንም፡፡ የተወሳሰቡ ሰራዎችን የሚከተል ግብም ተመራጭ ነው፡፡ ሁሌ ተመሳሳይ የሆነ ነገር ስንሠራ ብዙዎቻችን እንሰለቻለን፡፡ በመሆኑም የበለጠ ስኬታማ ለመሆን ግባችን ውስብስብ ስራዎች የሚፈልግ መሆን አለበት፡፡

ሰዎች ለምን ግብ አያስቀምጡም?

ስኬታማ መሆንን የማይፈልግ ሰው ይኖራል ብሎ ማሠቡ ተገቢ ባይሆንም ግብ የማናስቀምጥ ግን ብዙዎቻችን ነን፡፡ ከስኬት ቁልፎች አንዱ ግብ ማስቀመጥ እደሆነም ከላይ ለማየት ሞክረናል፡፡ ነገር ግን ግብ ሳያስቀምጡ ስኬት “ላም አለኝ በሰማይ” ነው፡፡ ታዲያ ሰዎች ለምን ግብ አያስቀምጡም? ብለን መጠየቅ ያሥፈልገናል፡፡

ግብ ላለማስቀመጥ ዋናው ምክንያት የምንፈልገውን አለማወቅ ነው:: ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን ማወቅ ቀላል መስሎ ሊታየው ይችላል፡፡ ነገር ግን የምንፈልገውን በትክክል ማወቅ እጅግ አስቸጋሪ ነገር ነዉ::ምክንያቱም ፍላጎታችን በየጊዜዉ የሚቀያየር በመሆኑ ነዉ::ለዚህም ነው ያየነው ሁሉ የሚያምረን፡፡ የሚያዝናና ኳስ ስናይ እግር ኳስ ተጨዋች መሆን ያምረናል፣ የኦሊምፒክ ሰሞን ደግሞ ሯጭ መሆን ያምረናል፡፡ ፊልም ስናይ አርቲስት መሆን እንፈልጋለን፣ አንድ የፈጠራ ስራ ስናይ ጥሩ ኢንጂነር መሆን ያምረናል፣ የሲ አይ.ኤ ንና ሞሳድን ዝና ስንሰማ ሰላይ መሆን ይከጅለናል ::የተሳካ ቀዶ ጥገና ስንሰማ ደግሞ ዶክተር መሆን በእጅጉ እንመኛለን:: አሪፍ ህንፃ ስናይ ባለ ሐብት መሆን እንቋምጣለን፡፡ ኧረ ስንቱ…፡፡ ስለዚህ የእኛ ትክክለኛ ፍላጎት የትኛው ነው? ፍላጎታችንን በትክክል ካወቅን ግብ ማስቀመጥ አይከብደንም፡፡

“ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ” እንዲሉ አንድ ወጣት የስኬታማነትን ቁልፍ ለማወቅ ፈልጎ ዝነኛውን የግሪኩ ፈላስፋ ሶቅራጥስን የስኬትን ቁልፍ እንዲነግረው ጠየቀዉ ይባላል፡፡ ሶቅራጥስም ወጣቱን ና እየሄድን እነግርሃለሁ ብሎ በባህር ውስጥ እየተራመዱ መሄድ ጀመሩ ፡፡ እየሄዱ እያለም ሶቅራጥስ ወጣቱን ምን እንደሚፈልግ ዳድም ይጠይቀዋል፡፡ ወጣቱም የስኬት ምስጢርን እንድትነግረኝ ፈልጌ ነው ይለዋል፡፡ ባሕሩ መሀል እንደደረሱ ሶቅራጥስ ወጣቱን አንገቱን ይዞ አሰጠመው፡፡ ወጣቱም አየር ለማግኘት ይፈራገጥ ጀመር፡፡ ሶቅራጥስ ግን ሊለቀው አልቻለም፡፡ ወጣቱም ኧረ እባክህ ልቀቀኝ ልትገለኝ ነው እያለ ቢጮህም ሶቅራጥስ አለቀቀውም፡፡ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ሶቅራጥስ ወጣቱን ከውሃው አወጣውና ለምን ይፈራገጥ እንደነበርና እንዲለቀው የጠቀበትን ምክንያት ይጠይቀዋል፡፡ ወጣቱም አየር ፈልጌ ነዉ ይለዋል፡፡ሶቅራጥስም ወጣቱን “አየህ አየር እንደሚያስፈልግሀ ስታውቅ እንደዚህ ከተፈረገጥክ ስኬታማ መሆን ከፈለግህም መጀመሪያ ምን እንደምትፈልግ እወቅ” ብሎ መለሰለት ይባላል፡፡

ስለዚህም ወደ እንቅስቃሴና ትጋት የምንገባው ውስጣችን እንድናገኘዉ የሚፈልገዉን ነገር ማወቅ ስንችል ነው፡፡ ማንኛውም ስኬታማ መሆን የሚፈልግ ሰው በመጀመሪያ ፍላጐቱን ማወቅ ግድ ይለዋል፡፡ ነገሩን ስናጠቃልለው ሰዎች ግብ የማያስቀምጡበት ዋነኛው ምክንያት ፍላጐታቸውን ማወቅ አለመቻላቸው ነው፡፡ ግብ ከማስከመጣችን በፊት ፍላጐታችንን ጠንቅቀን ማወቅ ታላቅ የቤት ሥራ ይሆናል፡፡

2. የውስጥ መነሳሳት (Motivation)

ግብ ስላስቀመጥን ብቻ ስኬታማ እንሆናለን ማለት አይደለም፡፡ ግባችንን ለማሳካት ያላሰለሰ ጥረት ያስፈልገናል፡፡ በመሆኑም ሁለተኛው የስኬት ቁልፍ ውስጣዊ መነሳሳትን መፍጠር ነው፡፡ ይህን ውስጣዊ መነሳሳታችንን ለማምጣት ደግሞ ያቀድነውን እቅድ በተለያዩና ሊታዩን በሚችሉ ቦታዎች ማስቀመጥ ይመከራል፡፡ ያስቀመጥነው ግብ ሁልጊዜ ስናየው የበለጠ ለመስራት እንነሳሳለን፡፡ ሌላው ውስጣችንን ለማነሳሳት ልንጠቀምበት የምንችለው ነገር ግባችንን ካሳካን በኋላ ልናገኘው የምንችለውን ስሜት በማሰብ ነው፡፡ ግቤን ሳሳከ ምን አያለሁ፣ ምን እሰማለሁ፣ ምንአይነት ስሜት ይሰማኛል የሚሉትን ጥያቄዎች ሁል ጊዜ በማንሳት ውስጣዊ መነሳሳትን ልናመጣ እንችላለን፡፡

3. ፅናት (persistence)

ስኬት ጽናት ለሌላቸዉ ጀርበዋን የምትሰጥ ወይዘሮ ናት፡፡ከእያንዳንዱ ስኬታማ ሰዉ በስተጀርባ ጽናት ይኖራል፡፡ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆነዉለት ስኬታማ የሆነ ማግኜት ይከብዳል፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት ያህልም ሁለት ዋሽንት የሚነፉ ሰዎች ነበሩ ይባላል፡፡አንደኛዉ ሲነፋ ሁሌም ዝናብ ይዘንባል ፡፡ሌላኛዉ ሲነፋ ግን አይዘንብም፡፡ዋሽንት ሲነፋ ዝናብ በሚዘንብለት ሰዉ የሚያዩት ሁሉ ይገረሙበታል፡፡ ሁለቱም ግን ተመልካች አላቸዉ፡፡ከእለታት በአንድ ቀን ዋሽንት ሲነፋ ዝናብ የማይዘንብለትን የሚመለከቱት ሰዎች ሲነፋ የሚዘንብለትን የሚመለከቱትን ሰዎች ዋሽንት ሊያሰሙዋቸዉ ጋበዙዋቸዉ፡፡ተጋባዦችም ዋሽንቱን ከሰሙ በሁዋላ ለጋበዙዋቸዉ ሰዎች እነርሱም በተራቸዉ ዋሽንት ሲነፋ ዝናብ የሚዘንብለትን ሰዉ ያዩት ዘንድ ጋበዙዋቸዉ:: ተጋባዦች ሲያዩ ሰዉዬዉ ሲነፋ ከቆየ በሁዋላ ዝናብ ይዘንብ ጀመር:: በጣም ተገረሙ ::ዋሽንት የሚነፋዉንም ሰዉየ እርሱ ሲነፋ ለምን ዝናብ እንደሚዘንብ ይነግራቸዉ ዘንድ ጠየቁት::ሰዉዬዉም "አይ እኔ ስነፋ አይደለም ዝናብ የሚዘንበዉ ነገር ግን ዝናብ እስከሚዘንብ ነዉ የምነፋዉ"ብሎ መለሰላቸዉ ይባላል::አዎ እኛም ያቀድነዉ እስከሚዘንብልን ድረስ መጽናት ያስፈልገናል:: ይህ ካልሆነ ግን ስኬትን ማምጣት ከባድ ነዉ:: በመጨረሻም
CHANGE YOUR WAY BUT NOT YOUR GOAL" ብዬ ላብቃ።
መልካም የስኬት ጊዜ!!!

Via unknown source

ቀለማት - ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ መድመቂያ ቀለም አለው።

Join us @qelemaat/@qelemaat