Get Mystery Box with random crypto!

“አዲስ ዓመት” አዲስ እኔ”ነት ነው! (New year is the philosophy of self op | ናሁሰናይ ፀዳሉ አበራ 🤷‍♂

“አዲስ ዓመት” አዲስ እኔ”ነት ነው!
(New year is the philosophy of self optimism)
(እ.ብ.ይ.)

ሰው ሁልጊዜ አዲስ ይሆን ዘንድ እንዲችል አዲስ ዓመትን ፈጠረ፡፡ ሰው ከራሱ ጋር ይታረቅ ዘንድ፣ እቅዱ ከግቡ እንዲስማማ፤ ውጫዊና ውስጣዊ ሕይወቱ እንዲጣጣም አዲስ ዓመት ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ የአዲስ ዓመት አፈጣጠሩም ሰው ለራሱ ቀና ለመሆን ከመነጨ ውስጣዊ ጉጉቱ ነው፡፡ የዛሬው ሰውም ለራሱ እንኳ ቀና መሆንን ባልቻለበት የእድሜ ዘመኑ አንዲቷ ቀን አዲስ ዓመት ትሆነው ዘንድና ለራሱና ለወገኑ መልካምና ቅን ያስብባት ዘንድ አባቶቹና ቅድመ አያቶቹ አዲስ አመትን ሰሩለት፡፡

አዲስ ዓመት የሰው ልጅ ራሱን የሚያሻሽልበት፣ ያለፈውን ሕይወቱን ገምግሞ ደካማውን ሽሮ ጠንካራውን ይዞ እንዲቀጥልበት ለራሱ የፈጠረው የቀን ቀጠሮ ነው፡፡ ተፈጥሯዊ ቀኑ ያው ከሌላው ቀን የተለየ አይደለም፡፡ እንደማንኛውም ቀን ይነጋል፤ እንደማናኝውም ምሽት ይመሻል፡፡ ነገር ግን ለቀኑ ስያሜ በመስጠት በቀኑ አማካኝነት ራስን መለወጥ፣ አስተሳሰብን ማደስ፣ አኗኗርን ማስተካከል ማሰብ ማሰላሰል በሚችለው በሰው ልጅ ታሪክ የተለመደ ወግ ነው፡፡ ምክንያት ፈልጎ ወይም ፈጥሮ አንድ ነገር ማድረግ ሰው የሰለጠነበት ልማዱ ነው፡፡ ዛሬም እንደጥንቱ በሰሜናዊው የሃገራችን ክፍል ሰው አይደለም ለደስታው ቀርቶ ለሐዘኑም ጭምር ደረቱን ለመድቃት፣ ፊቱን ለመንጨት እንኳ ቀድሞ የተረዳውን/የሰማውን የወዳጁን ወይም የዘመዱን ሞት እርሙን ለማውጣት ሲል ቀን ቀጥሮ ከዘመድ አዝማዱ ጋር ተሰባስቦ በቀጠሮ ለቅሶ ሐዘን ይቀመጣል፡፡ አዲስ ዓመትም አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ዕቅድ፣ ከበፊቱ የተለየ የሕይወት መንገድ የሚጀመርበት የቀን ቀጠሮ ነው፡፡

አዎ አዲስ አመት ሰው ለራሱ ቀና የሚያስብበት፣ አዲስ ቃል የሚገባት ዕለቱ ነው፡፡ ይሄ ቀን ደግሞ መጪው ጊዜ መልካም እንዲሆን፤ ኑሮው እንዲሳካ፣ ጎጆው እንዲሞላ፣ መንፈሱ እንዲረካ፣ አዕምሮው እንዲሰላ፣ ነፍስያው እንዲጠግብ፣ የውስጡም የውጪውም ሕይወቱ እንዲያምር ሀ ብሎ ስራ የሚጀምርበት ዕለት ነው፡፡ በርግጥ ብዙዎቻችን አዲስ ዓመትን ከአለባበስ፣ ከመብልና ከመጠጥ ጋር ብቻ የምናያይዝ ነን፤ እንዲሁም ከወዳጅ ዘመድ ጋር ተገናኝቶ ለመጫወት ብቻ ቀኑን የምናሳልፍ ጥቂት አይደለንም፡፡ ከቤተሰብ ጋር ሆኖ አምሮና ደምቆ በፍቅርና በደስታ አዲስ ዓመትን ማሳለፍ የሚያስደስት ቢሆንም እውነተኛ የአዲስ ዓመት ትርጉሙ ግን አዲስ ሰውነት፣ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ለውጥ፣ አዲስ የሕይወት መንገድ የምናበጅበት፣ ለራሳችን ቀና አስተሳሰብ የምንቀይስበት ዕለት ነው፡፡

የስቶይክ ፍልስፍና አራማጆች እንደሚመክሩት የሰው ልጅ ጭንቀቱና ትኩረቱ መሆን ያለበት መቆጣጠር በማይችላቸው በውጫዊ ኩነቶች ሳይሆን በቀላሉ ሊያስተዳድራቸው በሚችላቸው በውስጣዊ ሕይወቱ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ የሰውነት ጓዳ ጎድጓዳውን ሳይሞላ ቤቱን በቁስ የሚሞላ ሰው የአዕምሮ ድሃ ነው፡፡ ሕይወቱን ለመብላት ብቻ የሚያኖራት እውነተኛ ደስታ የለውም፡፡ ሆድን ከመሙላት በላይ አዕምሮን በማጥገብ ነው የሕይወት እርካታ የሚገኘው፡፡ የሰው ልጅ በእንጀራ ብቻ አይኖርም እንዲል ቅዱስ ቃሉ፡፡

ሰው ለአዲስ ዓመት አዲስ እቅድ ሲያዘጋጅ ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ብሎ ሳይሆን ገንዘብ እንዴት መስራትና በምን አግባብ ሐብት ማከማቸት እንደሚችል የሚያውቅ ጭንቅላት መፍጠር እንዳለበትም ጭምር ካልሆነ እቅዱ ትርጉም አይሰጥም፡፡ ገንዘቡ ግንዛቤ ከሌለው አደጋ ነው፡፡ አዲስ ዓመት በቁስ ሃብታም የመሆን ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ አዲስ ዓመት በአዲስ አስተሳሰብ የመንፈስ ባለፀጋ የዕውቀት ባለሐብት ለመሆን እቅድ ካልተያዘበት ዋጋ የለውም፡፡ ሰውነትን የማያበለጽግ እቅድ ግቡን ቢመታም ህይወትን አስደሳች አያደርግም፡፡

ወዳጄ ሆይ..... የአዲስ ዓመት ፍልስፍናህን ገምግመው፡፡ አንተ ራስህን ለመለወጥ ቆርጠህ ካልተነሳህ አዲስ ዓመት አንተን አይለውጥህም፤ ቀኑ በራሱ ጥንትም ማንንም ለውጦ አያወቅም፤ ወደፊትም አይለውጥም፡፡ አዲስነት በሃሳብ መለየት ብቻ ሳይሆን በግንዛቤ መበልጸግ፣ በጥበብ መጎልመስ፣ ራስን በመቆጣጠር መርቀቅም ጭምር መሆኑን ተረዳ፡፡ አዲስነት የትናንቱን ድካም፤ ያለፈውን አጉል ልማድ መድገም ሳይሆን አዲሱን ኑሮ በአዲስ ሰውነት፣ በሰለጠነ አስተሳሰብና በቀናነት መጀመር ነው፡፡ አዎ! አዲስ ዓመት ከአዙሪት ሕይወትህ ነጻ የምትወጣበት፤ ከአጉል ልማድ እስርህ ሐርነት የምታገኝበት የነፃነት ቀንህ ነው፡፡ አዲስ ዓመት ለራስህ፣ ለወገንህ፣ ለሐገርህ ቅን አስበህ በጎውን የምትከውንበት የስራ ዘመንህም ነው፡፡ አዲሱ ዓመት ሰላም የሞላበት፣ ፍቅር የበዛበት ይሆን ዘንድ ከራስህ ጋር ውል የምትፈፅምበት የቃልኪዳን ዕለትህም ጭምር ነው፡፡ አዲሱን ዓመት በአዲስ ሰውነት ካልተቀበልከው አዲሱ ዓመትህ ያረጃል፣ አንተም በአዲስ ዓመት ከበርቻቻ ትርጉም ታጣለህ፡፡

አዲስ ዓመት የአዲስ ሕይወት ጅማሮ፤ የቀናነት አስተሳሰብ የመጀመሪያው ክፍለጊዜ ነው፡፡

መልካም አዲስ ዓመት!

ቸር ዘመን!

____
እሸቱ ብሩ
@Psychoet