Get Mystery Box with random crypto!

ጥቁር ነጥብ፤ ======== የአንድ ትንሽ ከተማ የንግድ ምክር ቤት ዓመታዊ የእራት ግብዣ ላይ አ | Tona Media | ቶና ሚዲያ

ጥቁር ነጥብ፤
========

የአንድ ትንሽ ከተማ የንግድ ምክር ቤት ዓመታዊ የእራት ግብዣ ላይ አንዲትን አነቃቂ ተናጋሪ ጋበዘ። ምክንያቱም የማህበረቡ ኢኮኖሚ አሽቆልቁሎ፣ ሰዎቹም ተስፋ ቆርጠው ነበርና እንዲበረታቱና እንዲነቃቁ ለማስቻል ነበር።

ተናጋሪዋም ንግግሯን ስትጀምር በአንድ ትልቅ ነጭ ወረቀት መሀል ላይ ትንሽ ጥቁር ነጥብ በመሳል ነበር። ከዚያም በተሰበሰቡት ሰዎች ፊት ለፊት ከፍ አድርጋ በመያዝ ምን እንደታያቸው መጠየቅ ጀመረች።

አንዱ ሰው ፈጠን ብሎ "ጥቁር ነጥብ" አለ።

"እሺ ሌላስ" አለች ተናጋሪዋ።

ሁሉም በአንድ ላይ : "ጥቁር ነጥብ" አሉ።

"ከጥቁሩ ነጥብ ሌላ ምንም ነገር አልታያችሁም?" ብላ ደግማ ጠየቀቻቸው።

ተሰብሳቢዎቹም በአንድ ድምጽ : "ምንም" በማለት መለሱ።

"ትልቁ ነጭ ወረቀትስ?" በማለት ጠየቀች ተናጋሪዋ። "እርግጠኛ ነኝ ሁላችሁም አይታችሁታል" አለች። "ነገር ግን እሱን ትታችሁ ላዩ ላይ ያለውን ነገር ማየትን መረጣችሁ።"

"በሕይወታችንም ያሉንን እና በአካባቢያችን የሚከሰቱ አስገራሚ ነገሮችን በመተው ጥቃቅንና ነጥብ የሚመስሉ እንዲሁም የማይረቡ ነገሮች ላይ በማተኮር ጊዚያችንን እናባክናለን። 'ችግሮች' ብለን የምንጠራቸው ነገሮች በአብዛኛው ልክ ነጩ ወረቀት ላይ እንዳለው ጥቁር ነጥብ ናቸው። እይታችንን ካሰፋን እና ሙሉ ሥዕሉን ማየት ከቻልን ትናንሽና የማይረቡ ሆነው እናገኛቸዋለን።" በማለት ንግግሯን አጠቃለለች።

እርስዎስ ጉልበትዎንና ትኩረትዎን ነጥብ መሰል ችግሮች ላይ ከሚያደርጉ ሰዎች ተርታ የሚሰለፉ ነዎት? ወይስ ትልቁን ወረቀት በማየት ችግሮችን አሳንሰው አሸናፊ የሚሆኑ ነዎት?

ሳይክ አዲስ