Get Mystery Box with random crypto!

ሽንቁር በድቅድቅ ጨለማ በጥቁር ሰማይ ስር ብርሀን ምታስገባ አለች አንዲት ሽንቁር | የግጥም አለም

ሽንቁር
በድቅድቅ ጨለማ በጥቁር ሰማይ ስር
ብርሀን ምታስገባ አለች አንዲት ሽንቁር
በደምፀ(አቡጊዳ)

በታመቀ ምድር በእኔነት መንፈስ እጅግ ለተጎዳ
የኛነትን ንፋስ የሚያናፍስልን አለ አንድ ቀዳዳ
እረግ እረግ
ታፍነን የለም ወይ በእኔነት ማዕረግ
ማዕረግ ነው
ማዕረግ ነው ግድ የለም አንዲህ ሚያላቅሰን
ሠይጣን ያሣከለን ከሠውነት አንሠን
ቁጥቋጦ ያረገን ከዋርካነት ንዶን
ብቻዬን ለግሌ ሚያስብለን አባዜ
ሠውነትን ሚያስክድ የሠይጣን ኑዛዜ
አብረን ቁጭ ብለናል
የስልካችን ብርሀን ፊታችን ላይ በርቷል
ውስጣችን ጨልሟል
ወርቃችንን ትተን መዳብን ፍለጋ እሩቅ ተጉዘናል
ታድያ ከዚህ ወዲያ ማዕረግ ኬት ይገኛል
በሠይጣኒዝም ኮርስ ማስትሬት ይዘናል
ግን
ግን ደግሞ ይነጋል አይቀርም ጨልሞ
የጦቢያ ፋኖስ ልባችን ላይ ከትሞ
በድቅድቅ ጨለማ በጥቁር ሰማይ ስር
ብርሀን ምታስገባ አለች አንዲት ሽንቁር
ሽንቁር ናት ለሌው ኢምንት ምናምቴ
ከአድማስ ትሰፋለች ለኔና ለአያቴ
ሽንቁር ናት ለነሱ ሽንቁር ናት ለነዚያ
ለኔ ግን ምሉዕ ነች የንጋትን ጮራ የብርሀን ማያ
ጨለማ ይሏታል ጥቁሮች ይሉናል
አዎ እኛ ጥቁር ነን ሁሉንም ችለናል
ነጭማ ነጭ ነው ቶሎ ይመነችካል
ካንድ ቀን ባሻገር መች ተለብሶ ያውቃል
ጥቁሮች ነን እኛ ጨለማ ናት አሷ
ልብሳችን ቡቱቱ ቤታችን ደሳሳ
አርግጥ ነው አንክድም ሽንቁር ናት ለአለም
የብርሀን መግቢያ ከዚች ሽንቁር ውጪ ሌላ መንገድ የለም
ሽንቁር ነሽ ኢትዮጵያ ሽንቁር እናት አለም
የተሸነቆርሽው አርጅተሽ አይደለም
እንኳን ተሸነቆርሽ እንኳን ቀዳዳ ሆንሽ
የኛነትን መንፈስ ታናፍሽኛለሽ
በድቅድቅ ጨለማ በጥቁር ሰማይ ስር
ብርሀን ምታስገባ አለች አንዲት ሽንቁር
በታመቀ ምድር በእኔነት መንፈስ እጅግ ለተጎዳ
የኛነትን ንፋስ የሚያናፍስልን አለ አንድ ቀዳዳ