Get Mystery Box with random crypto!

'በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን' ሰኔ ፴ (30) | Orthodox picture

"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"

ሰኔ ፴ (30) ቀን።

እንኳን ለነቢዩ ለሰማዕቱ ለካህኑ ለሐዋርያው ለመጥምቀ መለኮት ለተወለደበት (ለልደት) በዓልና በሕንደኬ ካሉ ደሴቶቸ በአንዲቱ ውስጥ ለሚኖር ለገድለኛ ለሆነ ለአባ ጌራን ለዕረፍት መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከቅዱሳን ማርያና፣ ከማርታ፣ ከመነኰስ ገብረ ክርስቶስ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

+ + +
የዕለቱ አንገርጋሪ ግእዝ ዜማ፦ ሃሌ ሉያ "ሰምዑ አዝማዲሃ ወሰብአ ቤታ። እስመ አዕበየ እግዚአብሔር ሣህሎ ላዕሌሃ። ወተፈሥሁ ፍሥሃ ፈድፋደ። ወፈቀዱ ይስምይዎ በስመ አቡሁ ዘካርያስ። ወትቤ እሙ ዮሐንስሃ ይሰመይ"። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ላይ።

+ + +
ነቢይ፣ ሰማዕትና ሐዋርያ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ልደት፦ ይህም በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ ለእግዚአብሔር ልጅ የሰገደው ነው። ይህም በመድኅን ክርስቶስ ራስ ላይ እጁን ጭኖ በውኃ ያጠምቀው ዘንድ የተገባው ነው።

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተነገረ ወንድ ልጅን ትወልድ ዘንድ የኤልሳቤጥ የፅንሷ ወራት በተፈጸመ ጊዜ ወንድ ልጅን ወለደች። ዘመዶቿና ጎረቤቶቿ እግዚአብሔር ቸርነቱን እንዳበዛላት በሰሙ ጊዜ ስለርስዋ ደስ አላቸው። በስምንተኛውም ቀን ሊገዝሩት መጡ በአባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ጠሩት። እናቱ ግን "አይሆንም ዮሐንስ ይባል" አለች። "ከዘመዶችሽ ስሙ እንዲህ የሚባል የለም" አሏት።

አባቱንም ጠቅሰው "ማን ሊባል ትወዳለህ" አሉት። እርሱም ብራና ለምኖ ስሙ "ዮሐንስ ይባል" ብሎ ጻፈ። ሁሉም አደነቁ። ያን ጊዜም አንደበቱ ከድዳነት ተፈትቶለት ተናገረ እግዚአብሔርንም ፈጽሞ አመሰገነው። ስለ ልጁና ስለ መድኃኒታችን መምጣት ልጁ ዮሐንስም የልዑል ነቢይ እንደሚባልና በእግዚአብሔርም ፊት እንደሚሔድ ትንቢት ተናገረ።

ሰብአ ሰገልም መጥተው ከሔዱ በኋላ ሄሮድስ ሕፃናትን በገደላቸው ጊዜ ስለ ሕፃናትን በገደላቸው ጊዜ ስለ ሕፃኑ ዮሐንስ ለሄሮድስ ነገሩት እንዲገድሉትም ጭፍሮችን ላከ ጭፍሮችም ወደ አባቱ ዘካርያስ መጡ ሕፃኑንም ከእርሱ ፈለጉት አባቱም አንሥቶ በትከሻዎቹ ተሸክሞ ወደ ቤተ መቅደስ ከእርሱ ጋራ እንዲሔዱና ሕፃኑን ከዚያ እንዲወስዱት ወታደሮችን ለመናቸው።

ከዚህም በኋላ ሕፃኑን በመሠዊያው ጠርዝ ላይ አኖረውና "ከዚህ ራሳችሁ ተቀብላችሁ ውሰዱት" አላቸው ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መልአክ ነጥቆ ወደ በረሀ ወሰደው። ጭፍሮችም ባላገኙት ጊዜ አባቱ ዘካርያስን ገደሉት። ሕፃኑ ግን አድጎ ለእስራኤል እስከተገለጠበት ጊዜ ድረስ በበረሀ ውስጥ ኖረ።

"የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ የዐዋጅ ነጋሪ ድምጽ እነሆ" ብሎ ኢያሳያስ የተናገረለት ይህ ነው። ሚልክያስም ስለርሱ እንዲህ አለ "በፊትህ ጎዳናዬን አስተካክሎ የሚጠርግ መልአክተኛዬን እኔ እሰዳለሁ"።

ራሱ መድኃኒታችንም ስርሱ ሲናገር "ሴቶች ከወለዱአቸው መጥምቁ ዮሐንስን የሚበልጠው የለም" ብሏል። ይህ የእግዚአብሔር ልጅ በአጠመቀውና የማትዳሠሥ ራሱን በዳሠሠው ጊዜ "የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት" የሚል የአብን ቃል ሰምቷልና።

ዳግመኛም ክብር ይግባውና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ራስ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ሲቀመጥ አየ። እኛንም መድኃኒታችን እንዲምረንና ይቅር እንዲለን በአማላጅነቱ እያመን መታሰቢያውን እናድርግ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ በረከቱም እኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

+ + +
ገድለኛው የሆነ አባ ጌራን፦ ይህም ቅዱስ በሕንደኬ ካሉ ደሴቶች በአንዲቱ ውስጥ የሚኖር ነው። እርሱም እግዚአብሔርን የሚፈራና የሚወደው ጾምና ጸሎትንም የሚወድ ነበር። ወደ እግዚአብሔርም የሚለምነውን ሁሉ ይሰማው ነበር። በጸሎቱም ከዚያች አገር ንዳድ፣ አባር፣ ድርቅ፣ በጠላት መማረክ፣ የደም መፍሰስና የመርከቦች መሥጠም ተወገደ የፈለገውንም ሁሉ በጸሎቱ ያገኝ ነበር።

ሰይጣንም ስለዚህ ስለ ተሰጠው ጸጋ ቀናበት በዕንቊ ያጌጠ ነገሥታትን ልብስ በለበሰች መልከ መልካም ሴት አምሳልም ታየው እርሷም ብቻዋን ትንጎራደድ ነበር። በአያትም ጊዜ ወደርሷ ሒዶ ሥራዋን ጠየቃት እርሷም እንዲህ አለችው "የንጉሥ ሰርስባን ልጅ ነኝ እኅቴ ከአባቷ ባሮች ጋራ በአመነዘረች ጊዜ ሁላችንንም ሊገድለን ፈለገ። ስለዚህ ፈርቼ በሌሊት ወጣሁ ወደዚች በረሀም መጣሁ ቅዱሱን ሰው አንተን በማግኘቴም እድለኛ ነኝ" አለችው። እርሱም "ወደ እኔ የሚመጡ ሰዎች እንዳያዩሽ ወደዚያች የዐለት ዋሻ ሒጂ" አላት።

በሌሊትም ከአራዊት የተነሣ እንደፈራ ሰው እየጮኸች መጥታ "የዱር አራዊት እንዳይበሉኝ ክፈትልኝ" አለችው። እርሱም ከፈተላትና ገባች በጎኑም ተኝታ ደረቱን አቀፈችው ልቡን ወደ ፍቅርዋ እስከ አዘነበለችው ድረስ ነገሯን አለሰለሰችለት። ያን ጊዜ ያደረበት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተለየው ከእርሷም ጋራ ተኝቶ ኃጢአት እደሚሠራ ሆነ። ከስህተት ስካርም በነቃ ጊዜ በጠላት ሰይጣን ተንኰል ተሸንፎ እንደ በደለ አወቀ።

ከዚህም በኋላ ከሰይጣን ተንኰል የተነሣ ያገኘውን ሁሉ በሥጋውም ኃጢአት እንደሠራ ጻፈ። ከዚህ በኋላም ከደሴቱ ተራራ ድንጊያ አንሥቶ እስከሚሞት ድረስ ራሱንና ደረቱን እየደበደበ ኖረ። ነፍሱም ድና ወደ ዘላለም ሕይወት በጌታ ቸርነት ገባች።

ከዚህም በኋላ እንደ ልማዳቸው ከእርሱ ቡራኬ ሊቀበሉ ሰዎች መጥተው አላገኙትም በፈለጉትም ጊዜ ተኝቶ አገኙትና ያንቀላፋ መስሏቸው ጀምሩ ግን ሞቶ አገኙት አለቀሱለት ተሳለሙት ገንዘውም ቀበሩት።

ከዚህም በኋላ ሞቱ በጠላት ሰይጣን ተንኮል ምክንያት ስለመሆኑ የጻፈውን አገኙ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ጻድቃንና ሰማዕታት ጸሎት መንፈሳውያን በሆኑ በቅዱሳን መላእክትም አማላጅነት ይልቁንም አምላክን በወለደች በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጸሎቷና በአማላጅነቷ ከሰይጣን ወጥመድ ያድነን።

የተባረ የሰኔ ወር በእግዚአብሔር ቸርነት ተፈጸመ አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ 30ስንክሳር።


+ + +
"ሰላም ለዮሐንስ ግፋዕ ወቅቱል ንጹሕ ወቅዱስ ወስቡሕ ላእክ ወነቢይ ወሰማዕት ድንግል ካህን ጸያሒ ወሰባኪ መጥምቀ እግዚኡ"። ትርጉም፦ ጌታውን ያጠመቀና ሰባኪ፤ መንገድ ጠራጊ፣ ካህን ድንግል ሰማዕት፣ ነቢይና አገልጋይ፤ ምስጉን ቅዱስና ንጹሕ፤ ተገፍቶ የተገደለ ለኾነ ለቅዱስ ዮሐንስ ሰላምታ ይገባል። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።


+ + +
የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ "አሜሃ ይቤሉ አሕዛብ። አዕበየ ገቢረ ሎሙ እግዚአብሔር። ወኮነ ፍሡሓነ። መዝ 125፥2፥3። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥76-ፍ.ም።