Get Mystery Box with random crypto!

ኢቮሊውሽን - ፪ (Dec. 19, 2019 የተጻፈ) ዛሬ ደግሞ የምንመለከተው የምድርን ረጅም ዕ | ምስባከ ጳውሎስ (Paul's Pulpit)

ኢቮሊውሽን - ፪

(Dec. 19, 2019 የተጻፈ)

ዛሬ ደግሞ የምንመለከተው የምድርን ረጅም ዕድሜ የሚቀበለውን ክርስቲያናዊ አስተሳሰብ ነው፤ Old Earth creationism ተብሎ ይታወቃል። በዚህ ንድፈ ሐሳብ መሠረት የምድር ዕድሜ ሳይንሱም እንደሚለው በሚሊዮንና በቢሊዮን ዓመታት ሊቆጠር ይችላል። ከዚህ የተነሣ፣ በዚህ ጎራ ውስጥ ያሉ ወገኖች ፊዚክስን፣ ኬሚስትሪን፣ ጂኦሎጂን በሚመሳስሉ ጉዳዮች ከሳይንስ ጋር ዝምድና እንጂ ጠብ የላቸውም። ከሳይንስ ጋር ልዩነታቸው ያለው የሳይንስን ባዮሎጂ ነክ ትንታኔ፤ አዝጋሚ ለውጥን ባለመቀበል ነው። የዚህ ሐሳብ አቀንቃኞች ምድር ረጅም ዕድሜ እንዳላት ቢቀበሉም ወደዚህ መረዳት የደረሱባቸው የተለያዩ መንገዶች አሏቸው። አንድ ሁለቱን ዛሬ መመልከት እንችላለን።

የመጀመሪያዎቹ Gap theory ተብሎ የሚታወቀውን ንድፈ ሐሳብ ይቀበላሉ። ይኸውም በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ቁጥር 1 እና 2 መካከል እጅግ ረጅም የሆነ የዘመናት ክፍተት መኖሩን የሚያስብ ነው። በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን መፍጠሩን ዘፍጥረት 1፥1 ይናገራል። የሚቀጥለው ቁጥር ግን ምድር ባዶ፣ ጨለማና አንዳችም ያልነበረባት መሆኑን በማስረዳት ይቀጥላል። እግዚአብሔር ግን ባዶና ጨለማ ምድርን አይደለም የፈጠረው። ምድር ምሉዕ ነበረች። እግዚአብሔር አሟልቶ ፈጥሯት በሰላም ለብዙ ዘመናት እየኖረች ሳለ፣ ከተፈጠሩት ኪሩቦች መካከል አንዱ በእግዚአብሔር ላይ ዓመፀና ከነግብረ አበሮቹ ወደ ታች ተወረወረ።

ይህ ኪሩብ፣ ማለትም ሰይጣን ከሰማይ ወደ ምድር ሲጣል ብዙ ምስቅልቅል ተከስቷል። በዚህም ምድር ተናግታለች፤ በላይዋ የነበረው ሁሉ አደጋ ደርሶበታል። ስለዚህ ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ቁጥር 2 “ምድርም ባዶ ነበረች፤ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ” የሚለው ይህንኑ ነው። ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር በሰይጣን ዓመፅ የተበለሻሸችውን ምድር እንደገና ሊያበጃጃትና ሊያስካክላት ሥራ ጀመረ። በዚህ ጎራ ያሉ ሰዎች በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ቁጥር 1 እና ቁጥር 2 መካከል በሚሊዮን (ወይም በቢሊዮን) የሚቆጠሩ ዓመታት መኖሩን ስለሚያሰቡ በምድር ዕድሜ ጉዳይ ከሳይንስ ጋር ይስማማሉ።

ሌለኞቹ ደግሞ እግዚአብሔር ፍጥረቱን በፈጠረባቸው ስድስት ቀናት ትርጓሜ ላይ ያተኩራሉ። በዚህ ጎራ ሐተታ መሠረት በዘፍጥረት 1 ላይ “ቀን” የተባለው አሁን እንደምናውቀውን 24 ሰዓት ተደርጎ መታሰብ የለበትም። ቀን የሚለው የዕብራይስጥ ቃል "ዮም" ብዙ ዘመናትንም ሊወክል ይችላል። ለምሳሌ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “የጌታ ቀን ይመጣል” እያለ ስለ መጨረሻው ቀን ሲናገር፣ 24 ሰዓት ስላለው ቀን እያመለከተ አይደለም። (እኛም ብንሆን “ቀን ወጣለት፣ ቀን መጣ፣ ቀን ይመጣል” እያልን ስንናገር 24 ሰዓትን እያሰብን አይደለም።) ስለዚህ በዘፍጥረት 1 ላይ እግዚአብሔር ፍጥረታትን የፈጠረባቸው ቀናት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዓመታት ሊሆኑ ይችላሉ።

ኧረ እንዲያውም ምድራዊ ቀናት ላይሆኑም ይችላሉ፤ cosmic time እንጂ። (ፀሓይ ሳትፈጠርም ጭምር ቀናት ሲቆጠሩ እንደ ነበር ልብ ይሏል።) የጊዜ አቆጣጠሩ የዚህ ዓለም ካልሆነ ደግሞ አንዱ ቀን ለእኛ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዓመታት ሊሆን ይችላል። በእነዚህ ሚሊዮን ዓመታት ውስጥ እግዚአብሔር እየመጣ፣ አስቀድሞ በፈጠረው ፍጥረት ላይ አንዳች ነገር እያከለ ማለትም እያበጃጀው ይሄዳል። ፍጥረት የተፈጠረው በዚህ መልኩ ቀስ በቀስ፣ ለውጥ እየተካሄደበት ነው። አሁን ያለው ነገር በሂደት የተበጃጀ እንጂ ከመጀመሪያው እንደዚሁ አይደለም የተፈጠረው። ስለዚህ እዚህኛው ውስጥ ያሉቱ እንደ ላይኞቹ በጂኦሎጂ፣ በፊዚክስና በኬሚስትሪ ብቻ ሳይሆን፣ በተወሰነ መልኩ ከባዮሎጂም ጋር ከሳይንስ ጋር ስምሙ ናቸው።

የምድርን ረጅም ዕድሜ የሚቀበሉቱ ክርስቲያኖች አዝጋሚ ለውጥን በሚመለከት micro evolution ይቀበላሉ እንጂ macro evolutionን አይቀበሉም። micro evolution በአንድ የፍጥረት ቤተሰብ (species) ውስጥ ብቻ የሚካሄድን ለውጥ ይመለከታል። ለምሳሌ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አዳምና ሔዋን ቢሆኑም፣ ቀስ በቀስ ጥቁር፣ ነጭ፣ ቀይ፣ ቡኒ ተብሎ የሚታወቅ የሰው ዘር መጥቷል፤ በሚኖሩባቸው ውስጣዊና ከባቢያዊ ሁኔታዎች ምክንያት። ይህም የሰውን ቁመት፣ የቆዳ ቀለም፣ የአፍንጫንና የከንፈርን ቅርጽ፣ የጠጉርን ዐይነት፣ ወዘተ. የለወጠ ሂደት ነው። አለዚያማ አፍሪካዊ፣ አረባዊ፣ ቻይናዊ፣ ሕንዳዊ፣ ላቲናዊ፣ ምዕራባዊ፣ እስያዊ … የሚባሉ መልኮች ከየት መጡ? በአዝጋሚ ለውጥ አይደለምን? ልክ እንደዚሁ ዐይነት ለውጦች በእንስሳትም ሆነ በተክሎች መካከል ተከስተዋል። ሁሉም ለውጦች ግን በአንድ የፍጥረት ቤተሰብ (species) ውስጥ ብቻ የተገደቡ ናቸው። ከአንድ ቤተ ሰብ ወደ ሌላኛው የተካሄደ ለውጥ የለም። እናም ከእንስሳ በአዝጋሚ ለውጥ ሰው ወደ መሆን ለውጥ አልተካሄደም። እናም እነዚህኞቹ በማይክሮ ኢቮሊውሽን ካልሆነ በቀር በማክሮ ኢቮሊውሽን ከሳይንስ ጋር አይስማሙም።

(በነገራችን ላይ የዘፍጥረት አንዱ “ቀን” 24 ሰዓት ላይሆን እንደሚችል ጥያቄ መነሣት የጀመረው ዛሬ አይደለም፤ በ4ኛው እና በ5ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው የቤተ ክርስቲያን አባት ቅዱስ አውግስጢኖስም (St. Augustine) ይህንኑ ብሎ ነበር።)

የአገራችንን ክርስቲያኖችን በሚመለከት በዘፍጥረት 1፥1 እና 1፥2 መካከል ረጅም ዕድሜ መኖሩን የሚያምኑ በጣም ጥቂት ክርስቲያኖችን ዐውቃለሁ፤ የዘፍጥረት 1 ቀን 24 ሰዓት ላይሆን እንደሚችል የሚቀበሉም እጅግ በጣም ጥቂት ሰዎች አውቃለሁ። በስብከትም ሆነ በጽሑፍ ይህንኑ ለመግለጽ የደፈረ ግን አላጋጠመኝም።

እያየን እንጨምራለን።

https://t.me/PaulosFekadu