Get Mystery Box with random crypto!

በአንድ ወቅት አንድ ጋቭሮብ ይቸገርና ብር ለመበደር ወደ ሌላኛው ጋቭሮብ ጓደኛው ቤት በምሽት ያመራ | Our World

በአንድ ወቅት አንድ ጋቭሮብ ይቸገርና ብር ለመበደር ወደ ሌላኛው ጋቭሮብ ጓደኛው ቤት በምሽት ያመራል። እሳት ዳር ቁጭ ብለው እያወጉም የገጠመውን ችግር ለጓደኛው ያወያየውና ለስራ መጀመሪያ የሚሆነውን የተወሰነ ብር እንዲያበድረው ይጠይቀዋል። ጓደኛውም በሀዘኔታ የተባለውን ብር ቆጥሮ ይሰጠውና የጓደኝነት የእሳት ዳር ወጋቸውን ቀጠሉ። በመሐል ግን ፡ ብር የተበደረው ጋቭሮብ ከአንደኛው ኪሱ ውስጥ ሲጃራ ያወጣል ፣ ከሌላኛው ኪሱ ውስጥም ክብሪት ያወጣና ሲጃራውን ለኩሶ ማጨስ ይጀምራል። በዚህን ጊዜም ፡ አበዳሪው ጋቭሮብ "እስኪ ቅድም የሰጠሁክን ብር አንዴ ስጠኝ። በትክክል የቆጠርኩት አልመሰልኝምና ደግሜ ልቁጠረው!" በማለት ጓደኛውን ጠየቀው። ተበዳሪው ጋቭሮብም ምንም ሳያመነታ ብሩን አውጥቶ ድጋሚ ይቆጥረው ዘንድ ለአበዳሪው ጓደኛው ሰጠው። አበዳሪው ጋቭሮብም ብሩን በእጁ ካስገባ በኋላ ፡ ተበዳሪ ጓደኛውን "ጓደኛዬ ሆይ! ፊት ለፊትህ ይህን የመሠለ ቦግ ብሎ የነደደ እሳት እያለልህ ፡ ሲጃራህን ለመለኮስ አንዲት ክብሪትን በመጫር ያባከንክ ሰው ፡ ነገ ነግደህ ያበደርኩህን ብር ትመልሳለህ ብዬ ስለማላስብ ማበደሬን ትቼዋለሁኝ!" አለውና እሳቱ አጠገብ ቁጭ ያለውን ተበዳሪ ጓደኛውን ጥሎት ወደ ቤቱ ገባ!

ትንሽ ቀልድ መሳይ ታሪክ ናት። በውስጧ ግን ትልቅ አስተምህሮን አዝላለች።
ሰዎች ከአፋችን በሚወጡ ትናንሽ ቃላቶች ጭምር ማንነታችንን ይዳኛሉ። በምንተገብራት ትንሽ ተግባርም ብትሆን ሰለ ማንነታችን ይገምታሉ። ልክ በትልቅ ድስት የተሰራን ወጥ ፡ ጠብታውን ብቻ በመቅመስ "ወጡ ጨው አለው ወይም አንሶታል ፣ ወጡ ይጣፍጣል ወይም አይጣፍጥም... ወዘተ" እያልን የትልቁን ድስት ወጥን እንደምንዳኘው ሁሉ ማለት ነው። ሰዎችም ከውስጣችን በወጣች ትንሽ ቃልን በመስማትና ፡ ከልባችን የተገበርነው ትንሽ ተግባርን በመመልከት ማንነታችንን ይዳኛሉ!

በእለት ተእለት የምንተገብራቸው ትናንሽ ተግባሮችና የምናወራቸው ትናንሽ ቃላቶች የማንነታችን መገለጫ ናቸውና እራሳችንን ለመፈተሽ ይጠቅሙናል!