Get Mystery Box with random crypto!

ኢንተርኔትን መሰረት ያደረጉ የማጭበርበርና የማታለል ድርጊቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ መምጣታቸውን | Our World

ኢንተርኔትን መሰረት ያደረጉ የማጭበርበርና የማታለል ድርጊቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ መምጣታቸውን በቅርቡ የወጡ ጥናቶች አሳይተዋል። ለምሳሌ ከሳምንት በፊት ‘PIXM’ የተባለ የሳይበር ደህንነት ተቋም ያወጣው የጥናት ሪፖርት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 8.5 ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የማጭበርበርና የማታለል ድርጊቶች ሰለባ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።

አብዛኛዎቹ የማጭበርበር ድርጊቶች የተፈጸሙት በፌስቡክ ሜሴንጀር በሚደረጉት የማግባባት ሽንገላዎችና በሚላኩ ማስፈንጠሪያዎች (links) አማካኝነት መሆኑንም ጥናቱ አስነብቧል።

በርከት ያሉ የኢት የማጭበርበርና የማታለል ሙከራ ሊደረገባቸው እንደሆነ ሲጠረጥሩ የድርጊቱን ፈጻሚዎች የላኩላቸውን ማስፈንጠሪያ በማያያዝ እንድናጣራላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄዎች ያቀርቡልናል።

ለማጭበርበርና ለማታለል የሚላኩ ማስፈንጠሪያዎችን ደህንነትና ታማኝነት በሁለት መንገዶች ማጣራት ይቻላል። የመጀመሪያው ማስፈንጠሪያውን በሚገባ ማስተዋል ነው። በዚህም በማስፈጠሪያው ላይ የተጻፉትን ቃላት፣ ቁጥሮች እንዲሁም ምልክቶች ስለ ድረ-ገጹ ደህንነትና ታማኝነት ፍንጭ ሊሰጡን ስለሚችሉ በሚገባ ማስተዋል ይጠበቅብናል።

ሌላኛው የማስፈንጠሪያውን ደህንነትና ታማኝነት የሚያጣሩ መገልገያዎችን መጠቀም ነው። ጎግል ትራንስፓረንሲ ሪፖርት (Google Transparency Report)፣ ኖርቶን ሴፍ ዌብ (Norton Safe Web) እና ፊሽታንክ (PhishTank) ማስፈንጠሪያዎችን ለማጣራት ከሚረዱ መገልገያዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

1. Google Transparency Report: ይህ በጎግል አማካኝነት የቀረበ መገልገያ አጠራጣሪ ማስፈንጠሪያዎችን ለማጣራት ያግዛል። በመገልገያው ለመጠቀም የ Google Transparency Report ድረ-ገጽን ይክፈቱ፤ ከዚያም የማስፈንጠሪያውን URL በመፈልጊያ ቦታው ላይ ያስገቡና ‘Search’ የሚለውን ይጫኑ። ከሰከንዶች በኃላ ስለማስፈንጠሪያው ተዓማኝነት ጎግል መረጃ ይሰጥወታል። https://transparencyreport.google.com/safe-browsing/search?hl=en

2. Norton Safe Web: ይህ መገልገያ የማስፈንጠሪያዎችን ደህንነት እንዲሁም ታማኝነት ለማወቅ ይረዳል። በመገልገያው ለመጠቀም የNorton Safe Web ድረገጽን ይክፈቱ፤ ከዚያም የማስፈንጠሪያውን URL በመፈልጊያ ቦታው ላይ ያስገቡና ‘Search’ የሚለውን ይጫኑ። ከቆይታ በኃላ መገልገያው የማስፈንጠሪያውን ደህንነትና ተዓማኝነት መርምሮ ደረጃውን ይነግርዎታል። በተጨማሪም ሌሎች የማስፈንጠሪያው ተጠቃሚዎች የሰጡትን ምስክርነት ያስነብብዎታል። https://safeweb.norton.com/

3. PhishTank: ይህ መገልገያ ማስፈንጠሪያዎች ወደ አጭበርባሪዎችና አታላዮች ማምራት ወይም አለማምራታቸውን ለማጣራት ይረዳል። በመገልገያው ለመጠቀም የ PhishTank ድረገጽን ይክፈቱ፤ ከዚያም የማስፈንጠሪያውን URL በመፈልጊያ ቦታው ላይ ያስገቡና ‘Search’ የሚለውን ይጫኑ። በውጤቱም ያስገቡት ማስፈንጠሪያ ወደ አጭበርባሪዎች የሚወስድ ስለመሆኑ መረጃ ያገኛሉ። https://www.phishtank.com/

በኢሜል፣ በቴሌሌግራም፣ በዋትስአፕ፣ በሜሴንጀር እና በሌሎች ኢንተርኔትን መሰረት ባደረጉ መገናኛ ዘዴዎች የሚደርሱን አጠራጣሪ ማስፈንጠሪያዎች ለአጭበርባሪዎች፣ ለአታላዮች እንዲሁም ለመረጃ መንታፊዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ክሊክ ከማድረጋችን በፊት ስለደህንነታቸውና ታማኝነታቸው እናጣራ።