Get Mystery Box with random crypto!

ቅዱስ ሲኖዶስ ሠራኤ ሕግ ወፈጻሜ ሕግ የሆነውን ጌታቸውን የተከተሉ፣ ሙጽአ ሕግ የሆነችውን ቅድስት | ኦርቶዶክስ ተዋህዶን እንወቅ

ቅዱስ ሲኖዶስ ሠራኤ ሕግ ወፈጻሜ ሕግ የሆነውን ጌታቸውን የተከተሉ፣ ሙጽአ ሕግ የሆነችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተልእኮ በሕገ እግዚአብሔር በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈጽሙ አባቶች ስብስብ እንደሆነ አምናለሁ፣ አውቃለሁም።

ለዚህም ነው በዘወትር ጸሎታችን ያለውን እንደ ሁሉም ክርስቲያኖች ሁሉ ዕለት ዕለት “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት” ብለው ያስተማሩኝን የማምነው፣ የምመሰክረው፣ የምጸልየውም።

ቤተ ክርስቲያን ከጉባኤያት ፣ ከምክር ቤቶች፣ ከስብሰባዎች ሁሉ በላይ የሆነችውም በተፈጥሮዋም፣ በአሠራሯም፣ በሂደቷም ከሁሉም በላይ በሆነው በጌታዋ በቤዛዋ በመድኃኒቷ እንዲህ ጸንታ የምትኖር ስለሆነች እና መሆንም ስላለባት እንደሆነ አውቃለሁ፣ አምናለሁም።

አንዳንድ ሰዎች ዘመን ሰጠን፣ ጉልበት አገኘን ብለው ይህን አስትተው እንደ ጎሣ ምክር ቤት፣ እንደ ፌዴሪሽን ምክር ቤት፣ እንደ ወንድማማቾች እድር፣ እንደ ተወላጆች ማኅበር፣ እንደ መሳሰሉት ቅርጽ እና መልክ ይዛ እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ መሆኗ ቀርቶ እንተ ታህ
ሕተ ኩሉ መንግሥታት፣ ፓርቲያት ፣ ብሔር ወጎሣ ወመማክርት እንድትሆን የሚፈልጉትን ሁሉ ነፍሴ አጥብቃ ትጸየፋለች፣ በሚቻለኝም ሁሉ እንደ አባቶቼ ይህን እቃወመዋለሁ። እንዲህ እንዲሆን የሚመኝ የሚሠራ ካለም ክርስቶስን ረዳቴ እና ጌታየ አድርጌ ቅዱስ ጴጥሮስ ሲሞንን እንደረገመው እረግመዋለሁ፣ ከኅብረቱ እንደለየውም ቢያንስ ራሴን ከእንዲህ ያለው እለያለሁ።

የእኔ ጥያቄ ለሲኖዶስ፦

እኔ ቅዱስ ሲኖዶስን የምጠይቀው የመብት ጥያቄ የለኝም። ቅዱስ ሲኖዶስ የታዛዦች የአገልጋዮች ጉባኤ እንጂ የባላ ሥልጣናት ምክር ቤት አይደለምና።
እኔ ቅዱስ ሲኖዶስን የምጠይቀው የአካባቢ፣ የጎሳ፣ የቋንቋ፣ ... የመሳሰሉት የውክልና ጥያቄም የለኝም። የሰማያውያን የመላእክት ወንድሞች የሆኑ ይህን ዐለም የካዱ አባቶች ጉባኤ ነውና። ቅዱስ ሲኖዶስን የምጠይቀው የእገሌ ይሾም የእገሌ አይሾም ጥያቄም የለኝም። ጥያቂዬ የሕግ እና የሥርዓት እንጂ የመብት እና የፖለቲካ አይደለምና።

ቅዱስ ሲኖዶስ አማኞች እንደ ፓርቲ ያቋቋሙት በፈለጉ ጊዜ ሕጉን ቀይረው ዘመን የወለደውን ንጉሥ የወደደውን አስመስለው የሚሠሩት ተራ ተቋም እንዳልሆነ ስማር ኖሪያለሁ፣ በዐለም ባሉት ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያን ሁሉም እንዲህ እንዳልሆነ አውቃለሁ፣ አያለሁምና ምንም ዐይነት የመብት ጥያቄ የለኝም። የመብት ጥያቄ ያለው ክርስቲያን ሆኖ ሊኖር የሚችልም የለምና።

የእኔ ጥያቄ መዳኑ በቤተ ክርስቲያን ሊፈጸምለት እንደሚሻ አንድ ኃጢአተኛ እና ደካማ ሲኖዶሴ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያኔም ቤተ ክርስቲያን ሆና ማየት ብቻ ነው። ቤተ ክርስቲያንን መገለጫዋን ቅዱስ ሲኖዶስን በሌላው እንዳደረጉት ኢትዮጵያን ይምሰል በሚል ሽፋን ምክር ቤት ይምስል፣ የጎሳ ውክልና ምጥጥን ስሌት ይጠቀም የሚሉትን የምቃወመው ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን እንድትሆን የልጅነት ድምፄን፣ ክርስቲያናዊ ግዴታዬን ለመወጣት ብቻ ነው።

መብት በሚል አደገኛ የፖለቲካ ቃል በር አስከፍቶ ሲኖዶስን የጎሳ ምክር ቤት፣ ቤተ ክርስቲያንም የድኅነት ቤት የፍጥረት ሁሉ መጠጊያ ሐመረ ኖኅ መሆኗን አስጥሎ ጥቅመ ሰናዖር፣ ሐይመተ ፈርዖን ሆና እንድትቆጠር እና ራሷ ከሆነው ከጌታ ከክርስቶስ ከብልቶቿ ከንጹሐን ምእመናን ለመለየት የሚደረገውን ጥረት የምቃወመው ሊቀርብ የሚገባው ጥያቄ የሕግ እና የሥርዓት እንጂ የመብት እና የፖለቲካ አይደለም ብዬ ስለማምን ነው።

ባለፈው ጊዜ በሻሸመኔ እና በተለያዩ አካባቢዎች የተገደሉ፣ አካላቸው የጎደለ፣ የታሠሩ የተገርፉ እና አሁንም የሚታሠሩ፣ ቤተ ክርስቲያናቸው እስካሁን የተዘጋባቸው፣ በአዲስ አበባ እንኳ ከሥራቸው ተፈናቅለው በደስታ የተቀበሉት ጥያቄያቸው የድኅነት የሕግ የሥርዓት ይከበር ጥያቄ ስለሆነ እንጂ የመብትማ ቢሆን እንዲህ አይሆንም ነበር። እነዚህ ሁሉ ጥያቄያቸው ቤተ ክርስቲያናቸውን ከወንበዴዎች፣ በጎቹንም ከተኩላ ጠብቃችሁ አድኑን የሚል ትሑት እና የመጨረሻ አነሥተኛ ጥያቄ ነው። የእኔም ጥያቄ ድኅነት ፈለገው የመጡ ምእመናን የጌታን ደም በቁርባን ሰጥተው በማዳን ፈንታ የምእመናን ደም ላፈሰሱ፣ በልተው ላልጠገቡ ለተራቡ ተኩላዎች ሰጥታችሁ አታስበሉን፣ ይልቁንም ድኅነታቸውን ሽተው ለሚያድኑን እረኞች አብቁን የሚል ብቻ ነው።

ይህ ካልሆነ ሲኖዶሱ ሲኖዶስ አይደለም ያሰኝና ብዙዎችን ሊያስወጣ፣ ምእመናን ሊከፋፍል፣ ... ሌላም ሌላም ችግር ሊያስከትል ስለሚችል የእነዚያ ሰዎች የድኅነት ጥያቄ የእኔም ልባዊ ጥያቄ ነው።

አባቶቼ የምታመልኩት የምታገለግሉት፣ እኔም ኃጢአተኛው እና ደካማው የማመልከው ላገለግለውም የምመኘው ሕያው እግዚአብሔር በሚያውቀው ጥያቄዬ አንድ እና አንድ ብቻ ነው።

ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳትም ሆነ ማንኛውም ነገር በሕግ እና በሥርዓት ፣ ቀኖናውን መሠረት ባደረገ ለማንም በማያዘነብል፣ ለምእመናን ድኅነት እና ለቤተ ክርስቲያን እድገት እንጂ ለፓርቲዎችና እና ለፖለቲከኞች መሣሪያ ባልሆነ ግልጽ እና ሁሉም ሊያውቀው በሚችል በሲኖዶስ በጸደቀ የምርጫ መመሪያ እና ባለማድላት በተመሰከረላቸው አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሲፈጸም ሕግ ሥርዓት ሲተገበር የማየት የልጅነት ጥያቄ ብቻ ነው።

በእኛ ዘመን ለምን ሕግ ይወጣል? ቀኖናስ ለምን ይጠበቃል የሚል ድምጽ ለሚሰሙት እንዴት ይረብሻል በእውነት። ይህ ድምፅ ይሰማል የሚል እምነት ባይኖረኝም መረበሹን አለመናገር ግን ድምፃቸውን እንደ አማራጭ ማስቆጠር መስሎ ስለተሰማኝ ከፊል የተስማማሁ ስለመሰለኝ ነው ያነሣሁት እንጂ ይደረጋል ብዬ አላስብም።

ጥያቄዬ ቅዱስ ሲኖዶስ በዓላማው በክብሩ ጸንቶ እንዲኖር ቅዱስ ጳውሎስ የሚያውኳችሁ ይቆረጡ እንዳለው ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ለመጣል እና ቤተ ክርስቲያንን ለማወክ ያሰፈሰፉ ሁሉ በሕግ ተቆርጠው እንዲወድቁ ብቻ ነው።

ጥያቄዬ ቤተ ክርስቲያንን ተሳታፊዎች የሚዘውሯት ተራ ምድራዊ ተቋም ሳትሆን ሰማያዊ መልኳን ይዛ እንድትጸና ሕግ ሥርዓቷ ይከበር የሚል ብቻ ነው።

ጥያቄዬ አሳሳቾች በሚፈጽሙት ችግር ምእመናን እንዳይረበሹ ለድኅነታቸውም መሰናክል እንዳይበዛ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይከበር የሚል የልጅነት ጥያቄ ብቻ ነው።

ይህን መጠየቅ ካልቻልኩማ ምኑን ልጇ ሆንኩት፣ ስማረው የኖሩክትስ ምን ይጠቅመኛል። ለድኅነት ካልሆነስ ምን ይረዳኛል። ቤተ ክርስቲያኔ ቤተ ክርስቲያን ካልሆነችስ ምን ይጠቅመኛል። ፓርቲማ መች ቸገረኝ፣ ሕግ ጥሰት እና ድፈረትማ በዓለም ሁሉ ሞልቶ የለ። ከዚህ ሁሉ የጥፋት ባሕር ቀዝፋ የምታሽግር መርከቤን ሽንቁረው ውኃውን አስገብትው አብረን እናስጥምህ ሲሉኝ ዝም ካልኩኝማ ምኑን ሰው ሆንኩ? የተርሴስ ተጓዦች የተጨነቁትን ያህል ካልተጨነቅሁ ምን እጠቅማለሁ? እነሱ እንዳደረጉት ለመርከቢቱ የከበደውን ነገር ባላውቀው እንኳ ሸክም ካልቀነስኩ ምን ረባሁ? የተኛውን ካልቀሰቀስኩ ወደ አምላክህ ጩህ ካላልኩ ከእነዚያ ተጓዦች የማንስ እጅግ ምስኪን አልሆንምን? ስለዚህ የእኔ ጥያቄ የድኅነት እንጂ የመብት ጥያቄ አይደለም። የመብት ጠያቂዎችንም መስማት አልፈልግም። እርሱ ለፖለቲካ ፣ ለድርጅት፣ ለዚህ ዓለም ሰው ሰራሽ ተቋም እንጂ እግዚአብሔር ለመሠረታት፣ ፍጽምት እና አለነውር እንድትሆን ላደረጋት ቤተ ክርስቲያን የመብት ጥያቄ የለኝም፣ ሊኖረኝም አይችልም። የእኔ ጥያቄ እንተ ላዕኩሉን እንተ ታሕተ ኩሉ ሊያደርጉ የመጡትን በሕግ በሥርዓት ቆርጣችሁ፣ መርከባችን ከሚያናውጥ ማዕበል ቀዝፋችሁ አድኑን የሚል የድኅነት የሕግ የሥርዓት