Get Mystery Box with random crypto!

የምናከብራችሁ አባቶቻቸን ሆይ ያስተማሯችሁ መምህራን ተዋክበውና ታስረው ከእናንተ ደጅ የማይደርስ ይ | ኦርቶዶክስ ተዋህዶን እንወቅ

የምናከብራችሁ አባቶቻቸን ሆይ ያስተማሯችሁ መምህራን ተዋክበውና ታስረው ከእናንተ ደጅ የማይደርስ ይመስላችኋልን?

የእናንተን ባናውቅም እኛ ግን እነሱን ባሰብን ጊዜ ሂደንም ባየን ጊዜ ልባችን ይደማል!

የኔታ ብላችሁ ቀለም ቀስማችሁ የእግዚአብሔርን ቃል የተማራችሁባቸው ጉባኤ ቤቶች ተዘግተዋል።

እነዛ ተቀምጣችሁ የቤተ ክርስቲያንን ጣእም የቀመሳችሁባቸው ወንበሮች ታጥፈዋል።

እነዚህ ጎጆዎች ያልፈረሱት በእነሱ የእግዚአብሔር አገልግሎት ቀናኢነት ነው።

አብነት መምህራኑ ግን የድርሻችንን እንወጣ አሉ እንጂ ወደ እናንተ አልቀሰሩም። በጉባኤ በር እንኳ ሳያልፉ ነገር ግን በከተማ በቅንጡ ቤት በሚኖሩት እና ዘመናዊ መኪና ከያዙ አገልጋዮች ራሳቸውን አነጻጽረው አልታገዝንም እና እንበተን አላሉም።

 ዛሬም የተራበና የተጠማ የተማሪ ፊት እያዩ በሰቀቀን ያስተምራሉ።

 እየራባቸው እየቸገራቸው ጉባኤ ዘርግተው በእግዚአብሔር ቃል ይበረታሉ።

ይህን ሁሉ ዋጋ የሚከፍሉት የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ እንዳይቋረጥ ነው።

የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲቀጥል ከተፈለገ አብነት ትምህርት ቤት መምህራንን መጠበቅ መብት ሳይሆን ግዴታ ነው።

ቤተ ክርስቲያን ለጉባኤ ቤት መምህራን ጥበቃና ከለላ ማደረግ ያለባት ለማንም ብላ ሳይሆን ለሕልውናዋ ስትል ነው።

ምእመናን አባቶቹን እንደዐይኑ መጠበቅ ያለበት ደስ ስለሚለው አይደለም እግዚአብሔር የሚያይባቸው ዐይኖቹ የሆኑ ካህናትን የሚያፈሩ ስለሆኑ ነው።

እናም የመምህር ኃይለማርያም ዘውዱ ጉዳይ ሊገዳችሁ ይገባል። አንድ የጉባኤ ሊቅ እንዴት ባለቤት አይኖረውም?

እንደእናንት "በእንተ ስማ ለማርያም" ብለው ከውሻ ተጋፍተው ተምረዋል።

ገጠር ከተማ ሳይሉ ጉባኤ ዘርግተው ሊቃውንትን ሰጥተውናል።

በዚህ 2 ቀናት እንኳ ስንት ጉባኤ ታጠፈ? እሳቸውን የሚጠብቁ ስንት ምእመናን አንገት ደፉ?

ቢያንስ ምን ማድረግ ባትችሉ ያሉበትን ሁኔታ ከሚመለከታቸው ጠይቃችሁ ካለጥፋት ከሆነ በሕግ አምላክ በሉልን! ያልተረዳነው ካለም ለምእመናን አስረዱን!

ዛሬ በዝምታ ያለፋችሁት እውነት ነገ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን አለማንኳኳት አይችልም! ለመምህሩ የመጣ ለተማሪው አለመድረስ አይችልምና!

ሌላው ቢቀር ለምእመናን ስነ ልቦና ስትሉ ዋኖቻችንን ጠብቁልን!

ቤተ ክርስቲያን ችግር ባጋጠማት ጊዜ በልጅነታችሁ ከጎኗ የነበራችሁ የሕግ ባለሙያች ከእግዚአብሔር ጋር ከእናንተ ብዙ እንጠብቃለን! ከሊቁ ጎን ቁሙልን!

መስከረም ጌታቸው

http://t.me/ortodoxtewahedo