Get Mystery Box with random crypto!

#የሰንበትን_ቀን_ትቀድሰው_ዘንድ_አስብ ‹‹ስድስት ቀን ስራ፣ተግባርህም ሁሉ አድርግ በሰባተኛው ቀ | ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች

#የሰንበትን_ቀን_ትቀድሰው_ዘንድ_አስብ

‹‹ስድስት ቀን ስራ፣ተግባርህም ሁሉ አድርግ በሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው፡፡እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን አርፏልና ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታል፡፡ ›› (ዘጸ 20፡10-11)

#ሰንበት_ማለት_ምን_ማለት_ነው ?

ሰንበት ማለት አቆመ፣አረፈ ማለት ነው፡፡ይህ ቀን የጌታ ዕረፍት የተባረከም ቀን ነው፡፡ከማንኛውም ሥጋዊ ሥራ ተቆጥበን የእግዚአብሔርን ውለታ የምናስብበት ቀን ነው፡፡ ሰው እረፍት ያስፈልገዋል፡፡ የሰንበት ቀንም የተፈጠረው ለዚህ ነው፡፡ (ዘዳ 5፡14)፣(ማር 2፡38)
ከሳምንቱ ሰባት ቀናት መካከል ለእረፍት የተቀደሰው የተባረከው ዕለት ሰንበት ብቻ ነው፡፡ ስለሌሎች ቀናት የተነገረው ‹‹ ያ መልካም እንደሆነ አየ››የተባለው ብቻ ነው፡፡ ሰንበትን ግን ባርኮታል ቀድሶታል፡፡ (ዘፍ 1፡12፣ 18፡20፣ 25፡31)

በሐዲስ ኪዳን ለክርስቲያን ሁለት ሰንበት አለ ቀዳሚት ሰንበት(ቅዳሜ) እና ሰንበተ ክርስቲያን(እሑድ)
ቀዳሚት ሰንበት (ቅዳሜ)
ጌታ ያረፈባት ለእስራኤል ዘሥጋ የታዘዘው ሰንበት ነው፡፡ ይህ ቀን እስራኤላውያንን እግዚአብሔር አምላክ ከግብፅ ባርነት ወደ እረፍት እንዳወጣቸው ያመለክታል፡፡ዘዳ5-2-16 በእግዚአብሔር እና በህዝቡ መካከል ምልክት ነበረ ሰንበትን አለማክበር ግን ከባድ ቅጣት ያስከትል ነበር፡፡ (ዘጸ 3፡17) ፣ (ሕዝ 20፡12) ፣ (ዘኁ 15፡32-36)
ፈሪሳውያን በነበራቸው የተሳሳተ አመለካከት በሰንበት ቀን እንኳን መልካም ሥራን አይሰሩም ነበር፡፡ስለዚህም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተወቅሰዋል፡፡ (ማቴ 12፡14) ፣ (ሉቃ 4፡16)

#ሰንበተ_ክርስቲያን_(እሑድ)

ይህች ቀን ለሳምንቱ መጀመሪያ፣ጌታችን ሥነ ፍጥረትን መፍጠር የጀመረበት ጌታ የተነሣበት፣መንፈስ ቅዱስ የወረደበት እንዲሁም ጌታችን ዳግመኛ በክብር የሚመጣበት ዕለት ስለሆነ ሰንበተ ክርስቲያን እንለዋለን፡፡ በሰንበተ ክርስቲያን (በጌታ ቀን) የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ልዩ ትኩረት በመስጠት ይሰባሰቡ ነበር፡፡ (ሐዋ 20፡7) ፣ገንዘብ ያዋጡበት ነበር (1ኛቆሮ 16፡2) ፣ በሥርዓተ ዓምልኮ የሚተጉበት፣የጌታችን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሚቀበሉበት ዕለት ነበር፡፡ (ዮሐ 20፡1-24) ፣ (ሐዋ 2፡11-14)

በቤተክርስቲያን ታሪክ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዕለተ እሑድ የክርስቲያኖች ሰንበት ናት በማለት ሥራ እንዳይሰራባት አዋጅ አስነግሮ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ይህቺ ዕለት በሐዲስ ኪዳን መከበር የጀመረ ቢሆንም በብሉይ ኪዳን ከፋሲካ በፊት የሰንበት (የቀዳሚት) ማግስት በመባል በኩራት እና ቀዳሚያት የሚያቀርቡበት ቀን ነበር፡፡ (ራዕ 1፡10)

በቀዳሚት ሰንበት ቅዱስ እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ አርፎ ሥጋዊ እረፍትን ለሰው እንዳስተማረ በዚህች ቀን (በሰንበተ ክርስቲያን) በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት የተገኘውን የዘላለማዊ የነፍስ ዕረፍት የምናስብበት ነው፡፡ (ዕብ 4፡1-10)

#የሰንበት_ቀን_መሰጠት_ዓላማ

የሰው ልጅ ባሕርይ ደካማ ነውና እግዚአብሔር ሰንበትን ሰራለት፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ደካማ ባህሪያችንን ስለሚያውቅ ከሳምንቱ ዕለታት አንዱ ሰንበት እድርጎ ለዕረፍት ሰጠን፡፡ ከድካማችን የተነሳ በዕለቱ መስራት አንችልምና ሰንበት ለሥጋችን ጠቃሚ ነው፡፡ ነገር ግን ሰንበት የተሰጠበት ምክንያት ሰው በዚህ ዓለም ሲደክም ስጋውን ብቻ ሲያገለግል እንዳይኖር የአምላኩን ውለታ እያሰበ በመንፈሳዊ አገልግሎት ፀንቶ እንዲኖር ነው፡፡ ዘጸ 5-14-15

ለምልክት

አምላካችን እግዚአብሔር እንደተናገረው ሁሉ ሰንበት የዘላለማዊ እና የመንፈሳዊ ዕረፍታት ምልክት ሆኖ የተሰጠ ጸጋ ነው፡፡ ዘጸ 31-13 ሰንበት ለሚመጣው ዘላለማዊ ዕረፍት ምሳሌ ሆኖ የተሰጠ የብሉይ ኪዳን ሕግ ነው፡፡ በህጉ መሰረት በሰንበት ዕረፍተ ሥጋ ይደረጋል፡፡ይህም ለኋላው ዘመን ለድኅነተ ነፍስ ምሳሌ ነው፡፡ በሐዲ ኪዳንም የተገለጠው የክርስቶስ ትንሳኤ በሰንበተ ክርስቲያን ተፈፅሟል፤ ሰንበተ ክርስቲያንም የሰው ልጆች ለዘለዓለም አርፈው ከእግዚአብሔር ጋር በደስታ የሚኖሩበት ምስጢረ ትንሣኤ የተገለጠባት የድኅነት ቀን ናት፡፡

#ሰንበትን_እንዴት_ማክበር_ይገባል?

ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰንበት ለመንፈሳዊ ሥራዎች(አገልግሎቶች) የተሰጠች መሆኗን ለማስተማር በሰንበት ድውያንን ይፈውስ፣ በምኩራብ እየተገኘም ያስተምር ነበር፡፡ (ዮሐ 5፡2-11 ፣9-14)፣(ሉቃ 14፡1-6)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመፍቅረ ሰንበት አይሁድ ስለሰንበት አከባበር ሲያስተምራቸው ‹‹ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበትም በጉ በጉድጓድ ቢወድቅበት ይዞ የማያወጣው ማን ነው? እንግዲህ ሰው ከበግ እንደምን አይበልጥም? ስለዚህ በሰንበት መልካም ሥራን መሥራት ተፈቅዷል›› ብሏል።

ማቴ12-10-13 ክርስቲያን ሰንበትን ሲያከብር እንደጌታችን ትምህርት መንፈሳዊ ሥራን በመሥራት ይገባል እንጂ ልክ እንደ አይሁድ ያጠፈውን ሳይዘረጋ የዘረጋውን ሳያጥፍ ሊያሳልፍ አይገባም፤ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሯል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር!!!
    Join @ortodoxslijoch