Get Mystery Box with random crypto!

#የምወደው_ልጄ_ይህ_ነው!! በጥምቀት በዓል በታላቅ ፍቅር ሲያመሰግኑ በነበሩት ወጣቶች አንጻ | ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች

#የምወደው_ልጄ_ይህ_ነው!!

በጥምቀት በዓል በታላቅ ፍቅር ሲያመሰግኑ በነበሩት ወጣቶች አንጻር የሚከተለው #ተግሳጽ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ- "የምወደው ልጄ ይህ ነው!"
<< የምወደው ልጄ ይህ ነው! ባንተስ ደስ የምለኝ መቼ ነው?? >>
( በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ)

በእርግጥ ያንተን ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መውጣት አይችልም፤ ኦሪት ዘፍጥረት የቱ ጋር እንደሆነ, ዜና መዋእልም የት እንደሚገኝ አያውቅም። ምናልባት ከራእይ ዮሐንስ ሀይለ ቃል ለማንበብ መዝ.ዳዊት ላይ ገልጦ ይዳክር ይሆናል፤ ምንም ምስጥር አያውቅም፤ ለአንድምታው,ለትርጓመውም እንግዳ ይሆናል፤ መላእክት ጻድቃን ሰማዕታትን አይለይም።

ጊዮርጊስ ሰማዕቱን ከመላእክት አንዱ አድርጎ ያስበዋል፤ ለየትኛውም ሃይማኖታዊ ጥያቄ መልስ መስጠት አይችልም፤ ዛሬም የእርሱ ጥያቄ ዓሣ ፆም አለው ወይስ የለውም ? የምል ልሆን ይችላል፤ በማህሌት እና በሰዓታት በቅዳሴና በወረብ መካከል ያለው ልዩነት አይገባውም! ለእርሱ በቤ/ክን ውስጥ የሚሰማ ዜማ ሁሉ ቅዳሴ ነው፤ ስለ ስርዓተ ቤ/ክን ምንም አያውቅም በእርሱ አስተሳሰብ በፆም ቀን ፀበል መጠጣት ፆሙን አያፈርስም፤ የምያማትበውም አንተ በምታውቀውና በምታብራራው ሥርዓት ሳይሆን እጅን በማወዛወዝ ልሆን ይችላል፤ የሰንበት ት/ቤትን ተከታታይ ት/ት አልተማረም ፤ በጉባኤ አባልነትም አልተመዘገበም፤ በየትኛውም ምድብ አያገለግልም፤ ከየተኛው መንፈሳዊ ት/ቤት አልተመረቀም፤ ይሁንና የምወደው ልጄ ይህ ነው።

የሚዘምረው መዝሙርም ሥርዓተ ቤ/ክን ያልጠበቀ ነው፤ ሽብሸባውም እንዲሁ፤ አለባበሱም ብዙ ጉድለት አለበት፤ ነጠላውን እንደዋዛ ይጠመጥመዋል እንጅ በትምህርተ መስቀል አያደርግም፤ አረማመዱም የምንፈሳዊ ሰው አይደለም ፀጉሩን የተንጨባረረ እና የተጠቀለለ ነው፤ የምውልበት ሥፍራ መልካም ላይሆን ይችላል፤ በሰው ሁሉ የተጠላ የተተፋ፤ ይሁን ግን ልንገርህ -የምወደው ልጄ ይህ ነው።

አናንያ ሆይ < የሳኦልን ክፉ አትንገረኝ ፤ የእርሱን የቀደመ ጭካኔውንና በሰው ዘንድ ያለውን ክፉ ስም አትንገረኝ፤ ጌታ ሆይ መጥፎ ነው >እያልክ አትወትውተኝ ሁሉንም አውቀዋለሁ፤ ነገር ግን ካንተ ይልቅ የሚሰማኝ የምፈራኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው።

አንተ በቤቴ ኖረህ ሳትሰማኝ ቃሌንና ትእዛዜን ተለማምደህ ቸል ብለህ ስትኖር፣ የተናገርኩትን ትእዛዝ ቸል ሳይል የምፈፅም የእኔ ምርጥ እቃ- የምወደው ልጄ ይህ ነው።
አንተ የለመድከውን አንተ የተዳፈርከውን መቅደሴን በሩቅ እያየ የምፈራ የምንቀጠቅጥ ሳነሳው የምነሳ ሳስቀምጠው የምቀመጥ ምርጥ እቃዬ -የምወደው ልጄ ይህ ነው።

እርግጥ ነው ዜማ አያውቅም እኔን ግን ያውቀኛል፤ ምንም ጥቅስ አልያዘም ትህትናን ግን ይዙዋል፤ የቅዳሴን ተሰጦ አይመልስም እኔ ስጠራው ግን ይመልስልኛል: እኔ ግን ይፈራኛል: ስለ ስሜ ስተጋ አይታክትም፤ ስለ ክብሬ ሲንከራተት አልተማረረም፤ ያንተን ቸልተኛውን ትእዛዝና ተገሳፅ በትህትና ተቀበለ እንጅ እኔን አክብሮ አከበረህ እንጅ ለታቦት ማለፍያ መንገድ ስደለድል፤ ቆሻሻ ሲዝቅ አፈር ሲሸከም ካንተ ያገኘውን ጥቅስ በየመንገዱ ሲሰቅል ድንጋይ ሲሸከም በፊቱ ላይ ደስታን እንጅ አንዳች ምሬት አላየሁበትም። ስሜታዊ ሆኖ ነው: ስላልበሰለ ነው አትበለኝ የቤቴ ቅናት የምትበላው ለእኔ የታመነ የምወደው ልጄ ይህ ነው።

ስሜታዊ መሆንስ እንዳንተ ማንቀላፋት ነው፤ መብሰልስ ቸልተኝነት ነው ስምኦን ሆይ ስለሱ አንዳች ክፉ አትንገረኝ ኃጥአተኛ ነው እንድህ አድርጓል አትበለኝ አንተ ያልሠራሀውን አልሠራም እኔ ያየሁትን ክፋቱን አይደለም፤ በንስሐ በትህትና ማጎንበሱን ነው። ለክብሩ ሳይሳሳ በእንባ እግሮቼን አጥቧል ምንጣፍ አንጥፎ ሳር ጎዝጉዞ በአደባባይ ከፊቴ ስደፋ ያን ጊዜ ነው የልጄን ልብ ያየሁት:: ስለሱ አንዳች ክፉ አትንገረኝ - የምወደው ልጄ ይህ ነው።

አንተ መዘመር ሰልችቶሃል ፤ ማጨብጨብም ደክሞሃል፤ እርሱ ግን ስያመሰግን ብውል ብያድር አይጠግብም። ምናልባት ጀማሪ ስለሆነ ነው ትል ይሆናል፤ አንተ ፈፃሚ ስለሆንክ ነው የተሰላቸህው? አንተ መዝሙር ምታጠናው ከበሮ ለመምታት ብቻ ይሆናል ፤እርሱ ግን በባዶ እጁ በማመስገኑ ደስተኛ ነው። አንተ እንዴት እንደምሸበሸብ እያወክ ታበላሸዋለህ ፤ እርሱ ግን ላገኘው ሁሉ እንዲህ ነው የሚሸበሸበው እያለ ይጨነቃል፤ ልክ ነህ ጀማሪ ነው፥ ስሜታዊ ነው፤ ያልበሰለ ነው ፤ ነገር ግን የምወደው ልጄ ይህ ነው። ባንተ ደስ አልተሰኘሁም፤ በተማርኸው መጠን አልኖርክም በዘራሀው መጠን አላፈራህም፤ ስለ ቅናቱ በእርሱ ደስ የምለኝ - የምወደው ልጄ ይህ ነው። ባንተስ ደስ የምለኝ መቼ ነው????????????

ይህን የእግዚአብሔር ተግሳጽ ከመቀበል ጋር አንድ መልእክት ይቀራል:: እነዚህ ወጣቶች ቀድሞም በቃለ እግዚአብሔር ተኮትኩቶው አላደጉም:: ምንም በጥሩ ምግባር ባይታወቁም በልባቸው ግን እንደ እሳት የሚንቀለቀል ሃይማኖት አላቸው:: ፈሪሃ እግዚአብሔር አላቸው::

እኛ ወደ እነርሱ ባንሄድ እነሱ ግን ወደኛ መጥተዋል:: ሌላ ምን እንላለን:: ነብዩ <መንፈሱ ሰብስባቸዋልና ከነዚህ አንድ አትጠፋም > እንዳለ ያለ ቀሽቃሽ የሰበሰባቸው የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲጠብቃቸው እንዲያጸናቸው እንመኛለን:: በጎች ኑረው በረት ጠበባ አይባልምና ቤተ ክርስቲያንም መዋቅሯን አጠናክራ እንደምትቀበላቸው ተስፋ እናደርጋለን::

ለወጣቶቹ ግን < ምንነው ለጥምቀት ብቻ > ከሚል ምክር ጋር አንድ ቃለ ሐዋርያ እንጥቀስ::
" እግዚአብሔር፥ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፥ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም። " ዕብራውያን 6፥10

ወጣት ሆይ! አንብበህ ስታበቃ ተገሳፁ ላንተ እንደሆነ አስተውል!! "እኛስ ለታቦት ሥራ አለብን" ብለው እራሳቸውን ዝቅ ያደረጉ ወንድሞችህ "የምወደው ልጄ ይህ ነው" ተብለዋል። አንተም ከእነርሱ ተማርና የምወደው ልጄ አንተ ነህ ለመባል ያብቃህ!
[ጸሐፊ :- ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
የምወደው ልጄ ይህነው !