Get Mystery Box with random crypto!

​​እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አቡነ አረጋዊ እና አባ አርከሌድስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ | ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

​​እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አቡነ አረጋዊ እና አባ አርከሌድስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

#አቡነ_አረጋዊ_ዘደብረ_ዳሞ

ጻድቁ ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮዽያ ቢሆንም ሃገረ ሙላዳቸው የጥንቱ የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ናት:: አቡነ አረጋዊ ከዘጠኙ (ተስዓቱ) ቅዱሳን አንዱ ናቸው:: ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው::

ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው:: በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር:-

1. የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ:
2. ዓላማ (የእግዚአብሔር መንግስት) እና
3. ገዳማዊ ሕይወት ነው::

አቡነ አረጋዊን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግስት ነው:: እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል:: አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል::

በምናኔ ቅድሚያውን አባ ዸንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ:: ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት 5ኛው መቶ ክ/ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ::

በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮዽያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም:: ስለዚህም በ470ዎቹ ዓ/ም አልዓሜዳ በኢትዮዽያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ::

ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ: ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው:: ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው:: ይህች ቦታ ቤተ ቀጢን ትባላለች:: አቡነ አረጋዊና 8ቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር::

ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዛው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ:: በወቅቱ በአቡነ ሰላማ: በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አቡነ አረጋዊ እንደገና አቀጣጠሉት::

ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት:: የካደውን እየመለሱ: የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ:: ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ::

ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው:: በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ:: ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አቡነ አረጋዊ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማሕበር ነበር:: በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም::

የነ አቡነ አረጋዊ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ:: ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው:: እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ::

#ዸንጠሌዎን በጾማዕት:
#ገሪማ በመደራ:
#ሊቃኖስ በቆናጽል:
#አባ ይምዓታ በገርዓልታ:
#ጽሕማ በጸድያ:
ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ::
አባ አረጋዊ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ዳሞ (እዛው ትግራይ) ሆነ::

በሃገራችን ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ እኒህ ጻድቅ ናቸው:: ጻድቁ የተወለዱት በ5ኛው መቶ ክ/ዘ አጋማሽ አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው ንጉሥ ይስሐቅና ቅድስት እድና ይባላሉ:: የተለወለዱበት አካባቢም ሮም ነው::

ስማቸው ብዙ ዓይነት ነው:: ወላጆቻቸው "ዘሚካኤል" ሲሏቸው በበርሃ "ገብረ አምላክ" ተብለዋል:: በኢትዮዽያ ደግሞ "አረጋዊ" ይባላሉ:: አቡነ አረጋዊ ምንም የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም በልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው ነበርና ጠፍተው ገዳም ገቡ::

በዚያም በገዳመ ዳውናስ (ግብጽ) የታላቁ ቅዱስ ዻኩሚስ ደቀ መዝሙር ሆነው ከነ አባ ቴዎድሮስ ጋር ሥርዓተ መነኮሳትን ተምረዋል:: ከመነኮሱ ከዓመታት በሁዋላም ወደ ሃገራቸው ሮም ተመልሰው በማስተማር 7 ያህል የቤተ መንግስት ሰዎችን ወደ ምናኔ ማርከዋል::

"የት ልሒድ" ብለው ሲያስቡም ቅዱስ መልአክ በክንፉ ጭኖ ወስዶ ኢትዮዽያን አሳያቸው:: ተመልሰውም ለ8 ባልንጀሮቻቸው "ሃገርስ ባሳየሁዋችሁ! ሐዋርያ ሳያስተምራት በሕጉ በሥርዓቱ ጸንታ የምትኖር" ብለው ከ8ቱ ጋር ወደ ኢትዮዽያ መጡ::

በዚህ ጊዜም እናታቸው ቅድስት እድናና ደቀ መዝሙራቸው አባ ማትያስ አብረው ነበሩ:: ወደ ሃገራችን የመጡ በ470ዎቹ አካባቢ ሲሆን አልዓሜዳ በክብር ተቀብሏቸዋል:: በቤተ ቀጢን (አክሱም) ተቀምጠውም መጻሕፍትን እየተረጐሙ: ወንጌልን እየሰበኩ ቆይተዋል::

ለሥራ በተለያዩ ጊዜም አቡነ አረጋዊ በዓት ፍለጋ ብዙ ደክመዋል:: በመጨረሻ ግን ደብረ ዳሞን (ደብረ ሃሌ ሉያን) አይተው ወደዷት:: የሚወጡበት ቢያጡም ጅራቱ 60 ክንድ የሚያህል ዘንዶ ተሸክሞ ከላይ አድርሷቸዋል::

እንደ ወጡም "ሃሌ ሉያ ለአብ: ሃሌ ሉያ ለወልድ: ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ" ብለው ቢያመሰግኑ ከሰማይ ሕብስት ወርዶላቸው ተመግበዋል:: በዚህም ቦታዋ "ደብረ ሃሌ ሉያ" ተብላለች:: ጻድቁ ቦታውን ከገደሙ በሁዋላ ከተለያየ ቦታ መጥተው 6ሺ ያህል ሰዎች በእጃቸው መንኩሰዋል::

ምናኔን በማስፋፋታቸውና ሥርዓቱን በማስተማራቸውም "አቡሆሙ ለመነኮሳት ዘኢትዮዽያ - የኢትዮዽያ መነኮሳት አባት" ይባላሉ:: አቡነ አረጋዊ በሕይወታቸው ከተጋድሎ ባሻገር በወንጌል አገልግሎትና መጻሕፍትን በማዘጋጀትም ደክመዋል::

ቅዱስ ያሬድና አፄ ገብረ መስቀልም ወዳጆቻቸው ነበሩ:: በተራራው ግርጌ ያለችውን ኪዳነ ምሕረትን ለሴቶች ሲገድሟት ቀዳሚዋ መነኮስ እናታቸው ንግስት እድና ሁናለች::

ጻድቁ ንጹሕ ሕይወታቸውን ፈጽመው በተወለዱ በ99 ዓመታቸው በገዳሙ በስተ ምሥራቅ አካባቢ ተሰውረው ብሔረ ሕያዋን ገብተዋል:: ጌታም 15 ትውልድን የሚያስምር የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል:: ዛሬ ጻድቁ የተወለዱበት ቀን ነው::

@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur