Get Mystery Box with random crypto!

​​​​ጾመገሀድ በየኔታ ዘለዓለም ሐዲስ ከዘጠኙ ዓበይት የጌታ በዓላት ሁለቱ የልደትና የጥምቀት | ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

​​​​ጾመገሀድ
በየኔታ ዘለዓለም ሐዲስ


ከዘጠኙ ዓበይት የጌታ በዓላት ሁለቱ የልደትና የጥምቀት በዓላት ተጠቃሾች ናቸው በሁለቱ በዓላት ቀን ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በኀዘን ማሳለፍ እንደሌለበት ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ ምክንያቱም የክርስቶስ ልደትና ጥምቀት የዕዳ ደብዳቤያችን የተቀደደባቸው የድኅነታችን መሠረት የተጣለባቸው ዐበይት በዓላት ስለሆኑ ነው።

እነዚህ በዓላት በረቡዕና በዓርብ ቀን ከዋሉ አስቀድመን በዋዜማው ለውጥ አድርገን እንጾማቸዋለን ልደት ረቡዕ ከሆነ ማግሰኞ በዋዜማው፣ ዓርብ ከሆነ ሐሙስ በዋዜማው እስከምሽቱ አንድ ሰዓት (13 ሰዓት) እንጾማቸዋለን በሌሎችም ቀናት በዋዜማቸው በየዓመቱ ይጾማሉ ቀናቱ ሁለት ቢሆኑም ቁጥራቸው ግን ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ተብለው ነው የሚቆጠሩት፡፡

ገሀድ ሁለት መጠሪያ ስሞች አሉት ገሀድና ጋድ፡፡ #ገሀድ ማለት መገለጥ መታየት መታወቅ ማለት ነው ተገለጠ ታየ ታወቀ የተባለውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ምንም ከዚያ በፊት አምላክነቱ የተገለጠባቸው ብዙ መንገዶችና ተአምራት ቢኖሩም አብ በደመና ሁኖ የምወደው ልጄ ይህ ነው በማለት፣ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ በመቀመጥ የክርስቶስ አምላክነት የተገለጠበት ዕለት ስለሆነ ገሀድ መገለጥ ተብሎ ተሰይሟል።

በሌላም በኩል #ጋድ ማለት ለውጥ ማለት ነው ልደትና ጥምቀት ረቡዕና ዓርብ ሲሆኑ ለውጥ ሁኖ የሚጾምበት ማለት ነው ስለዚህ ገሀድ ስንል የክርስቶስን አምላክነት በዕለተ ጥምቀት መገለጥ፣ ጋድ ስንል ደግሞ ለዓርብና ለረቡዕ ጾም ለውጥ ሁኖ የተጾመውን ጾም ማለታችን ነው፡፡ ይህንን ጾም ጥር 10 ቀን የሚነበበው ስንክሳር እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፡፡

ወበእንተዝ አዘዙነ አበዊነ ከመ ይደሉ ንጹም እሎንተ ክልኤተ ዕለታተ ዘእምቅድመ በዓለ ልደት ወበዓለ ጥምቀት እስመ እላ ዕለታት ህየንቴሆሙ ለረቡዕ ወዓርብ ሶበ ይከውን ላዕሌሆሙ በዓለ ልደት ወጥምቀት ወበዝንቱ ይትፌጸም ለነ ክልኤቱ ግብር ግብረ ጾም ወግብረ በዓል ወከመዝ ሥሩዕ ውስተ አብያተ ክርስቲያኖሙ ለግብፃውያን ወለእመ ኮነ ዕለተ በይረሙን ዘውእቱ አስተርእዮ በዕለተ እሑድ አው በዕለተ ሰንበተ አይሑድ ይጹሙ በዕለተ ዐርብ እምቅድሜሁ እስከ ምሴት በከመ ተናገርነ ቅድመ ወለእመ ኮነ በዓለ ልደት ወበዓለ ጥምቀት በዕለተ ሰኑይ ኢይትከሀል ከመ ይጹሙ በዕለተ ሰንበት ዳዕሙ ይትዐቀቡ እምነ በሊዕ ጥሉላተ፡፡

ስለዚህ ከልደትና ከጥምቀት በዓል በዋዜማ ያሉትን ሁለቱን ዕለታት እንድንጾም አዘዙን የልደትና የጥምቀት በዓል በረቡዕና በዓርብ ላይ በሚሆን ጊዜ በረቡዕና በዓርብ ፈንታ እንድንጾማቸው ይገባልና በዚህም ሁለት ሥራ ይፈጸምልናል የጾም ሥራና የበዓል ማክበር ሥራ ነው እንዲሁም በግብፃውያን አብያተ ክርስቲያን የተሠራ ነው በይረሙን (መገለጥ፣ ገሀድ) በእሑድ ወይም በአይሁድ ሰንበት ቀን ቢሆን ይህም ጌታ የተገለጸበት ጥር ዐሥር ቀን ነው በዋዜማው ዓርብ እስከምሽት ይጹሙ አስቀድመን እንደተናገርን ጥሉላትን ከመብላት ይጠበቁ በማለት ይገልጸዋል፡፡

ከላይ እንዳየነው ጥምቀት ወይም ልደት እሑድና ቅዳሜ ከዋሉ ጾሙ መጀመር ያለበት ዓርብ መሆኑን ተመልክተናል ይህንም መነሻ በማድረግ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጥምቀት ሰኞ ሲሆን ዓርብ እስከ አንድ ሰዓት፣ ቅዳሜ እስከ ስድስት፣ እሑድ እስከ ቅዳሴ መውጫ እስከ ሦስት በመቁጠር የጾሙን ሰዓት 13 ሰዓት ያደርጉታል ይህም ከላይ የተገለጠውን ስንክሳር መነሻ በማድረግ የመሚናገሩት ስለሆነ አክብረን እንቀበለዋለን ቅዳሜ እስከ ስድስት ለመጾሙም ሃይ ምዕ 20 ተጠቃሽ ነው።

በሌላ በኩልም ጋድ አንድ ቀን ነው ሰኞ ሲሆን እሑድን ብቻ ከጥሉላት እንከለከላለን እንጅ ቅዳሜን አይጨምርም በማለት ይህን የሚቃወሙ አሉ ስንክሳር የተናገረውን ምን እናድርገው ተብለው ሲጠየቁም ስንክሳር የታሪክ እንጅ የሥርዓት መጽሐፍ አይደለም የሚል መልስ ነው የሚሰጡት፡፡

ይህ ጥያቄ ወደሌሎች ሊቃውንት ሲቀርብ የሚሰጡት መልስ ደግሞ ስንክሳር ታሪክ ብቻ ሳይሆን ሥርዓትም የተካተተበት መጽሐፍ መሆኑን ይናገራሉ በእርግጥ ስንክሳር ማለት እስትጉቡእ ስብስብ ማለት ስለሆነ ሥርዓተ ቤተ ክርስተቲያንን ከሠሩ አበው ታሪክ የተሰበሰበ መሆኑን መዘንጋት የለብንም ከላይም እንዳየነው ወበእንተዝ አዘዙነ አበዊነ ስለዚህ አባቶቻችን አዘዙን በማለት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጻፉ አበው አዘዙን አለ እንጅ ስንክሳርን የጻፉ ሰዎች የራሳቸውን ሐሳብ ያንጸባረቁበት አይደለም ስንክሳርም ቢሆን ምንም ቁጥሩ ከአዋልድ መጻሕፍት ቢሆን የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ነውና ጥምቀትና ልደት ሰኞ ከሆኑ ቅዳሜና እሑድን ከጥሉላት ተከልክለን ቅዳሜንም እስከ ስድስት ሰዓት ጹመን የአበውን ትዕዛዝ ማክበር አለብን፡፡

በሌላም በኩል ጋድ አንድ ነው እሱም የጥምቀት ዋዜማ ብቻ ነው የልደት ዋዜማ የለውም የሚሉም አሉ እንዲህ ለሚሉት መልሱ አጭር ነው ጾመ ነቢያት ስንት ነው የሚል ጥያቄ ማንሣት ነው እንደሚታወቀው ጾመ ነቢያትን ስንጾም ቀናቱ አርባ አራት ናቸው 40 ጾመ ነቢያት፣ 3ቱ የፊልጶስ ደቀ መዛሙርት የጾሙትና አብርሐም ሦርያዊ ተራራ ያፈለሰበት ጾም፣ አንዱ ጾመ ገሀድ ነው ስለዚህ በበዓለ ልደት ዋዜማ የምንጾመው ገሀድ መሆኑን ሁሉም የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡

ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በተግሳፁ አንዳስቀመጠው "ስለ ፆም ክርክር በተነሳ ጊዜ ሁሌም ቢሆን ለፆም አድሉ "

"" መልሱ እንዲህ ከምስክር መምህራን ሲሆን ይሻላል፡፡ እኛ ከምንናገረው፡፡

የኔታ ዘለዓለም ሐዲስ ማለት የክቡር ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ምክትልና የ፬ቱ መጻሕፍተ ትርጓሜ መምህር ናቸው፡፡ (እንዲያው የኔ ብጤ የፌስቡክ አርበኛ እንዳይመስሉህ ብዬ ነው!)

DN YORDANOS ABEBE

ዝክረ ቅዱሳን ጉባኤ

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል:: አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/

#ሼር
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur