Get Mystery Box with random crypto!

ወር በገባ በ15 ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ነው። ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ ❖ | "ቤተ ማርያም መንፈሳዊ ሚዲያ💒

ወር በገባ በ15 ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ነው።
ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ

❖ ይህም ቅዱስ ከዋክብትን ከሚያመልኩ ሰዎች ሀገር ነው አባቱም ክብር ይግባውና የክርስቶስን አምልኮት የሚጠላ የጣዖት ካህን ነበር፤ በዚያን ጊዜም የእግዚአብሔር ቸርነት ቀሰቀሰችውና አነሳሥታ የንጽቢን ጳጳስ ወደሆነው ወደ አባ ያዕቆብ ወሰደችው እርሱም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቀው በእርሱም ዘንድ በጾምና በጸሎት ያለማቋረጥ እየተጋደለ ለብዙ ዘመናት ኖረ።
❖ የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ አደረበት አሕዛብን ተከራክሮ ይረታቸው ነበር፤ ኒቅያ በሚባል ከተማ የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት አባቶች ኤጲስቆጶሳት ጉባኤ በተደረገ ጊዜ ይህ ቅዱስ ኤፍሬም ከመምህሩ ከአባ ያዕቆብ ጋራ ወደ ቅዱሳን ጉባኤው ሔደ።
❖ ከሀዲው አርዮስንም አውግዘው ከለዩት በኋላ ይህ ቅዱስ ኤፍሬም በዚያች ሌሊት ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ አየ ከዚህ ራእይም የተነሣ አደነቀ ይገልጽለትም ዘንድ ወደ ጌታ ጸለየ ይህ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ባስልዮስ ነው የሚል ቃል ከሰማይ ወደርሱ መጣ።
❖ ቅዱስ ኤፍሬምም ያየው ዘንድ ወድዶ ወደ ቂሣርያ ሀገር ተጓዘ በደረሰም ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በማእዘኑ በኩል ቆመ ቅዱስ ባስልዮስንም ወንጌልን ሊያነብ በወጣ ጊዜ ዋጋው ብዙ የሆነ ከወርቅ የተሠራ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ አየው፤ ሦስት ምልክቶችንም እሰኪያይ ድረስ ተጠራጠረ ምልክቶችም እኒህ ናቸው ነጭ ርግብ መጥታ በራሱ ላይ አረፈች ሁለተኛም በልብሱ ላይ የሚያርፉ ተዋሐስያን ይቃጠሉና ይረግፉ ነበር። ሦስተኛም ከአፉ የእሳት ነበልባል ወጥቶ በምእመናን ላይ ያድር ነበር።
❖ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ባስልዮስ ቅዱስ ኤፍሬምን በስሙ ጠራውና እርስ በርሳቸው ሰላምታ ተለዋወጡ፤ በአስተርጓሚ ይነጋገሩ ጀመሩ፤ የየራሳቸውንም ቋንቋ ይገልጽላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንዲጸልይ ቅዱስ ኤፍሬም ቅዱስ ባስልዮስን ለመነው፤ በጸለየ ጊዜም ተገልጾላቸው ያለ አስተርጓሚ ተነጋገሩ።
❖ ከዚህ በኋላም ቅዱስ ኤፍሬምን ዲቁና ሾመው ከጥቂት ወራትም በኋላ ቅስና ሾመው ከእርሱም ብዙ ትሩፋቶች ተገለጡ በመንፈሳዊ ተጋድሎ ሁሉ ተጋደለ፤ አንዲት በወገን የከበረች ባለ ጸጋ ሴት ነበረች ራስዋንም ለካህን ለማስመርመር ታፍር ነበር ከታናሽነቷ ጀምራ የሠራችውን ኃጢአቷን ሁሉ ጽፋ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ አመጣች፤ አባቴ ሆይ በዚህ ክርታስ ውስጥ ያሉት ኃጢአቶቼ ይደመሰሱ ዘንድ ተናገር ብላ ለመነችው እርሱም እንዳልሺው ይሁንልሽ አላት፤ እርሷም ክርታሱን በገለጠች ጊዜ ከአንዲት ኃጢአትዋ በቀር ኃጢአቷ ሁሉ ተደምስሶ አገኘች ያችም ኃጢአት አስጨናቂና ታላቅ ኃጢአት ነበረች።
❖ ባገኘቻትም ጊዜ ያቺን የቀረች ኃጢአቷን ያጠፋላት ዘንድ አልቅሳ ለመነችው እርሱም ወደ ቅዱስ ኤፍሬም ሒጂ እርሱ ይህችን የቀረች ኃጢአትሽን ያስተሠርይልሻል አላት፤ ወዲያውም ወደ ቅዱስ ኤፍሬም ሔዳ ከርሷ የሆነውን ሁሉ ነገረችው፤ እርሱም እንዲህ አላት ፈጥነሽ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ሒጂ ግን ሙቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዱት ታገኝዋለሽ ሳትጠራጠሪም ይህችን ክርታስ በላዩ ጣይ ይደመሰስልሻል።
❖ ያቺም ሴት ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ተመለሰች ሙቶ ተሸክመው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዱትም አገኘችው፤ ያንንም ክርታስ በአስክሬኑ ላይ ጣለችው ወዲያውኑም ተደመሰሰላት፤ ይህም ቅዱስ ኤፍሬም ብዙ ተአምራቶችን አድርጓል በዘመኑም ዲዳን የሚባል አንድ ከሀዲ ተነሣ ይህም አባት ኤፍሬም ተከራክሮ ረታው።
❖ እጅግም ብዙ የሆኑ ዐሥራ አራት ሽህ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ ከእርሳቸውም ውስጥ አምላክን የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ውዳሴዋ ነው፤ አቤቱ የጸጋህን ማዕበል ግታልኝ እስከሚል ድረስ ድርሳናትን ደርሶአል፤ መልካም የሆነ ገድሉንም በፈጸመ ጊዜ ወደ ወደደው ወደ እግዚአብሔር ሔደ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በብፁዕ ኤፍሬም ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
ሰላም ለኤፍሬም ከመ ርግብ ተመሲሎ። መንፈስ ቅዱስ ዘርእየ ለርእሰ ባስልዮስ ዘይጼልሎ። ውኂዘ ድርሳናት ብዙኀ ሶበ ለልቡ ኀየሎ። አኀዝ እምኔየ መዋግደ ጸጋከ ኲሎ። ለእግዚአብሔር አምላክ እንዘ ይብል ሰአሎ።

https://t.me/Orthodoxtewahdoc ጆይን እያላችሁ ተቀላቀሉ