Get Mystery Box with random crypto!

#ሰማዕቱ ቅዱስ ሚናስ ማን ነው ❖#ወር_በገባ_በ15 የቅዱስ ሚናስ ሰማዕት ወርኀዊ በዓሉ ነ | "ቤተ ማርያም መንፈሳዊ ሚዲያ💒

#ሰማዕቱ ቅዱስ ሚናስ ማን ነው

❖#ወር_በገባ_በ15 የቅዱስ ሚናስ ሰማዕት ወርኀዊ በዓሉ ነው።
የዚህም ቅዱስ አባቱ አናቅዮስ ከሚባል አገር ነው ስሙም አውዶክስዮስ ነው እርሱም አገረ ገዥነት ተሹሞ ሳለ ወንድሙ ቀንቶበት በንጉሥ ዘንድ ነገር ሠራበት ንጉሡም ወደ አፍራቅያ አገር ሰደደውና በዚያም አገረ ገዢ አድርጎ ሾመው የአገር ሰዎችም ሁሉ ደስ አላቸው እርሱ ለሰው የሚራራ እግዚአብሔርንም የሚፈራ ደግ ሰው ነውና።

❖ እናቱም ልጅ አልነበራትም በአንዲት ዕለት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በበዓልዋ ቀን ገብታ የክርስቲያንን ወገኖች ያማሩ ልብሶችን ለብሰው ከልጆቻቸው ጋር ደስ እያላቸው ሲገቡ አየቻቸው።

❖ በእመቤታችንም በቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ፊት አለቀሰች ልጅን ይሰጣት ዘንድ ወደ ልጅዋ ወደ እግዚአብሔር እንድትለምንላትም ለመነቻት በዚያንም ጊዜ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል አሜን የሚል ቃል ወጣ።

❖ ከዚህም በኋላ ወደ ቤቷ ገብታ ይህን ቃል ለባሏ ነገረችው እርሱም የእግዚአብሔር ፈቃዱ ይሁን አለ፤ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ እግዚአብሔር ይህን የተባረከና የከበረ ልጅን ሰጣት የእመቤታችንም ሥዕል ሚናስ ብላ እንደሰየመችው ስሙን ሚናስ ብለው ሰየሙት፤ ጥቂት በአደገ ጊዜም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተማሩት።

❖ ዐሥራ ሁለት ዓመትም ሲሆነው በመልካም ሽምግልና አባቱ አረፈ ከእርሱም በኋላ በሦስተኛ ዓመት እናቱ አረፈች ቅዱስ ሚናስም ብቻውን ቀረ።
❖ መኳንንቱም አባቱን አብዝተው ከመውደዳቸው የተነሣ ሚናስን በአባቱ ፈንታ ምስፍናን ሾሙት እርሱም የክርስቶስን አምልኮት አልተወም።

❖ ዲዮቅልጥያኖስም በካደ ጊዜ ሁሉንም ሰዎች ጣዖታትን እንዲአመልኩ አዘዛቸው ብዙዎችም ክብር ይግባውና በክርስቶስ ስም በሰማዕትነት ሞቱ።
❖ በዚያንም ጊዜ ሚናስ ሹመቱን ትቶ ወደ ገዳም ገባ ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ ብዙ ዘመናት ኖረ። በአንዲትም ዕለት ሰማይ ተከፍቶ ሰማዕታትን የብርሃን አክሊሎችን ሲአቀዳጁአቸው አየ ስለ ክርስቶስ ስም በመከራ የደከመ ይህን አክሊል ይቀበላል የሚል ቃልን ሰማ።

❖ በዚያንም ጊዜ ወደ ከተማ ተመለሰና ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመነ ሰዎችም አብዝተው አባበሉት በወገን የከበረ እንደሆነ እነርሱ ያውቁ ነበርና።
❖ መኰንኑም ብዙ ቃል ኪዳን ገባለት ባልሰማውም ጊዜ ጽኑዕ በሆነ ሥቃይ እንዲአሠቃዩት አዘዘ፤ ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ፤ በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ ብዙዎችም በእርሱ ምክንያት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በሰማዕትነት ሞቱ።

❖ የቅዱስ ሚናስንም ሥጋ ወደ እሳት እንዲጥሉት መኰንኑ አዘዘ እሳትም አልነካውም ምእመናን ሰዎችም የቅዱስ ሚናስን ሥጋ ወስደው በአማሩ ልብሶች ገነዙት የስደቱ ወራትም እስከሚፈፀም በአማረ ቦታ ውስጥ አኖሩት።
❖ በዚያንም ወራት የመርዩጥ አገር ሰዎች ከአምስቱ አገሮች ሠራዊትን ሊአከማቹ ወደዱ የቅዱስ ሚናስንም ሥጋ ረዳት ይሆናቸው ዘንድ በመንገድም እንዲጠብቃቸው ከእርሳቸው ጋር ወሰዱት።

❖ እነርሱም በባሕር ላይ በመርከብ ውስጥ ሳሉ ፊታቸው እንደ ከይሲ አንገታቸው እንደ ግመል አንገት ያለ አውሬዎች ከባሕር ወጡ ይልሱትም ዘንድ ወደ ቅዱስ ሚናስ ሥጋ አንገታቸውን ዘረጉ ከቅዱስ ሚናስም ሥጋ እሳት ወጥታ እነዚያን አራዊት አቃጠለቻቸው ሰዎችም አይተው አደነቁ ደስታም አደረጉ ፈርተው ነበርና።

❖ ወደ እስክንድርያ አገርም ደርሰው ሥራቸውን ፈጽመው ወደ ሀገራቸው በሚመለሱ ጊዜ የቅዱስ ሚናስን ሥጋ ከእሳቸው ጋር ሊወስዱ ወደው በገመል ላይ በጫኑት ጊዜ ገመሉ ከቦታው የማይነሣ ሆነ።

❖ ሁለተኛም በሌላ ገመል ጫኑት እርሱም መነሣትን እምቢ አለ አብዝተውም ደበደቡት ገመሉም ከቶ አልተንቀሳቀሰም እነርሱም ያ ቦታ እግዚአብሔር የፈቀደለት መሆኑን አወቁ ቦታውንም አዘጋጅተው በዚያ ቀበሩት።

❖ ጌታችንም በበግ እስከገለጠው ድረስ ብዙ ዘመናትን በዚያ ቦታ ኖረ ይህም ቤተ ክርስቲያኑ በከበረችበት በሰኔ ዐሥራ አምስት ቀን ተጽፎአል።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

አርኬ
ሰላም ለከ ሐራዊ መስፍን። ሰማዕተ መድኅን። ዘሰመየተከ ሚናስ ዘፆረተከ ማሕፀን። አመ ጸለየት ጸሎተ እንዘ ይእቲ መካን። እምሥዕለ ማርያም ሰሚዓ ዘይቤ አሜን።