2022-05-13 22:14:27
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
አባ አባ ብዬ በለመንኩህ ለቅሶ ተሰምቷል ጩሀቴ
በውን ያስጨነቀኝ ተራራው ፈተና ተነስቷል ከፊቴ
የተማመንኩበት የሥምህ ስንቅነት አንዳች አልጎደለ
ተስፋ ያደረግሁት የጸሎትህ ሥምረት በሕይወቴ አለ
የተደገፍኩበት የደጅህ ዋስ’ነት ሜዳ አልጣለኝም
እንባ የረጨሁበት የ’ስማኝ!’ ዋይታዬ አልወደቀብኝም
ከህጻንነቴ አንተን ተማምኜ የሄድኩበት መንገድ
በጥቅጥቁ ጫካ አንበሳው አልነካኝ አልሆንኩ አልቦ ዘመድ
ልጅነቴ ሁሌ ገብረ ሕይወት እያለች በምልጃህ ተማምና
ትናንት እንዳልተውካት ዛሬም ስትጣራህ ለነፍሴ ጭንቅ ና፡፡
አቡየ አቡየ ብዬ ሀገር አሻግሬ ስምህን እጠራለሁ
ከግብጽ በረሃ ለምትሻህ ኢትዮጵያ ቶሎ ና እላለሁ
ታስፈልጋታለህ እንኳንና ለሰው ለአናብስት ሁሉ
የጽድቅህን ፍሬ የቀመሱ ነፍሳት አባ አባ ይላሉ
የንጽኅናህ ግርማ ከግብጽ እስከ ኢትዮጵያ ሀገር እያወደ
አንበሳውም ነብሩም እያገለገለህ አንተን እያጀበ ካንተ ጋራ ሄደ
አቡዬ ና ድረስ ና ገስግስ ዘንድሮም ቶሎ ና ለሀገሬ
እረፉ በላቸው እንዳይናከሱ ሰውንና አውሬ
ዛሬም ቁም ዝቋላ ግባ ከባህሩ እጆችህን ዘርጋ
ፈልግ ልጆችህን የጸሎት ፍሬህን የጠበቅኸውን መንጋ
ከሰሜን ከደቡብ ከምስራቅ ከምዕራብ የተጋደልህለት
“ኢትዮጵያን ማርልኝ !” ብለህ ከአምላክህ ፊት ብዙ የጸለይክለት
የረገጥከው መሬት ያረፍክበት ደብር የነካህ አፈሩ
ዳግም በዛሬው ቀን ጸሎትህን ይሻል መላው ሀገሩ
ምድረ ከብድ ድረስ ተገኝ በዝቋላ አንሳ እጆችህን
እስከምንጠገን ተሰብረናልና እየን ልጆችህን
አታሳፍረንም ገብረ መንፈስ ቅዱስ ብለን ስንጠራህ
እንግዲህ አቡኤ የኢትዮጵያን ነገር አሁንም አደራህ
የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ግጥሞች እና
ጥቅሶች ቻናል
{{ @orthodox_poem }}
@EOTC_library
@EOTC_library_bot
https://t.me/+YZYAOpgOgns2Njdk
13.5K viewsedited 19:14