Get Mystery Box with random crypto!

❀ ተጣሉብኝ ❀ ༺♱༻ 'ደቂቀ እምየ ተበአሱ በእንቲአየ ⇨ የእናቴ ልጆች ስለእኔ እርስበእር | ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴

❀ ተጣሉብኝ ❀
༺♱༻
"ደቂቀ እምየ ተበአሱ በእንቲአየ ⇨ የእናቴ ልጆች ስለእኔ እርስበእርሳቸው ተጣሉብኝ" (መኃ ፩፥፮)

በዛሬው ዕለት የምናገናቸው የከበሩ የቤተክርስቲያን መብራቶች ቅዱሳን ሰማዕታት ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ በአንድ ወቅት ስለ እናት ቤተክርስቲያን ክብር ተጣልተው እንደነበር! አንድነቷን ለመጠበቅ «ጽና ፣ አትዛል ፣ ፣ ከጥፋት ተመለስ…» ለመባባል በዛ መንድ ሳይሆን በዚህ መንገድ ጥቀማት እያሉ ተጣሉ!

ዛሬስ ለቤተክርስቲያን ሳይሆን በቤተክርስቲያን ላይ የተነሱ አንድነቷን ለማጽናት ሳይሆን ለመክፈል እንቅልፍ የሚያጡ “በዚህ መንገድ ቢሆን ነው ልክ” በሚል ቅንነት ያለው መበላለጥ ሳይሆን «ትክክል አንተ ነህ እኔ አጥፍቻለሁ» የሚል እንኳ ሲገኝ ይቅርታን በማይቀበል ጥመት ጨፍነው «ዘላቂ ጥቅም እንጂ ቋሚ ጠላት የለኝም» የሚለው ፖለቲከኛው እንኳን የሚበልጣቸው «ሃይማኖተኛ» መሳዮች!

ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው ሆኖ እየታመምን እናስታምማለን እንጂ ቁስላችን ሲያመረቅዙና ሕመማችን ሲያብሱማ ተዉ እንላለን! መንጋውን ለመጠበቅ ያልበቁ በመንጋው መጠበቅ የሚገባቸው ስማቸው እረኛ ከሚለው ወርዶ ተረኛ፣ ዘረኛ … በሚል እየተተካካ ቤተክርስቲያንን የሚያቆስሏት የሚያሳምሟት ከማያምን ይልቅ የከፉ እንዲህ ያሉ ገባርያነ እኪት ጸላዕያነ ሠናያት ለጥፋት ሲሮጡ ሔደው ሲለምኗቸው እምቢኝ ካሉ ተለይተው አለመወገዛቸው ፣ ተጠርተው አለመከልከላቸው ነገ የበለጠ ዋጋ ያስከፍለናል!

“ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።” 【1ኛ ጢሞቴዎስ 5፥8】

☞ የቀደሙቱ ጳውሎስና ጴጥሮስ ፣ አፈወርቅና ኤጲፋንዮስ ፣ ተክለሃይማኖትና ኤዎስጣቴዎስ… ስለእኔ እርስ በእርሳቸው ተጣሉብኝ ብላ የምታዝንላቸው ቤተክርስቲያን ነበረችን። ዛሬ ግን ስለእርሷ ሳይሆን በእርሷ ላይ ነውና ታዝንብናለች!

በሁሉ መንገድ ሴራው ቢበቃ፣ ሸፍጥ ቢቆም፣ «እበልጥ አልበለጥ» መባባሉ ብናስቀር ፣ መበሻሸቁን ብናርቅ … «በእነ እገሌ ምክንያት ይኽ ሆነ» ባዮች ወጣ ገባውን አይተን ለአንድነት እንቁም መለያየቱን እናስቁም፤ እድሉ ስላለን «በእኛ ምክንያት ነው ይህ ሁሉ የመጣው» ብለን የምንችለውን ብናደርግ። ባትሹት ግን ሁሉን የሚያስችለው እርሱ ሁሉን ይችላል!

ጌታችን ቅዱስ ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእን ከሊቀ ሐዋርያቱ ቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ወደ አንጾክያ እንዲያስተምሩ ቢልካቸው በዚያ አሕዛብ መከራ አጸኑባቸው ኋላ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ከቅዱስ ዮሐንስ ቢሰማ በአካሔድ መሳታቸውን ፣ ዘይቤ ማጣታቸውን አይቶ ተለያቸው … የአሕዛብን ልብስ ለብሶ ወደሸንጓቸው ገብቶ በፈሊጥ መከረና ከቅዱስ ጴጥሮስ ደርሶ በፊታቸው በጥፊ መታው ፦ ቅዱስ ጴጥሮስ " ተመይጠኑ ጳውሊ ሃበ ቀዳሚ ግብሩ" ብሎ ደነገጠ "እስኪ ሙት ካስነሳ እንመንበት?" ብሎ መክሮ ከሞተ ፫ ወር (መንፈቅ) ያለፈው የንጉሥ ልጅ እንዲያስነሳ ጠየቀላቸው! ሊቀ ሐዋርያት ሲጸልይ ቅዱስ ጳውሎስ ከውጭ፦ በእነርሱ ልብስ፣ ከውስጥ፦ በንጹሕ መንፈስ "ላንተ ብሎ እንጂ እሾም እሸለምበት ብሎ አይደለምና እባክህ ስማው አስነሳለት" እያለ በጥፊ ለመታው ወንድሙ ለመነ ያም ሙት ተነስቶ ያስነሳኝስ ያ ነው ብሎ ቅዱስ ጳውሎስን ጠቁሞላቸዋል በዚህ ነው "የእናቴ ልጆች ስለእኔ እርስበእርሳቸው ተጣሉብኝ" ያለው የተገለጠው!

የዛሬው የጠሉ የተጠሉና የተጣሉ ጥለኞች ለቤተክርስቲያን ምን እንደሚጠቅሟት እንጃ!

በእግራቸው ገስግሰው በእጃቸው ደም አፍሰው የተመለሱትን አጨብጭቦ ይቅር አልኩ ፣ ረሳሁ ፣ ታረቅሁ… ሲለን ያየነው አካል የገዛ አባቶቹን "ይቅርታቸውን አንቀበልም" ብሎ ልብንም በርንም ዘግቶ መጥፋትቱ የይቅርታን ትርጉም በምን እንደተረዳው እንጃ በራሱ መበቀል እግዚአብሔርን መጣል ነውና የበለጠ ቁጣ ይጠራል!

በዜና አበው እንዲህ የሚል ታሪክ አለ፦

አንድ ወንድም ወደ አባ ስልዋኖስ ሄደና "በጣም ክፉ ነገር እያደረሰብኝ ያለና ሊያጣፋኝ የሚፈልገኝ ጠላት አለብኝ:: እንዲገድሉኝም ለመሰርያን(ክፉ አድራጊዋች) ነግሯቸዋልና እንዲያሳርፍልኝና እንዲገስጸው ልነግር ወደ ባለስልጣኑ መሄድ እሻለሁ" አለው ::እርሱም "እ...የመሰለህን አድርግ አለው...." :: ያም ወንድም "እንግዲያውስ ጸልይልኝ" አለውና አብረው ጸሎት ሲያደርሱ "በደላችንን ይቅር በለን እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል" ከሚለው ስፍራ ላይ ሳሉ አባ ስልዋኖስ "በደላችንን ይቅር አትበለን:: እኛም የበደሉንን ይቅር ስለማንል::" አለ:: ያም ወንድም "አባ... ተው እንጂ እንዲህማ አትበል!" ቢለው "ይበቀልልህ ዘንድ ወደ መኮንኑ የምትሄድ ከሆነ ስልዋኖስ ከዚህ ሌላ አይጸልይም" አለው:: ያም እኁ(ወንድም) ይህን ሰምቶ ወደልቡ ቢመለስ ከእግሩ ሥር ተደፍቶ የበደለውን ይቅር አለ::

❀ ሮሜ. 12:19 "ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።"

❀❀ ማቴ. 5:44-45 "እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።"

❀❀❀ ማቴ.6:15 "ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና"

በዚህ አያያዝ ክርስትናችን ምኑ ላይ ነው? እንግዲህ እኛም እንደዚህ እያልን ልንጸልይ ነው "በደላችንን ይቅር አትበለን:: እኛም የበደሉንን ይቅር ስለማንል::"
አቤቱ ማረን ፈሪሃ ኃጢዓትን ፣
ፍቅረ መለኮትን ፣
ተዘክሮ ሞትን … ከእኛ አታርቅብን

☞ ሐምሌ አቦ ፳፻፲፭ ዓ.ም. በቴዎድሮስ በለጠ የተጻፈ።