Get Mystery Box with random crypto!

ምንት አሥሐቃ ለሳራ ?    ሣራ ለምን ሳቀች ?     【ዘፍ. ፲፰፥፲፱】 ▦▦ 〣𓆩⪩♱⪨𓆪 | ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴

ምንት አሥሐቃ ለሳራ ?
   ሣራ ለምን ሳቀች ?
    【ዘፍ. ፲፰፥፲፱】
▦▦ 〣𓆩⪩♱⪨𓆪〣 ▦▦
        የሰው ልጅ ከሌላው ፍጥረት በተለየ በፊት ገጽታው ፣ በአካላዊ ኹኔታው ፣ በቁመናው ፣ በዓይን እንቅስቃሴው ከዚያም ባሻገር በመንካትና በአካል ርሕቀት ጭምር የሚገልጣቸው ሐሳቦች አሉት፤  ታዲያ እኒህ መንገዶች አንዳንዴ ከቃል ንግግር ባልተናነሰ ሳይሆን በተሻለ መንገድ እውነተኛ ስሜትን የመግለጥ ጉልበት ይኖራቸዋል።  የነገረ ሰብእ አጥኚዎች (anthropologist)  ይኽን በአካላዊ እንቅስቃሴና በፊት ገጽታ መልእክት የማስተላለፍ መንገድ ኪኔሲክስ [Kinesics] ብለውታል።

      አንድ መረጃ  ቀጥታ በቃል ሳይነገር  በተዘዋዋሪ መንገድ የስሜት ተረፈ ምርት (emotion residue) በሆነ አካላዊና የገጽታ ኩነት ሲገለጽ  ሐሳቡ እንዴት መተርጎም እንዳለበት ልማዳዊ የጋራ ስምምነቶች ከቦታ ቦታ የሚለያዩ ቢሆንም  በዲበ ተግባቦት (Meta-communication)  ግን የጋራ ትርጉም እንዲሠጣቸው ታሶቦ «እንዲህ የሚኮነው በዚህ ምክንያት ነው» የሚል አስማሚ ትርጉም ይቀመጥላቸዋል።

      ሳቅ ከእነዚህ ውሥጥ አንዱ ነው። በሥሉስ ቅዱስ በኩል ሐይመተ አብርሃም ውሥጥ ለሳራ የቀረበ ጥያቄ አለ ፦  «ምንት አሥሐቃ ለሳራ ☞ ሣራ ለምን ሳቀች?»  በእርግጥ ጥያቄው ሳራ የሳቀችው በምን ምክንያት እንደሆነ ለማወቅ ተፈልጎ የተነገረ ሳይሆን «እንዲህ ተደንቃ የምትስቀው ፣ እጅጉን ተገርማ የምትፈገው ስለምነው? »   ለማለት እንጂ ። “እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች?”  እርሷ ግን ቅሉ ከሐሳብ አስቀድሞ ሁሉን የሚመረምረውን ፣ ከሕሊና አስቀድሞ ሁሉን የሚያውቀውን ልብአውቃ የሆነ ማእምረ ኵሉ  አምላክን ፈርታ ብትክደውም  “ሣራም ስለ ፈራች፦ አልሳቅሁም ስትል ካደች። እርሱም፦ አይደለም፥ ሳቅሽ እንጂ አላት።” (ቁ፲፭)

      ከዚህ ምዕራፍ ቀድሞ በተገለጠው የዘፍጥረት ታሪክ ውሥጥ ራሱን «ኤልሻዳይ» ብሎ ለአብርሃም የገለጠ ልዑል እግዚአብሔር ለይስሐቅ ይስቃል በሚል መጠሪያ መሰየም መነሻው ከነሚስቱ ሸምግሎ በእርግና ሳለ ትወልዳለህ ሲባል የአብርሃም ተገርሞ መሳቅ እንደነበር እናያለን፦
“አብርሃምም በግምባሩ ወደቀ፥ ሳቀም፥ …  እግዚአብሔርም አለ፦ በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ ”  【ዘፍ ፲፯፥፲፯(፲፱)】

         አብርሃምና ሳራን ምን አሳቃቸው?  ደስታ ነዋ! 
⊚⃝⊚ ሰው ሲደሰት ይስቃል (ከውሥጥ ወደ ውጪ)
☞ ያዘነ ሰው ፊቱ ጠቁሮ የተደሰተ ሰው ፊቱ በርቶ መታየቱ ለዚያ ነው  «እምከመ ይቴክዝ ልብ ይዴምን ገጽ እምከመ ይትፌሣሕ ልብ ይበርህ ገጽ» እንዲል
⊚⃝⊚  በሌላ መንገድ ሰው ሲስቅም ይደሰታል (ከውጭ ወደ ውሥጥ)
☞ የተከዙ ሰዎች ወደሳቅ የሚቀርቡት ያዘኑ ሰዎች መዝናናት የሚመርጡት ለዚያ ነው   "ሳቅ የደስታ ምንጭ ነው" እንዲል

ኢያሱ ወልደ አልዓዛር (ወልደ ሲራክ) በመጽሐፉ "እስመ እምራእዩ ይትዐወቅ ሰብእ፣ ወእምገጹ ይትዐወቅ ጠቢብ ⇨ ሰው በመልኩ ይታወቃልና ፣ ጠቢብም በገጹ ይታወቃል"

የተረጋጋ፣ ተስፋ የቆረጠ፣  የታመመ፣ የደከመ ሰው ከቸኮለ(ከሚጣደፍ) ፣ ከበረታ ፣ ከሚጓጓ…  ሰው  የሚለየው በአካሐዱ ነው ፤   
           ያዘነ ከሚደሰት ፣ ወደመኝታ የሚሔድ ወደሥራ ከሚሔ ፣ ወደቤተክርስቲያን የሚሔድ ከማይሔድ…  በአለባበሱ እንደሚታወቅ። ሳቅም ከአካሔድና ከለባበስ በበለጠ የአንድን ሰው አሁናዊ ሁኔታ በተሻለ መልክ ያስረዳል፤ በ‘ኢሞጂ’ ውሥጥ የፈገግታ ገጽ / የሳቅ ፊት (smiley face) አንዱ የደስታ ስሜን ወኪል ሥዕላዊ ምልክት (ideogram)  ተቀምጧል።  

«ወእምልብሰቱ ለሰብእ ወእምሑረቱ ወእምሠሐቁ ይትዐወቅ ግዕዙ  ⇨ ካለባበሱና ካካሄዱ ከአሳሣቁም የተነሣ የሰው ጠባዩ ይታወቃል» 【ሲራ ፲፱፥፳፯(፴)】

እንዲያውም  አንዳንዴ ሳቅ ከቁጥጥር ውጪ ‘እየገነፈለ’ የደስታን ስሜት የውሥጥን ሐሴት በሌላው ፊት ያሳብቃል፤ እንደ ሳራ! ታዲያ  ፎቶ አንሺ ፣ ቪዲዮ ቀራጭ ፣ ሠዓሊ… መታወሻ  ምስልን ለማስቀረት ሲሻ "እስኪ ፈገግ በሉ" ማለቱ ቅሉ ለዚህ ነው "ፍሡሓ ገጽ" ሆኖ መታየት የደስተኝነት መገለጫ ነውና።

          አቡነ ኤርምያስንስ ምን አሳቃቸው?
አቡነ ኤርምያስን በሐዘን ፊት ፣ በተቋጠረ ገጽ ፣ በዝቶ በሚፈሰው እንባ ፣ በተከዘ ልብ የማያውቃቸው የለም! «ጦርነት» በተባለው እርስበእርስ ፍጅት ከህዝበ ክርስቲያኑ ጋር የመከራውን ጽዋዕ ቀምሰዋል እንደቀደመው ኤርምያስ
ቅዱስ ቀሌምንጦስ ዘሮም  " ካህኑ ኤርምያስ ከሕዝበ እሥራኤል ጋር አብሮ የተሠደደው እስራኤሎችን ቃለእግዚአብሔር እንዲያስታውሳቸው ነው።" ብሏል! 

         እና ዛሬ ምን ተገኝቶ እንዲህ ይስቃሉ? 
“የእግዚአብሔርም ደስታ ኃይላችሁ ነውና አትዘኑ” 【ነህ ፰፥፲】
እንደሳራ ትውልዱ ላይ ተስፋ ፈንጥቆ የበረከት ዘር ሲተካላቸው  በመካን ማሕጸን ፍሬ ቢታያቸው ገጻቸው በርቶ ፊታቸው ፈክቶ ታይቷል!  በሀገሬ ቲቪ የቀረበው የዶንኪ ቲዩብ ድንቅ ልጆች መሰናዶ በዚህ ሳምንት በደስታ የሚስቁ በሐሤት የሚፍለቀለቁ አቡነ ኤርምያስን ደጋግሞ አሳይቶናል። ዐይናቸው ውሥጥ አንድ ሕፃን ሶልያና ተፈራ ብቻ ሳትሆን  የብዙ ተተኪ አዳጊ ዜጎች ተስፋ ይታያል!  [

]

     ፈለገ አእምሮ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በአቡነ ኤርምያስ ራእይ የታነጸው    “ታላላቅ ካቴድራሎችን ገንብተን በውስጡ አገልጋይ ከሚጠፋ አብነት ት/ቤቶችን ገንብተን እንደጥንቱ በድንኳን ብንገለገል ይሻለናል” በሚል ኃይለ ቃል እንዲህ ያለውን ፍሬ ለማየት ነበር።  ዛሬ ግን የባሰ ሌላ ችግር በሀገረ ስብከቱ ተጋርጧል፤

     ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ (ዶ/ር ) የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የበላይ ጠባቂ በሀገራችን «በወንድማማቾች መኻል ተከስቶ በነበረው እርስ በእርስ ግጭት» የደረሰውን ውድመት ተከትሎ እሑድ ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚሌኒየም አደራሽ ከቀኑ 6፡oo ጀምሮ የወደቀችዋን ድንኳን ለማንሳት ፣ የተናደውን ቅጥር ለመጠገን ፣ የፈረሰውን ለማደስና እንደቀድሞው ዘመን ለመሥራት ማንም የማይቀርበት ታላቅ መንፈሳዊ ጥሪ እንዲህ ሲሉ ለቤተክርስቲያን ልጆች አስተላልፈዋል፦
‹‹የክርስትናው ሀዲድ ተሰብሮ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ እንዳይቋረጥ ሃይማኖታዊ ግዴታችሁን ትወጡ ዘንድ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም አሳስባለሁ፡፡››

«ንሕነኒ ውስተ ሐይላ ንደይ ልበነ ንዴግና ወንበላ በሐ  ወትረ ንሳለማ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ☞ እኛም በቤተክርስቲያን  ኃይል ልቡናችንን እንጨምር እንከተላት ሰላምም እንበላት» 【መጽሐፈ ቀሌምንጦስ ፲፩፥፶】

✞ ቴዎድሮስ በለጠ ✞ ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ከፍራንክፈርት