Get Mystery Box with random crypto!

የደስተኝነት ምንጭ ምንጭ ፦ ደስታን የማግኘት ጥበብ ትርጉም ፦ ዳኜ መላኩ ህይወት ባልተጠበቁ ድ | ኑ እናንብብ

የደስተኝነት ምንጭ

ምንጭ ፦ ደስታን የማግኘት ጥበብ
ትርጉም ፦ ዳኜ መላኩ

ህይወት ባልተጠበቁ ድንገተኛ አጋጣሚዎች የተሞላች ሂደት ነች፡፡ ደስታም ሆነ ሀዘን ባልተጠበቀ መልኩ ወደ ህይወታችን ሰተት ይላል፡፡ ድንገተኛ እድልና ብልጽግና ሲመጣ ልቦናችን በጊዜያዊ ሀሴትና ፌሽታ ይወጠራል፡፡ በተቃራኒው ድንገተኛ አደጋ በህይወታችን ላይ ሲያንዣብብ አንዳች ረብሻና ስሜታዊ ድንዛዜ በውስጣችን ይነግሳል። ይሁን እንጂ ጊዜያዊው ፌሽታም ሆነ ስቃይ በውስጣችን እንደተቀመጠ የሚጸና አይደለም፡፡ ሰው በተፈጥሮው ነገራትን በፍጥነት የሚዛመድ ፍጡር በመሆኑ ከስኬቱም ሆነ ከውድቀቱ በቀላሉ ይላመዳል። ፈጠነም ዘገየ ድንገት የተከሰተው ሀሴትም ሆነ ሀዘን ተንኖ ወደተለመደው የስሜት ይዞታ መመለሳችን አይቀሬ ይሆናል፡፡

ይህ ነገራትን የመላመድ ተፈጥሯችን በእለት ተእለት ህይወታችን ውስጥ ሳያቋርጥ የሚስተዋል ክስተት ነው፡፡ የደሞዝ ጭማሪ ሊደረግልን፣ አዲስ መኪና ወይ ቤት ስንገዛ ወይም አዲስ ፍቅረኛ ስንተዋወቅ ለተወሰኑ ሳምንታት
ስሜታችን በሀሴት ይሞላል። ህይወታችን በአዲስ መልኩ የታደሰ ይመስለናል፡፡ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ይህ የህይወት ወረት ቀስ በቀስ እየተቀዛቀዘ ሄዶ ወደተለመደው የስሜት ይዞታ እንመለሳለን፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ህይወት የተገላቢጦሽ ትሆናለች፡፡ ምናልባት የእለት ተእለት ገቢያችን ይመናመናል፣ ከወዳጅ ባልደረቦች እንጋጫለን ወይም በሆነ አይነት ችጋርና መከራ እንከበባላን። እናም በሀዘንና ትካዜ መንፈሳችን ይታወካል። ሆኖም ከተወሰነ ቆይታ በኃላ ነገራት ቀስ በቀስ እየቀለሉ ወይም ከእውነታው እየተላመድን ስንሄድ መንፈሳችን ታድሶ ውስጣችን ይደረጃል፡፡

ከጊዜያዊ ስሜቶቻችን ባሻገር ሁሌም ወደተለመደው የህይወት መስመር የምንመለስ ከሆነ « በርግጥ መሰረታዊውን የደስተኝነት ባህሪ የሚወሰነው ምንድን ነው?” የሚል መሰረታዊ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።

በመስኩ ላይ ጥናት ያደረጉ የስነ ልቦና ተመራማሪዎች እንደሚገልጹት የሰዎች ባህሪ በብዙ መልኩ ከወላጆቻቸው በሚወርሱት ጂን ወይም ስነ ህይወታዊ ዘረ-መል የሚወሰን እንደሆነ አንዳንድ ሰዎች በቀላሉ የመደሰት ተፈጥሮ ሲኖራቸው፣ አንዳንዶች በተቃራኒው
ጭንቀትና ድብርትን የሚገፋፋ ባህሪ ይዘው ይፈጠራሉ፡፡ የተለያየ ቦታ ተራርቀው በሚኖሩ መንትዮች ላይ የተደረገ የባህሪ ጥናቶች እንዳመለከቱት ከአስተዳደግና ከባቢያዊ ሁናቴዎች በተለየ መልኩ የሰዎች ስነ-ህይወታዊ ዘረ-መል የደስታና የጭንቀት ባህሪያቸውን እንደሚወስን ጠቁመዋል፡፡

ከወላጆች የምንወርሰው ተፈጥሯዊ ባህሪ በስብዕናችን ላይ መልከ- ብዙ ተጽእኖ እንደሚኖረው እሙን ቢሆንም፣ አእምሯችንንና አመለካከታችንን በመለወጥ የደስተኝነት ስሜትና ባህሪያችንን ማሻሻል እንደምንችል የስነ ልቦና ባለሞያዎቹ ይገልጻሉ፡፡

በርግጥ ለደስተኝነትም ሆነ ለደስታ ማጣት መሰረታዊው መንስኤ ሁኔታዎችን የምንመለከትበት መንገድ ነው፡፡ በህይወታችን ውስጥ ከሚከሰቱ አጋጣሚዎች በላቀ አጋጣሚዎቹን የምንመለከትበት መንገድ ውስጣዊ ስሜታችንን ይወስነዋል።

ደስታን የመሻት መሰረቱ ውስጣዊ አመለካከትና ባለን ነገር የመርካት ልምድ ነው።

እራስን ማነጻጸር

በውድድር በተሞላ ማህበራዊ ስርአት ውስጥ እንደማደጋችን ከህይወት የምናገኘው እርካታ እራሳችንን አነጻጽረን በምናገኘው ውጤት ላይ የተመሰረተ ነው። ያለንበት ደረጃ በፊት ከነበርንበት የተሻለ ሆኖ ሲገኝ ደስታ ይሰማናል። ካለፈው በባሰ ሁኔታ ላይ የምንገኝ መስሎ በታየን ቁጥር ደግሞ በራሳችን እንከፋለን፡፡ አመታዊ ገቢያችን ከሀያ ወደ ሰላሳ ሺህ ሊያድግ ደስተኛ እንሆናለን፡፡ ሆኖም ከጥቂት ወራት በኋላ ስሳሳው አንሶን አርባ ሺህ መመኘት ስንጀምር በርግጥ የህይወት እርካታ በአመታዊ ገቢያችን ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡

የውድድር አባዜው የራሳችንን ህይወት በማነጻጸር ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ከራሳችን ባለፈ በዙሪያችን ያሉ ወዳጅ ባልደረባዎቻችንን እንፈካከራለን። ያገኘነውን ያህል ብናገኝ ጎረቤታችን የተሻለ ካገኘ በገቢያችን ደስተኛ አንሆንም፡፡ በአመት ሁለት ሶስት ሚሊዮን የሚያገኙ ፕሮፌሽናል አትሌቶች ሳይቀሩ ሌሎች ከፍተኛ ተከፋዮችን እየጠቀሱ ገቢያቸውን ያማራሉ። በርግጥ ኤች.ኤል. ማንኬን በአንድ ወቅት ‹‹ሀብታም ማን ነው›› ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹የሚስቱን እህት ባል በመቶ ዶላር የሚበልጥ ሰው ሁሉ ሀብታም ነው›› ብሎ ነበር፡፡

እራሳችንን ከቢጤዎቻችን የምናወዳድረው በገቢ ወይም በሀብት ብቻ አይደለም፡፡ በመልክ፣ በትምህርት ደረጃ፣ በትዳር፣ በቤታችን ስፋት... በማንኛውም ረገድ እራሳችንን ከሌሎች እናነጻጽራለን፡፡ እናም ደስታና እርካታችን በዚህ የንጽጽር ውጤት ላይ የተመሰረተ ይሆናል፡፡ ከህይወት የምናገኘው እርካታ በራሳችን ማንነት ሳይሆን በምንፎካከራቸው ሰዎች ማንነትና የኑሮ ደረጃ የሚወሰን ነው። በመልክ ወይም በአስተሳሰብ ከራሳችን የተሻሉ ሰዎች ስንመለከት ወይም ከእኛ በተሻለ ስኬታማ የሆነ ሰዎች ስናይ የቅናትና ደስታ የማጣት ስሜት ይወረናል፡፡

ደግሞም እራሳችንን የምናነጻጽረው ከሚበልጡን፣ ቢያንስ ከሚመጣጠኑን ሰዎች እንጂ ከሚያንሱን ጋር አይደለም፡፡ ምናልባት ከእኛ ከፍ ያሉትን ትተን ዝቅ ብለው የሚገኙትን ብንመለከት ህይወት የሰጠችንን ገጸ በረከት አመስግነን እንቀበል ነበር፡፡ ከእኛ የከፋ የህይወት እጣ ፈንታ የወደቀባቸውን ሰዎች ብንመለከት በርግጥ ባለን ነገር መርካት፣ በህይወታችን መደሰት እንጀምር ነበር፡፡

@Zephilosophy
@Zephilosophy