Get Mystery Box with random crypto!

ራስን ማታለል (Bad Faith) በሕይወትህ ለምን ያህል ጊዜ ለውድቀትህ ሌሎች ሰዎችን ወይም ሁነ | ኑ እናንብብ

ራስን ማታለል (Bad Faith)

በሕይወትህ ለምን ያህል ጊዜ ለውድቀትህ ሌሎች ሰዎችን ወይም ሁነቶችን ወቅሰህ ታውቃለህ? እንዲህ ባይሆን ኖሮ እንዲህ እሆን ነበር' ብለህስ ታውቃለህ? አለቃህ፣ መምህራኖችህ፣ ወላጆችህ የሆነ ነገር እንድታደርግ አስገድደውህ ያውቃሉ?

የሃያኛው ክ/ዘመን ፈላስፋ የሆነው ዣን ፖል ሳርት እነዚህን ሃሳቦች በአንድ ሰብስቦ “bad faith' ብሎ ይጠራቸዋል። ይህም ራስን ማታለልን ያመላክታል። ብዙውን ጊዜ በሕይወት ላይ አማራጭ እንደሌለን ለራሳችን እናሳምነዋለን፡፡ ይህን ያደርግነው እንዲህ ስለሆነ ነው የሚል ምክንያትም ከድርጊቶቻችን ጀርባ እናስቀምጣለን። አሁን ላለንበት ደረጃ ያበቁንን አስገዳጅ ምክንያቶች እና ሰበቦች እንደረድራለን፡፡ ራስን ማታለል በዙሪያችን እስር ቤት የመገንባት ያህል ነው።

ማህበረሰቡ ባስቀመጠልን አስገዳጅ ህጎች አልያም ልማዶች ራሳችንን ወስነን በነጻነት ከመምረጥ እንገደባለን፡፡ ለምሳሌ ሜሴጅ እንደላከልሽ ወዲያውኑ አትመልሽለት” አይነት ተራ ሕጎች ጀምሮ እስከ በዳኛ የተደነገጉ ሕጎች ድረስ - የመምረጥ ነጻነታችን ይገደባል።

እናም ራስን ማታለል (bad faith) የሚጀምረው ለውድቀታችን እነዚህን ህጎች ተጠያቂ ስናደርግና በእነርሱ ውስጥ ስንሸሸግ ነው::

እናም ከማህበረሰቡ ተውስን የምንወስዳቸው ብዙ ጭንብሎች አሉን፡፡ በብዙ የሕይወት ክፍሎቻችን ላይ እንዲህ መሆን አለብህ ስለተባልን ልክ እንደ ተዋናይ ሆነን እንተውናለን፡፡
ነገር ግን ይለናል ሳርት፤ ህግ፣ ደንብ፣ ባህል እና ወዘተ... ከመምረጥ አያግዱንም፡፡ ምርጫዎችን የመምረጥ እና የመወሰን ፈቃዱም በእኛ እጅ ላይ ነው ያለው፡፡

በእያንዳንዷ ቅጽበት፣ በእያንዳንዱ ቀን ምርጫዎች አሉን። በእያንዳንዱ ሰከንድም የወደድነውን የመምረጥ ነጻነት አለን። ይህንን ነፃነት ምንም አይነት ነገር ከእኛ ሊቀማን አይችልም፡፡ ነጻ ለመሆንም የተገባን ነን።

በዚሁ ልክም ለእያንዳንዱ ምርጫዎቻችን ውጤት የምንጠየቀው እኛ ብቻ ነን። ቀድሞውኑ በሚገባ አመዛዝነን ካልወሰንን እና መንገዳችን ወደ መጥፎ መዳረሻ ካደረሰን፣ ከእኛ ውጪ ልንከሰው የሚገባ አካል አይኖርም፡፡ ጥፋታችንንም ከማመን ውጪ ማንም ላይ ማላከክ የለብንም፡፡

ነጻ ነህ ... ነጻነትህን ተጠቅመህ መንገድህን ምረጥ...

ምንጭ-ፍልስፍና ከዘርዓ ያዕቆብ እስከ ሶቅራጠስ
ዝግጅት-ፍሉይ አለም

@Zephilosophy
@Zephilosophy