Get Mystery Box with random crypto!

ጤና የለንም “ሁሉ በሽተኛ ሁሉ ራሴን ባይ ከቤታችን ደህና መጥፋቱ ነው ወይ” የትልቅ ነገር ክ | Nolawi ኖላዊ ኄር

ጤና የለንም

“ሁሉ በሽተኛ ሁሉ ራሴን ባይ
ከቤታችን ደህና መጥፋቱ ነው ወይ”

የትልቅ ነገር ክብረት የትንንሽ ነገር ቅለት ነው ። ጤና እስካለ የከበዱ ጤና ሲጎድል የረከሱ ነገሮች ለመኖራቸው ትናንታችን ምስክር ዛሬያችን ዋስትና ነው ። የመውጣትን ያህል መግባትን ስናስብ የመድረስን ያህል መጀመርን አንወድም ። የትናንቱ የሀገራችን መልካምና ክፉ ታሪክ ውስጥ ጠልቀን ስንገባ በክፉ ታሪክ ላይ መልካም ታሪክን ያጎሉ በመልካም ታሪክ ክፉ ታሪክን የሻሩ አባቶቾ እንዳሉ እንገነዘባለን ። በዚህ ውስጥ የምንረዳው ነገር ክፉ በክፋቱ ሲበረታ ከሚከተለው ባላይ የሚተቸው እንደነበረ ፤ መልካሙ ለትውልድ ሲጥር ተተኪነትን የሚወድ ሕዝብ እንደነበረን ለመረዳት በልብ ሀገር ሀገሬ ኢትዮጵያን መጎበኝት በቂ ነው ። ክፉ ነገር ዜና የሆነበት ዘመን ይህ  የእኛ ዘመን ነው ። ለክፉ ዜና ጆሮ ከመስጠት መልካሙን ለመሥራትና ለማድመጥ ጥረት ማድረግ የክፋቱን ምንጭ መድፈን ባይቻል እንኳ ከርዕሰ አደባባይ መሻር ይቻላል ።   በርግጥ ዘመን እኛ የሆነውን ነው የሚሆነው ። ይህ ''ክፉ" ዘመን የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ ። ክፉ ግን ሕዝቡ እንጂ ዘመን አይደለም ። ዘመን እንደኛ ነው የሆነውን ይሆናል ። አህያ ሰርዶ አብቅላ ብትመገብ ለማለቁ አትሰስትም ። የምትሳሳው ከመብላቷ በላይ ለማብቀል ነው ። የማዕዷ ፍቃድ ከአምላክ ዘንድ ነውና ይህን አቋም ግን የላትም ። ልክ እንዲሁ ሕዝባችን የመረጃ ሆኖ የሚታረድ በዛ ።  ሕዝቡ ከምሕረት አደባባይ ወርዶ ለቂም በቀል ንቁ ሆነ ። መረጃ መታረጃ ሆኖልንም ልንሰማው ያልወደድነው አንድ ድምፅ አለ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው ። ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ የ activists መረጃ ልባችንን ገዝቶታል ፣ ከቤተክርስቲያን ዓውደምሕረት   ይልቅ የፖለቲከኞች የጹሑፍ  መድረክ ዓይናችንን ማርኮታል ። ከመምሕረነ ወንጌል ትምህርት ይልቅ የጎሰኞች መንደር እግራችንን መርቶታል ። ከመንፈሳዊያን  አባቶች ምክር ይልቅ የአዝማሪዎች ውሸት ልባችንን ደልሎታል ። ከሀገር ሽማግሌዎች መሪነት ይልቅ ለዘረኞች ጄኔራል ተግዘተናል ። ወገኖቼ  በዘመኑ ውስጥ እኔ አንድ ዘመን ነኝ ማለት አለብን ። ዘመን ትርጉሙ ፦ የታደሰ ፣ ልቆ ያለ ፣ የተሻለ ፣ የሚበልጥ ፣ ከሆነ በላይ የሆነ ፣ ከመሰለው ባለይ የመሰለ ፣ ከሚሰራው በላይ የሚሠራ ማልት ነው ። ዘመን የታደሰ ሆኖ በእኛ አርጅቷል ፣ ዘመን የሚልቅ ሆኖ በእኛ ተዋርዷል ፣ ዘመን የተሻለ ሆኖ በእኛ መክኗል ፣ ዘመን የሚበልጥ ሆኖ በእኛ አንሷል ። በተሻለው ዘመን ተሽሎ መገኘት በሚበልጠው ዛሬ ልቆ ከፍ ማልት ያስፈልገናል ። የዘመን ሰጪው ግን ጌታ ነውና ካላከበሩት ያዋርዳል ። ከትልቁ እግዚአብሔር የተቀበልነው ትንሽ ነገር የለም ። ዘመንም የመድኃፉ ብርሃን ነውና ዘመኑን እንደሆነው ከምናደርገው ሊያረገን የወደደውን ብንሆን እግዚአብሔር ይደሰታል ። ዘመንን እንደ ዘፈኑ ፣ ዘመንን እንደ ዜናው ፣ ዘመንን እንደ ስሜታችን ፣ ዘመንን በአሉ ፣ ዘመንን በግዴለሽነት መቀበል የዕለት ተግባራችን ሆኗል ። በዚህ ምክነያት ከእግር እስከ ራስ ታመናል ። አባት በብልጫው ፣ ሽማግሌ በክብሩ የማይከበሩባት ሀገር ሀገሬ  ኢትዮጵያ ናት ። መምህራን በእውቀታቸው ፣ ጠቢባን በጥበባቸው ፣ ድሆች በጉልበታቸው ማዋያ ያጡጧባት ሀገር ሀገሬ ኢትዮጵያ ናት ። ጳጳሳት በመሪነታቸው ፣ ቀሳውስት በመስቀላቸው ፣ ዲያቆናት በትሕትናቸው ሥፍራ ያጡባት ሀገር ሀገሬ ኢትዮጵያ ናት ። ለእውነት ያደሩ የሚገፉባት የውሻት ባለሟሎች የሚሾባት ሀገር ሀገሬ ኢትዮጵያ  ናት ። አስታራቂን የሚተች ገዳይን የሚያሞግስ ወገኔ ታሟል ።  ይቅርታን የራቀ ሰይፍን የመዘዘ ወገኔ ጤና አጥቷሎ ።


የሀገራችን ኢትዮጵያ ጉዳይ ሲያስለቅሰን እንደ መንፈሳዊ ግን ተስፋ እናደርጋለን ። አዎ ወገኖቼ የሀገራችን ጉዳይ አስለቃሽ እና ልብን የሚሰብር ነው ። ሀገር ማለት ሰው ስው ማለት ሀገር ነው ። ሰው ይታመማል ሀገርም ይታመማል ። ሰው ይወድቃል ሀገርም ይወድቃል ። ሰው ይሞታል ሀገርም አንድአንድ ጊዜ ይሞታል ። በማይደፈር ቅጥራቸው እና በሕንፃ ጥበባቸው የከበሩ ዛሬ ግን ደብዛቸው ጠፍቶ በበረሃ አሸዋ የተዋጡ ብዙ ሀገራትን እናውቃለን ።  የነቢዩ የኢሳይያስ ትንቢት የዛሬዋን ኢትዮጵያ አቋም ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ። ቃሉን ልብ እንበል “ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፤ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፤ አልፈረጠም፥ አልተጠገነም፥ በዘይትም አልለዘበም።” ( ኢሳይያስ 1፥6 ) ። በዚህ ቃል ውስጥ የዛራዋን ኢትዮጵያ ብንፈልጋት የምናገኛት በምን ሥፍራ ነው ቢሉ ፦

“ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም አለ ነብዩ ፦ ማለትም ከሕዝብ እስከ መንግሥት ታመናል እንደ ማለት  ነው ። አዎ ወገኖቼ ሕዝብ እንደ ዜጋ አይኖርም ፤ መንግሥትም እንደ መሪነቱ አይከበርም ። ለሚመራው ሕዝብ የማይራራ ለመረጠው መንግሥት የማይገዛ ሕዝብ መቼም ሰላም የለውም  ። ባሳለፍነው ዘመን ውስጥ መሪዎች ክብራቸው በጣሞ የላቀ ነው ። እንደውም ጃንሆይ ወደ ደበረዘይት አከባቢ ሔደው አንዲት እናትን ሰላም ብለው ጨበጡ እነዛ እናት ታዲያ ቀኝ እጃቸውን በነጭ ሻሽ ጠምጥመው ንጉሦ በጨበጠ እጄ ሰው አሰጨብጥም እያሉ እንደ ነበሩ ታሪክ ያወጋናል  ። መሪ ይህን ያህል የሚከበርባት ሀገር ነበረችን ። ዛሬ ከደቂቅ እስከ ሊቅ መንግሥትን የሚሳደብ ነው ። ወገኖቼ መሪ ማለት አቅጣጫ ጠቋሚ ብቻ አይደለም ራሱ ግን አቅጣጫም ነው እንጂ ። መንግሥትን የማያከብር ህዝብ ሕዝቡን የማያከበር መንግሥት ዙፋኑ የረገረገ ነው ። አዎ ወገኖቼ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ላይ የምናየው ውርደት ይህ ነው ። ከሕፃን እስከ ትልቅ መንግሥትን የሚሳደብ ሕዝብ ነው ። ለመከፋፈል የጨከነ ነጌን የማያስብ ሕዝብ ሆነናል ። ወገኖቼ በልኩ መንገድ ስንሄድ የሚገባን ነገር ተስፋችን መሪዎቻችን እንዳልሆኑ ነው ። ተስፈኛ ተስፋ አይሆንም ። በዚህ መክንያት መንግስትን ከመስደብ እና ቀሎ ከመገኘት መጸለይ መልካም ነው ። እኛ መንግሥትን ከመናገር ይልቅ  ለመተቸት ቅርብ ነን ። በዚህ ምክንያት ነው ከልጅ እስከ አዋቂ ጤና ያጣነው ። ለመንግሥታት ከመጸለይ ይልቅ ብንሰድባቸው ይቀናናል ። ከዚህ በላይ በሽታ አለ ? ከዚህ ባላይ መታመም አለ ? እግዚአብሔር ያስበን ! ። ወገኖቼ ዝም ብላችሁ ጤና አትጡ መንግሥትን በዙፋኑ ያስቀመጠ የእናንተ የመርጫ ወረቀት አይደለም ። መንግሥትን መንግሥት ያረገው እግዚአብሔር ነው ። ስለዚህ የእኛ ድርሻ መጸለይ ነው ። የሚጸልይ ሕዝብ ይባረካል  ። ከሊቅ እስከ ደቂቅ የታመምን ሕዝቦች ነን ። እንኳን ለእግዚአብሔር ለሰለጠኑ ሀገራት የማይመጥን ማንነት እያካበትን ነው ። አዎ ኢትዮጵያን በዘፈን የሚወዳት እንጂ በተግባር የሚወዳት ወገን አጥተናል ።

“ሁሉ በሽተኛ ሁሉ ራሴን ባይ
ከቤታችን ደህና መጥፋቱ ነው ወይ”

የተባለው ለዚህ ነው ። ሁሉ በሽተኛ ከሆነ ማን ሊያክም ነው ? ሁሉ እኔን ባይ ከሆነ ድሆችን የሚያስብ ማነው ? አረ አስተውሉ ይህ ጉዞ ጨለማ ነው ። አረ ተመለሱ ወንድም ወንድሙን አሸንፎ አያውቅም !? አረ መንገድ ተስቷል ወንድምን ገድሎ ሹመት የለም !? ። ለኢትዮጵያ ወይ ሸክም አቅልሉላት ወይ ሸክም አትሁኑባት ። ይህን የጤና ጠንቅ መገደብ የሚቻለው ቢያንስ አንድ ሰው ከእኔነት ሲድን ነው ። ኢትዮጵያን ማዳን ባትችሉ እንኳ ሕመሟ አትሁኑ ።