Get Mystery Box with random crypto!

ንቁ ክርስቲያኖች- WAKE UP CHRISTIANS

የቴሌግራም ቻናል አርማ nkuchristeyanoch — ንቁ ክርስቲያኖች- WAKE UP CHRISTIANS
የቴሌግራም ቻናል አርማ nkuchristeyanoch — ንቁ ክርስቲያኖች- WAKE UP CHRISTIANS
የሰርጥ አድራሻ: @nkuchristeyanoch
ምድቦች: ያልተመደበ
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 1.16K
የሰርጥ መግለጫ

🙏በዝህ ቻናል የተለያዩ የማንቅያ መልእክቶችን🙏
🙏ተቀሚ ፅሑፎችንም መፃህፍቶችን ያገኛሉ 🙏
🙏እንዲሁም ዝማሬዎችን ስብከቶችን ያገኛሉ 🙏
🙏ይቀላቀላሉን🙏
🙏እንዲሁም ባለማህተቦችን ጋብዙ 🙏
የቻናሉ መወያያ ግሩፕ link 👇
https://t.me/yenkuchirsteyanochgroup

Ratings & Reviews

3.50

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

1

3 stars

1

2 stars

0

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች

2022-09-01 09:23:36
''በከፍተኛ ቁጣ የተሞላ ሰው ራሱን ይገድላል። ይህ ሰው ለስህተት ተጠያቂ የሆነና ደካማ ጤንነት ያለው ሰው ነው። ጢስ ንቦችን ከቀፎአቸው እንደሚያስወጣቸው ቁጣም እውቀትን ከልብ ያስወጣል።''

ቅዱስ ኤፍሬም
509 views06:23
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-30 06:59:59
117 views03:59
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-30 06:59:09 የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ዕረፍት

ቅዱሳን ጻድቃን በሕይወተ ሥጋ እያሉ፣ ከሞቱም በኋላ (በዐጸደ ነፍስ ኾነው) በጸሎታቸው ለሚታመኑ፤ በቃል ኪዳናቸው ለሚማጸኑ ምእመናን የድኅነተ ሥጋ፣ የድኅነት ነፍስ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ቅዱሳን ጻድቃን በመንፈሳዊ አርአያነታቸው፣ በጸሎታቸውና በትምህርታቸው ከከበቡን የነፍስ ጠላቶች፤ ከርኲሳን መናፍስትና ከጨለማው ልጆች፤ ከክፉ ሰዎች ሽንገላና ተንኰል ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት ሥልጣን ምን ጊዜም ይሠራል፡፡ በጻድቃን መኖር አገር ከጥፋት ትድናለች፡፡ የጻድቃንን ስም ጠርቶ እግዚአብሔርን በመለመን በረከትና ረድኤት ይገኛል፡፡ ስለ ጻድቃን ብሎ እግዚአብሔር ምሕረቱን ያድላል፡፡ ጻድቃንን ማሰብ፣ ሥራቸውንም መዘከር ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ያጐለምስልናል፡፡ በነፍስ በሥጋም ይጠብቀናል፤ ይረባናል፤ ይጠቅመናል፡፡ ስለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቃንን እንድናስባቸው፤ በስማቸውም ለድሆችና ለጦም አዳሮች እንድንመጸውት፤ መታሰቢያቸውንም እንድናደርግ የምትመክረን፣ የምታስተምረን፡፡ ከእነዚህ ቅዱሳን መካከል መካከል ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንዱ ናቸው፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ፤ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ብሥራት ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብ እና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኃረያ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፲፪፻፲፪ (1212) ዓ.ም በቡልጋ አውራጃ ኢቲሳ በሚባል ቦታ ተወለዱ፡፡ (ቦታው በአሁኑ ሰዓት ደብረ ጽላልሽ ኢቲሳ ተክለ ሃይማኖት ተብሎ ይጠራል)፡፡ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን እሑድ ከጠዋቱ በሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ በተወለዱ በ፲፭ ዓመታቸው መዓርገ ዲቊናን፤ በ፳፪ ዓመታቸው ደግሞ መዓርገ ቅስናን ከግብጻዊው ጳጳስ አባ ጌርሎስ (ቄርሎስ) ተቀብለዋል፡፡
ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም ‹ፍሥሐ ጽዮን› ነው፡፡ በአንድ ወቅት ሕፃኑ ፍሥሐ ጽዮን ወደ ጫካ ለአደን ሔዱ፡፡ በዚያች ዕለት ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ጸጋ መንፈስ ቅዱን አሳደረባቸው፡፡ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ወንጌል ወዳልተዳረሰበት ቦታ እንደሚልካቸውም አስረዳቸው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ከአውሬ አዳኝነት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስ እንደ ተመረጡ፤ አጋንንትን የማውጣት፣ ተአምራትን የማድረግ ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው፤ ስማቸውም ‹ተክለ ሃይማኖት› እንደሚባል፤ ትርጓሜውም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት እንደ ኾነ አበሠራቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ያላቸውን ንብረት ዅሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው ‹‹አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደ ተከፈተ ተውኹልህ›› በማለት ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናትንም አሳንጸዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በደብረ ሊባኖስ ገዳም (ገዳመ አስቦ) ዋሻ በመግባትም ሁለቱን በፊት፣ ሁለቱን በኋላ ሁለቱን በቀኝ፣ ሁለቱን በግራ ስምንት ጦሮችን ተክለው እጆቻቸውን በትእምርተ መስቀል በመዘርጋት የክርስቶስን ሕማም፣ ሞትና ነገረ መስቀል በማሰብ በተመስጦ ሌሊትና ቀን ያለ ማቋረጥ በጾም፣ በጸሎት ተወስነው ሲጋደሉ፤ ከቊመት ብዛት የተነሣ በ፺፪ኛ ዓመታቸው ጥር ፬ ቀን ፲፪፻፹፱ (1289) ዓ.ም አንዲቱ የእግራቸው አገዳ ተሰብራለች፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የመንፈሳዊ አባታቸውን ስባረ ዐፅም (የዐፅም ስባሪ) አክብረው በሥርዓት አኑረዋታል፡፡ እግራቸው እስኪሰበር የቆዩባቸው ዓመታትም ፳፪ ናቸው፡፡ ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው ቆመው ያለ ምግብና ያለ ውኃ በትኅርምት ሌሊትና ቀን እንደ ምሰሶ ጸንተው በትጋት ለሰው ዘር ዅሉ ድኅነትን ሲለምኑ ኖረዋል፡፡ ከሰባቱ ዓመታት ውስጥ ጥቂት ውኃ የቀመሱት በአራተኛው ዓመት ብቻ እንደ ነበረ መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡
ጻድቁ አባታችን ምድራዊ ሕይወታቸውን በተጋድሎና በሐዋርያዊ አገልግሎት ከፈጸሙ በኋላ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ የሚያልፉበት ቀን ተቃረበ፡፡ በዚህ ጊዜ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ወደ እርሳቸው በመምጣት የሚያርፉበት ዕለት መድረሱን ነገራቸው፡፡ የተጋድሏቸውን ጽናት አድንቆ በስማቸው መታሰቢያ ለሚያደርጉ፣ ለነዳያን ለሚመጸዉቱ ቤተ ክርስቲያን ለሚያሠሩ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ስለ ተጋድሏቸው ጽናትም ‹‹በሰው እጅ የማይለካውን ይህንን የመንግሥት አዳራሽ ውሰድ›› በማለት የመለኮትን ነገር የሚናገር የእሳት አንደበት ያለው የጸጋ ልብስ አልብሷቸዋል፤ በመስቀል ምልክት ያጌጡ ሰባት የሕይወት አክሊላትንም አቀዳጅቷቸዋል፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት የዕረፍታቸው ጊዜ መቃረቡን ባወቁ ጊዜ የመንፈስ ልጆቻቸውን ጠርተው ጌታችን የነገራቸውን ዅሉ አስረድተው አባታዊ ምክርና ተግሣፅ ከሰጧቸው በኋላ ነሐሴ ፳፬ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፈዋል፡፡ የመንፈስ ልጆቻቸውም ለአንድ ቅዱስ አባትና ካህን በሚገባ ሥርዓት በማኅሌት፣ በዝማሬና በምስጋና ቀብረዋቸዋል፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችንና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ተገልጾላቸዋል፤ ነፍሳቸውንም ‹‹የጠራሽ፣ ንጽሕት ነፍስ ሆይ ወደ እኔ ነዪ›› ብሎ በክብር ተቀብሏታል፡፡ በመጽሐፈ ገድላቸው እንደ ተጠቀሰው አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዚህ ዓለም የኖሩበት ዕድሜ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከዐሥር ወር ከዐሥር ቀን ነው፡፡ በእናት አባታቸው ቤት ፳፪ ዓመት፤ በከተታ ፫ ዓመት፤ በይፋት ፱ ወር፤ በዳሞት ፲፪ ዓመት፤ በአማራ ፲ ዓመት፤ በሐይቅ ፲ ዓመት፤ በደብረ ዳሞ ፲፪ ዓመት፤ በትግራይና በኢየሩሳሌም ገዳማት ፩ ዓመት፤ ዳዳ በሚባል አገር ፩ ወር፤ በደብረ አስቦ ገዳም ፳፱ ዓመት ከ፲ ቀን መቆየታቸውን መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል (ገ.ተ.ሃ ፶፱፥፲፬-፲፭)፡፡

በአጠቃላይ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደ ገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና ከመኖራቸው ባሻገር እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፤ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያችንም ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፡፡ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል፡፡ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋው አይጠፋበትም›› (ማቴ. ፲፥፵-፵፪) በማለት ጌታችን የተናገረውን መለኮታዊ ቃል ኪዳን መሠረት አድርጋ መጋቢት ፳፬ ቀን የፅንሰታቸውን፤ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን የልደታቸውን፤ ጥር ፬ ቀን የስባረ ዐፅማቸውን (እግራቸው የተሰበረበትን)፤ ግንቦት ፲፪ ቀን የፍልሰተ ዐፅማቸውን፤ ነሐሴ ፳፬ ቀን የዕረፍታቸውን በዓል በትላቅ ደስታ ታከብራለች፡፡ የጻድቁ በረከት አይለየን፡፡
2.3K views03:59
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-26 22:10:28 #ይህን_ያውቁ_ኖሯል?
ሼር አድርጉት
አሐዱ ተብሎ ቅዳሴ ከተገባ በኃላ (በቅዳሴ ሰአት)፡-
- ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወር፣
- ቅዳሴ አቋርጦ መውጣት
- የግል ፀሎት ማድረግ፣
- የጸሎት መጽሐፍትን ማንበብ፣
- ሳቅ፣ ወሬ፣
- ሞባይል ማስጮህና ማነጋገር
- ምግብ ይዞ ወደ ቤተ መቅደስ መግባት
- ወደ አውደ ምህረት አካባቢ መጠጋት
- እህቶች ሱሪ አድርገው መምጣት እንዲሁም ፀጉርን በሚገባ ሳይከናነቡ ለቅዳሴ ጸሎት መቆም
- ልጆችን ያለ ነጠላ ማቁረብ
- ቅዱስ ቁርባን በሚሰጥበት ግዜ ስነ-ስርአቱን በቪዲዮ፣ ፎቶ ካሜራ እና በሞባይል መቅረጽና ማንሳት ፈጽሞ የተከለከለ መሆኑን
- በተጨማሪ ህፃናትን ማቁረብ ሲያስቡ በተቻለ መጠን ካህናት ቅዳሴ ከመግባታቸው በፊት ይዘዋቸው ወደ ቤተ-መቅደስ ቢደርሱ መልካም ነውና ዘወትር ይህንን ተግባራዊ ያድርጉ።

#ለሰው_ሳይሆን_ለጌታ_እንደምታደርጉ፤
#የምታደርጉትን_ሁሉ_በትጋት_አድርጉ።
913 views19:10
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-21 21:59:59 #ነሐሴ_16

#ዕርገተ_ማርያም

ነሐሴ ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሥጋዋ ወደ ሰማይ ያረገበት መታሰቢያዋ ሆነ ። ከዕረፍቷም በኋላ ከእርሳቸው ስለመለየቷ ሐዋርያት ፈጽሞ እያዘኑ ነበር ።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ተገለጠላቸው እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድ እንዳላቸውም ተስፋ ሰጣቸው ። ወንጌላዊ ዮሐንስም እስያ በሚባል አገር እያስተማረ ሳለ በነሐሴ ወር ዐሥራ ስድስተኛ ቀን ተድላ ደስታ ወደአለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቀ ።

የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ሥር ተቀምጦ አየው። የንጽሕት እናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው ። እነርሱም የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት ። ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ወጣ ።

የክብር ባለቤት ጌታችንም እንዲህ እያለ አረጋጋት የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ ዘላለማዊ ወደ ሆነ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነዪ ። ያን ጊዜም በገነት ያሉ ዕፀዋት ሁሉም አዘነበሉ መላእክት የመላእክት አለቆች ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ እያመሰገኗት አሳረጓት ።

አባቷ ዳዊትም ንግሥት እመቤታችን ወርቀ ዘቦ ለብሳ ደርባ ደራርባ በቀኝህ ትቀመጣለች እያለ በበገና አመሰገናት ። በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጣ ከዐረገች በኋላ በልጁዋና በፈጣሪዋ ቀኝ በታላቅ ክብር ተቀመጠች ።

ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ሰግዶላት ተመልሶ ከሰማይ ወረደ ሐዋርያትን ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው ። እርሱም እንደ አየ እንደ ሰማ ሥጋዋንም በታላቅ ክብር በምስጋና እንደ አሳረጓት ነገራቸው ።

ሐዋርያትም በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ ። ከዚህም በኋላ እያዘኑ ሳሉ እነሆ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸውና የፍቅር አንድነት ልጆች ሰላም ይሁንላችሁ ስለ እናቴ ማርያም ሥጋ ለምን ታዝናላችሁ ። እነሆ እኔ እርሷን በሥጋ ላሳያችሁ ልባችሁም ደስ ሊለው ይገባዋል አላቸው ይህንንም ብሎ ከእርሳትው ዘንድ ወደ ሰማያት ዐረገ ።

ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ የነሐሴም ወር በባተ ቀን ለሐዋርያት ዮሐንስ እንዲህ አላቸው አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሰየን ዘንድ ኑ ይህን ሁለት ሱባዔ በመጾም የክብር ባለቤት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው በልጅዋ በወዳጅዋ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በእርሷ ደስ እንዲለን ።

በዚያን ጊዜም ዮሐንስ እንዳላቸው በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ የነሐሴ ወር እንደ ዛሬ ዐሥራ ስድስተኛ ቀን በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው ። በታላቅ ክብር በተወደደ ልጅዋ ቀኝ ተቀምጣ ከሥጋዋ ተዋሕዳ ተነሥታ እመቤታችን ማርያምን አዩዋት። እጆቿንም ዘርግታ የከበሩ ሐዋርያትን እያንዳንዳቸውን ባረከቻቸው በልባቸውም እጅግ ደስ አላቸው።

የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዒ ካህን ሆነ ። እስጢፋኖስም አዘጋጀ ዮሐንስም በመፍራት ቁሙ አለ ። ሁሉም ሐዋርያት በመሠዊያው ዙሪያ ቆሙ በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ።

ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው ። ከዚያም በኪሩቤልና በሱራፌል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን ማርያምን እንዲህ ብሎ ተናገራት።

በዚች ቀን የሆነ የዕርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰብኩ ልጆችሽ ሐዋርያትን እዘዣቸው ። መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ሁሉ ተጠብቆም በዚች ቀን ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ ። የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም መታሰቢያሽን ለሚያደርግ ሁሉ በዚች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውት ቸርነቴ ትገናኘዋለች ይህም ሥጋሽ ወደ ሰማይ ያረገበት ነው።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ክብር ይግባውና ጌታችንን እንዲህ አለችው ልጄ ሆይ እነሆ በዐይኖቻቸው አዩ በጆሮቻቸውም ሰሙ በእጆቻቸውም ያዙ ሌሎችም ታላላቅ ደንቆች ሥራዎችን አዩ ። እመቤታችንም ይህን ስትናገር ጌታችን ሰላምታ ሰጥቷቸው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ ።

የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ በፍጹም ደስታ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል እርሷ ስለእኛ ወደ ተወደደ ልጅዋ ሁልጊዜ ትማልዳለችና ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን ። በረከቷም ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከአባ ማትያስ ከሁሉም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት ጋራ ሐዋርያት ከሰበሰቧት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ከሁላችን ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ)
1.3K views18:59
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-21 21:59:42
286 views18:59
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-21 17:47:05
ከእርሱ ጋር ኀብረት ፍጠሩ!

እግዚአብሔርን ለማወቅ ለመውደድ ከእርሱ ጋር መተባበር አለባችሁ። ንባብ ብቻውን በቂ አይደለም። ንባብ የሚከፍትላችሁ መዝጊያውን ብቻ ነው። ከዚህ በኋላ እናንተ ትገቡና ከእግዚአብሔር ጋር ትኖራላችሁ ከዚያም ከእርሱ ጋር መኖር ጣፋጭ መሆኑን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ።

ስለሆነም ከእግዚአብሔር ጋር የሚሆን ሕይወትን ትሞክሩታላችሁ እርሱ በሁሉም ነገር ውስጥ ተካፋይ እንዲሆንም ትፈቅዳላችሁ።

እንደ ባልጀራችሁ አድርጋችሁ ልትወዱት ሞክሩ አሳቦቻችሁንና ሚስጥሮቻችሁን ለእርሱ ንገሩት። ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ጠብቁና እርሱ ምን ያህል ከእናንተና ለእናንተ እንደሚሰራ ታያላችሁ። ከዚህ በተጨማሪ በአሳቦቻችሁና በተሰጥኦዎቻችሁ ከመተማመን የበለጠ በእርሱ ላይ መተማመንን ታውቃላችሁ።

#አቡነ_ሺኖዳ_ሣልሳዊ
904 views14:47
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-18 21:03:37 በዓለ ደብረ ታቦር እና ቡሄ

ነሐሴ 13 ቀን 2014ዓ.ም

ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን ለገለጠበት ለበዓለ ደብረ ታቦር እንኳን በሰላም አደረሰን!
ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን በዓሉ በድምቀት ይከበራል፡፡ ይህ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ ‹ቡሄ› በመባል ይታወቃል፡፡ ቡሄ ማለት ‹መላጣ፣ ገላጣ› ማለት ነው፡፡ በአገራችን ክረምቱ፣ ጭጋጉ፣ ደመናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት በዚሁ በዓል አካባቢ ስለ ኾነ በዓሉ ‹ቡሄ› ተብሎ ይጠራል፡፡ በዓለ ደብረ ታቦር ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት፤ ብርሃን የታየበትና ድምፀ መለኮቱ የተሰማበ ዕለት ስለ ኾነ ‹የብርሃን› ወይም ‹የቡሄ› በዓል ይባላል፡፡
ቡሄ ሲመጣ የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ወደ ብርሃን፣ ወደ ጥቢ የሚያመራበት፤ ወደ መፀው የሚገባበት፤ ወገግታ የሚታይበት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚሸጋገርበት ወቅት በመኾኑ ከቡሄ በኋላ የጠነከረ ክረምት አይኖርም፡፡ ‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› እንዲሉ፡፡ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የቡሄ ዕለት ማታ ምእመናን ችቦ ያበራሉ፡፡ ይህም በደብረ ታቦር ለታየው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ ነው፡፡ ሕፃናቱ ይህ በዓል ከመድረሱ በፊት ቀደም ብለው ጅራፍ ሲገምዱና ሲያጮኹ (ሲያኖጉ) ይሰነብታሉ፡፡ እናቶችም ለዚህ በዓል የሚኾን ዳቦ ለመጋገር ስንዴያቸውን ሲያጥቡ፣ ሲፈትጉ ይሰነብታሉ፡፡ በበዓሉ ዋዜማ (ነሐሴ ፲፪ ቀን) ሕፃናት በየቤቱ እየዞሩ ‹‹ቡሄ ና በሉ፤ ቡሄ በሉ፡፡ ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ፤ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ …›› እያሉ ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ዳቦ እያነሡ ይሰጧቸዋል፡፡ ሕፃናቱ ‹ቡሄ› የሚሉትም ዳቦውን ነው፡፡
ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት እረኞች ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጥተዋል፡፡ ‹ቡሄ› ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና በበዓሉ ችቦ የሚበራውም ከዚህ ታሪክ በመነሣት ነው፡፡ ለክርስትና ልጅ፣ ለአማች፣ ለምራት፣ ለዘመድ አዝማድ ዅሉ የቡሄ ዳቦ ይሰጣል፡፡ ልጆችም ዳቧቸውን እየገመጡ ጅራፍ ሲገርፉ ይውላሉ፡፡ የጅራፉ መጮኽ የድምፀ መለኮት ምሳሌ ሲኾን፣ ጅራፉ ሲጮኽ ማስደንገጡም ነቢያትና ሐዋርያት በድምፀ መለኮት መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን ያስታውሳል፡፡
መምህረ ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ተማሪዎቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ በደብረ ታቦር ምሥጢር መግለጡን በማስታዎስ የአብነት ተማሪዎች ከመምህራቸው ጋር በመኾን በዓለ ደብረ ታቦርን (ቡሄን) ያከብራሉ፤ ስሙን ይጠራሉ፡፡ የአብነት ተማሪዎች ‹‹ስለ ደብረ ታቦር›› እያሉ እኽል ከምእመናን በመለመንና ገንዘብ በማዋጣት ጠላውን ጠምቀው፣ ዳቦውን ጋግረው፣ ቆሎውን ቆልተው ለደብረ ታቦር ዕለት ሊያስቀድሱ የመጡትን ምእመናን በመጋበዝና እርስበርስ በመገባበዝ፣ እንደዚሁም ቅኔ በማበርከት በዓለ ደብረ ታቦርን በታላቅ ድምቀት ያከብራሉ፡፡ ይህም እስከ አሁን ድረስ በአብነት ትምህርት ቤቶች የሚሠራበት ነባር ትውፊት ነው፡፡
ነገር ግን በአንድ አካባቢዎች በተለይ በከተማ ዙሪያ በዓለ ደብረ ታቦር (ቡሄ) ሃይማኖታዊ ትውፊቱን የለቀቀ ይመስላል፡፡ ለዚህም ልጆች የሚጫወቱበት መዝሙር ግጥሙና ዜማው ዓለማዊ መልእክት የሚበዛበት መኾኑ፤ በወቅቱ ችቦ ከማብራት ይልቅ ርችት መተኮሱና በየመጠጥ ቤቱ እየሰከሩ መጮኹ፤ ወዘተ. የበዓሉን መንፈሳዊ ትውፊት ከሚያደበዝዙ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም በዚህ በዓል ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ የሚሽቀዳደሙ ነገር ግን የበዓሉን ታሪካዊ አመጣጥ የማያዉቁ ልጆችም ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ስለዚህ ወላጆች ለልጆቻቸው የበዓለ ደብረ ታቦርን መንፈሳዊነት፣ የመዝሙሮቹን ያሬዳዊነትና አከባበሩን ከቤተ ክርስቲያን መምህራን በመጠየቅ ማስተማር፤ ልጆችም ከወላጆች ወይም ከመምህራን በመጠየቅ የበዓሉን አከባበር መረዳትና የዚህን በዓል መንፈሳዊ ትውፊት ሳይበረዝ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባቸዋል፡፡ ‹‹ድምፅህን ሰማና በብሩህ ደመና፤ የቡሄው ብርሃን ለእኛ በራልን …›› የሚለውንና ይህን የሚመስሉ መንፈሳውያን መዝሙራትን እየዘመሩ በየቤቱ በመዘዋወር የሚያገኙትን ዳቦና ገንዘብ ለነዳያንና ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ ልጆችንም ማበረታታትና አርአያነታቸውን መከተል ይኖርብናል፡፡
መልካም በዓል ይኹንልን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
1.3K views18:03
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-18 21:03:32
286 views18:03
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-17 14:27:10
ቡሄ ማለት ምን ማለት ነው
ቡሄን ለምን እናከብራለን
ጅራፍ ለምን እናጨዋለን
ሙልሙል ዳቦ ለምን እንጋግራለን።
983 views11:27
ክፈት / አስተያየት ይስጡ