Get Mystery Box with random crypto!

ላሁኑ እዚህ ደርሰናል! የመንፈሳዊ አገልግሎት ጉዳይ መያዣ መጨበጫ ጠፍቶለት፤ ውሉ እንደጠፋ በግስ | ነገረ ወንጌላውያን

ላሁኑ እዚህ ደርሰናል!

የመንፈሳዊ አገልግሎት ጉዳይ መያዣ መጨበጫ ጠፍቶለት፤ ውሉ እንደጠፋ በግስጋሴ ላይ ይገኛል፡፡ እንኳ ይሆናል ይሰማል ብለን የማናስበው ነገር ሁሉ በመሐከላችን እየነገሠ ነው፡፡ መጠየቅን አነውረው የሚያዩ በተቀደደው ሁሉ የሚፈሱ ምእመናን እየበዙ፣ ስሕተት ቀንድ እና ጥፍር አብቅሏል፡፡

ወንጌላዊው ክርስትና ሐዲዱን ለቅቆ እየተንሸራተተ፣ የወንጌሉ ማእከላዊነት ጥጉን ይዞ፣ የግለሰቦች ገናናነት ሰማይ ደርሷል፡፡

የልክነት እና ስሕተት ሚዛኑ የማይለወጠው ቃለ እግዚአብሔር መሆኑ ቀርቶ ግለሰቦች በማይከሰሱበት እና በማይወቀሱበት ዙፋን ላይ ተሰይመዋል፡፡ መጠየቅ የተረገመ ሆኗል፤ ለምን? በሚሉ ላይ እልፍ የስድብ ምላሶች ይዘረጋሉ፤ ተቀባን ባዮች ስር እልፎች ተኮልኩለው በሆነው መንገድ ረድኤታቸውን ይጠባበቃሉ፡፡ እግዚአብሔርን በግል መማጠን ያለፈበት ፋሽን ሆኗል፡፡ የማይመረመሩት እና አይጠየቄዎቹ ቅቡዐን ያለ ከልካይ ይፋንናሉ፡፡

የዛሬ አመት እንዳሁኑ ወቅት የነሸጠው ቅቡዕ እግዚአብሔር እንደተናገረው እየማለ እየተገዘተ “2014 አንዳች ኮሽታ የሌለበት፣ ክፉ ሁሉ የሚያልፍበት፣ ለእናንተ እና ለኢትዮጵያ የመድረስ አመት ይሆናል፡፡” ብሎ ለፍፎ ነበር፡፡ አመቱ ግን እንዳያልፍ አለፈ፡፡ ለምን? ያለ ግን አልነበረም፤ አንዳንድ ደፋሮች እንደውም ትንቢቱን ቀባብተው እውነተኛ ለማስመሰል አይጥሩ ጥረት ጣሩ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እንቅጩን የመናገር ችግር የለበትም፤ ተናግሮም ከሆነ ዘወርዋራነት ጨርሶውኑ ሊኖረው አይችልም፡፡

በዘመነ ኤርሚያስ ሕዝቡ ተማርኮ መከራውን እንደሚበላ ነጩን ነበር የተናገረው፤ እርግጥ ይህ ያልተዋጠላቸው ሐሳውያን ነባያት ከገዛ ልባቸው እየወለዱ፣ በባዶ ተስፋ ሕዝቡን ሊያረጋጉ ይሞክሩ ነበር፡፡ በእስራኤል እና በይሁዳ የሆነው ግን እግዚአብሔር በኤርሚያስ የተናገረው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ከሌለበት ማባባበል፣ እግዚአብሔር ያለበት ቁጣ በስንት ጣዕሙ፡፡ የሆነው ሆኖ ግን ሕዝቡም ይህንን ወድዷል፤ ሐሰትን እየተጋተ ባዶነትን ያገሳል፡፡

ያልዘራችሁትን፣ ያለፋችሁበትን፣ ያልደከማችሁበትን ትበላላችሁ የሚልም ቅዠት ሰምተን ነበር፡፡ በየአካውንታቸው የራሳቸው ያልሆነን ብር የሚጠብቁ፣ የባንክ ደብረታቸውን በውሃ እና በዘይት ያረጠቡ፣ የኤቲኤም ካርድ የገዙ ተላላ “ምእመናንም” አይተናል፡፡

ከእግዜሩ ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀናል፤ ክፍተኛ ግብግብ ላይ ነንም የሚለውን ጀግና አይተናል፡፡

በዚህ ሰሞን ደግሞ አዳፋ ላቤን የጠረኩበትን ስስ ወረቀት soft እያኘካችሁ በውሃ አወራርዱት ባይ ተከስቷል፡፡

እስከ አሁን እንግዲህ እዚህ ደረሰናል፡፡ ነገ የትም ልንደርስ እንችላለን፡፡ የክርስቶስ የሆነችው ቤተክርስቲያን ከድንዛዜዋ ወጥታ እንዲህ ያለውን ሸፍጥ እንቢኝ ልትል እና እውነትን በማስተማር ምእመኗን ልትጠብቅ ይገባታል፡፡ መሽኮርመሟን ወዲያ ጥላ፣ እውነት በሚጠይቀው ድፍረት ልትገለጥ ይገባታል፡፡ ቅዱሱን ወንጌል ከሚያረክስ እና ከሚያስወቅስ የትኛውም የሐሰት አሠራር ጋር ያላት ሰውር ይሁን ግልጥ ሕብረት ልታቆም ይገባታል፡፡ አጥሯን በማጠባበቅ የገዛ ዐደራዋን በአግባብ ልትወጣም ይገባታል፡፡

እግዚአብሔር ይርዳን!!!

መጋቢ ስንታየሁ በቀለ