Get Mystery Box with random crypto!

የትኛውን ኢየሱስ ተቀበሉ? ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያቱ ከስህተት ትምህርት ስለ መጠበቅ ብዙ ብለዋል። | ነገረ ወንጌላውያን

የትኛውን ኢየሱስ ተቀበሉ?

ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያቱ ከስህተት ትምህርት ስለ መጠበቅ ብዙ ብለዋል። የአዲስ ኪዳን መልዕክቶችም እኩሌታ ስለዚሁ ጉዳይ የሚያወሳ ነው። ሌላ "ወንጌል" እና ሌላ "ኢየሱስ" የሚባልም ነገር አለ ብለውናል። በተለይ የሃሰትን ትምህርት ጉዳይ በቀላሉ ልንመለከተው እንደማይገባ በርካታ ማሳሰቢያዎች ተፅፈውልናል። ለምሳሌ እንኳ ብንወስድ ጴጥሮስም ሃሰት ስለሚያስከትለው አደጋ እንዲህ ነበር ያለው:-

“ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ.... አሹልከው ያገባሉ” (2ጴጥ 2:1)

ጳውሎስ ደግሞ የሚከተለውን ብሏል

“መንፈስ ግን በግልጥ፦ በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል” (1ኛ ጢሞ 4፥1-2)

ቢያንስ በእነኚህ ሁለት ጥቅሶች መሰረት ሃሰትን መማርም ሆነ ማስተማር ጌታን "መከተል" ሳይሆን "መካድ" ነው። "የህይወት" ሳይሆን "የጥፋት" በር ነው። ሃይማኖትን "መጠበቅ" ሳይሆን "መካድ" ነው። የእግዚአብሔር ልጅ የሆነውን "ኢየሱስ" ሳይሆን ሌላ "ኢየሱስ" ማምለክ ነው። የእግዚአብሔርን "ወንጌል" ሳይሆን ሌላ "ወንጌል" መቀበል ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያቱም ሆነ የቤተክርስቲያን አባቶች ሃሰትን በአደባባይ የሚገልጡትና ጉባኤ ጠርተው የሚቃወመት ብሎም የሚያወግዙት።

ወንድሜ ሆይ የሃሰት ትምህርት በነገሰበት ጉባኤ ወይም የሃሰት ትምህርት በነገሰበት አስተማሪ "አገልግሎት" ይህንን ያክል ሰው "ዳነ" ብሎ ማንቆለጳጰስ የጌታን ቁስል መውጋት ነው። ለንፁሁ ወንጌል ውድ ህይወታቸውን የከፈሉትን አባቶች መቀለጃ ማድረግ ነው። ስለዚህ "ጌታን ተቀበሉ" ሲባል ጠይቅ፤ የቱን ጌታ ሐዋርያቱ የሰበኩትን ወይስ እነ ኬነት ሃገን የሰበኩትን? የቱን ኢየሱስ መስቀል ላይ የሞተውን ወይስ ሲኦል የሞተውን? መንፈሰ የሆነውን ወይስ አምላክ ሰው የሆነውን? የቱን ከእኛ ጋር አኩያ የሆነውን ወይስ ከአብ ጋር እኩያ የሆነውን?.....የቱን ኢየሱስ ተቀበሉ ብለህ ጠይቅ?

"ዳነ" የተባለውን ሁሉ "በምስጋና" የምንቀበል ከሆነ ታዲያ ለምን ኦንሊ ጂሰሶች ሲያጠምቁ አብረን አንዘምርም? ለምን ታዲያ ጆሆቫ ዊተነሶች አዳዲስ አባላቶቻቸውን በጉባኤያቸው ሲያስተዋውቁ እልል አንልም? ሞርሞኖች "የወንጌል" ስርጭት መርሃ ግብራችን "የተሳካ ነበር" ሲሉ ለምን "በርቱልን" ብለን የምስጋና ደብዳቤ አንፅፍላቸውም? ኦርቶዶክሳዊያኑም እኮ አዳዲስ አባላት አጥምቀው ይቀበላሉ ለምን ታዲያ "አበጃችሁ ድንቅ የጌታ ስራ ነው" አንላቸውም?

ወገን "መመዘኛችን" በራሱ "መመዘኛ" ያስፈልገዋል። በጴንጤነት ጎራ (መደብ) ሳይሆን በቃለ እግዚአብሔር መርህ "መለካት" አለብን። በቃል እምነት (word of faith) ስሁት ትምህርቶች የተጠመቀ (ዮናታን የword of faith ሰው ካልመሰህ ኮሜንት መስጫ ላይ ሊንክ አስቀምጥልሃለሁ) እና በሃሰት ትንቢት የተገኘ ሰው "ይህንን ያክል ሰዎች ጌታን ተቀበሉ አመስግኑልኝ ሲል" ምን ሰበከላቸው? የትኛውንስ ጌታ ነው የተቀበሉት?....ወዘተ ብለህ ሳትጠይቅ ለጭብጨባ እጅህን የምታነሳ ከሆነ በርግጥ "በመጨረሻው ዘመን ይገለጣል" የተባለው ክፉ መንፈስ አግኝቶሃል። ወንጌሉም አልገባህም። "የትም ፍጪው..." በሚለውም ተረት ታምናለህ ማለት ነው። "ከፈሪሳዊያን እርሾ ተጠበቁ" ያለው ምን እንደሆነም ገና አልመረመርክም። "ለድነት" የአስተምህሮ ጤነኛ መሆን የግዴታ እንደሆነ ከቶ አላወቅህም። አባቶችም ዋጋ እየከፈሉ ከሃሰት ትምህርት ጋር ለምን እንደተጋደሉም ገና አልተገለጠልህም ማለት ነው። ታዲያ በዚህ አያያዝህ ነገ ሃሰተኛው ክርስቶስም ሲገለጥ ሳታጨበጭብ ትቀራለህ? ይርዳሃ!

አንዳንዶች "የዮኒ ስህተት እኮ ብዙም አይደለም" ብለው ለመሸፋፈን ይጥራሉ። ሲጀመር ተሳስተዋል እነርሱ እንዳሉት እንኳ ይሁን ብንል፤ የብርጭቆ ውሃ ጥቂት ብቻ መርዝ ቢገባበት ለመጠጥ ይሆናል? ጥቂት እርሾስ ሊጡን ሁሉ አያቦካውም? ለመሆኑ አንድ ትምህርት "የስህተት ትምህርት" ለመባል ምን ያህል መጠን "ስህተት" ሊገባበት ያስፈልገዋል? ወዘተ..ብለን እንጠይቃለን። ወዳጅ ሆይ መመዘኛችን ቃለ እግዚአብሔር እንጂ የሚዲያ "ፕሮፖጋንዳ" ወይም "አባቶች" የተባሉ ሰዎች "አጃቢነት" አይደሉም።

በመጨረሻም

“ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን”
(ገላ1፥8) ተብሎ እንደተፃፈ ማስታወስ "ለማሰብ" ይረዳል እላለሁ። ሌላው ደግሞ ሃሳዊያን ላይ ተቃውሞ በቀረበ ቁጥር ተሽቀዳድመው "ቀንታችሁ ነው" "እናንተ ምን ሰራችሁ!?" "አንድ ሰው አድነሃል!?" የሚሉ ደካሞች ወይም በገንዘብ የተገዙ አሉ። ለእነርሱ ያለኝ መልስ "አዎ ቀንቼ ነው!" ይህንን ሁሉ የምለው ለክርስቶስ ወንጌል "ቀንቼ ነው" ልክ ያልሆነውን የምናገረው ደግሞ ከእኔ "ስራ" ጋር ሳይሆን ከቃሉ ጋር አስተያይቼ ነው የሚል ነው። የዚህ ልጥፍ ዓላማም "የእንጠይቅ ጥሪ" እንጂ የሰውን ስራ የማጣጣል አለመሆኑ ይታወቅልኝ። ማስተዋሉን ያድለና!

ቴዎድሮስ ተጫን