Get Mystery Box with random crypto!

ቤተክርስቲያን እና ቄሳር ታሪክ እንደሚነግረን በአውግስጦስ ቄሳር ዘመነ መንግስት በመካከለኛው ምስ | ነገረ ወንጌላውያን

ቤተክርስቲያን እና ቄሳር

ታሪክ እንደሚነግረን በአውግስጦስ ቄሳር ዘመነ መንግስት በመካከለኛው ምስራቅ የተጀመረችው የክርስቶስ ቤተክርስቲያን በተለይ በቄሳር ኔሮ አገዛዝ ወቅት በብዙ ስደትና መከራ አልፋለች። በዘመነ ቆስጠንጢኖስ ደግሞ የሮም መንግስታዊ ሃይማኖት ለመሆን በቅታለች። ቀስ በቀስም የሮም አፄያዊ አገዛዝ እየተዳከመ ሲመጣም ከመንፈሳዊ ተቋምነቷ በፍጥነት ተለውጣ የፖለቲካ አመራሩን በእጅ አዙርም ቢሆን ወደ መምራት መጣች።

በመጀመሪያዎቹ ሶስት መቶ አመታት የነበራት ወንጌል የመስበክና ደቀ መዛሙርትን የማፍራት ትጋት በቄሳር ዘንድ ባገኘችው ተቀባይነት ምክንያትና "በቤተመንግስት ያለው ንጉስ የኛ ሰው ነው" በማለት ወንጌል የማስፋቱን ስራ "በመስዋዕትነት" ሳይሆን በቄሳር ቆስጠንጢኖስ ቤተመንግስት ትዕዛዝ ወደ ማከናወን ቀየረችው። ሺዎችም በቄሳር ትዕዛዝ "ጌታን" እንዲቀበሉ አደረገች ትልልቅ መሰብሰቢያ አዳራሾችን መግንባቱንም በሰፊው ገነባችበት።

ደቀ መዝሙር ማድረግ የሚባለው ጉዳይ እየተዘነጋ አገልጋዮቹም ስልጣን ማደላደልና በቤተመንግስት ማለፊያ ማዕድ ዙሪያ መታደም ላይ ብቻ አተኮሩ። ቤተክርስቲያንም የወንጌል ስራዋን በሶስተኛው ክፍለ ዘመን ላይ እርግፍ አድርጋ ትታ ከቄሳር ጋር አሼሼ ገዳሜ ማለቱን እንደ ዋና ስልት ወሰደችው። ኋላም በስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተወለደው እስልምና ጡንቻ አውጥቶ በአስረኛው ክፍለ ዘመን ላይ ኢየሩሳሌምን ልቆጣጠርና ዓለምንም ልሸፍን አንድ ምዕራፍ ነው የቀረኝ እያለ ሲፎክርባት ምርጫ ስላልነበራት "የመስቀል ጦርነትን" አወጀች። ጠብ መንጃ "ባርካ" በዚህ ጦርነት የተሳተፈ "የእርሱና የቤተሰቡ ሃጥያት ይሰረይለታል" ብላ ልጆቿን አሰለፈች። መስቀልና ሰይፍንም በአንድነት አነገበች። ያሳዝናል!

ቀድማ በጀመረችበት ሩጫ ልክ ፈጥና ቢሆን ኖሮ! "ኖሮ" ነው። የቆስጠንጢኖስ ግብዣ ባያደናቅፋት ኖሮ ቤተመንግስቱም "እንደገፋት" ቢቀር ወይም እርሷ "አንቢ ለግብዣህ" ብላው ቢሆን ኖሮ። "በቤተመንግስት እኮ ያለው የእኛ ሰው ነው" ማለት ባትጀምር ኖሮ። ዓለምን በሸፈነች! የክርስትና ተቃራኒ የሆኑትም ሆነ ሌሎች ሃይማኖቶችም ባልተስፋፉ ነበር።

ዛሬም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከተሰጣት ወንጌልን የመስበክና ደቀ መዝሙር የማፍራት ተልዕኮ ፈቀቅ ብላ "በቤተመንግስት እኮ ያለው የእኛ ሰው ነው" ብላ መንግስትን ወደ ማጀብ አልፋም የመንግስትን ስልጣን መከጀል ከጀመረች ሰንበት ብላ እንደ ጥንቱ ዘመን ታሪኳ ወንጌልን ለማስፋፋት ሆነ ለመጠበቅ የመንግስት ጡንቻ (ክላሽ) መበደሯ አይቀርም።

ስለዚህ የቀደመውን አጭር ልጥፍ እዚህም እደግመዋለሁ.... መንግስትን "መደገፍም" ሆነ "መቃወም" የቤተክርስቲያን ተልዕኮ አይደለም። የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ወንጌል መስበክና ደቀ መዛሙርትን ማፍራት ብቻ ነው።

ቆም ብሎ ለማሰብ ጊዜው ነው!

ቴዎድሮስ ተጫን

ዙሪያዬን አጅቦኝ ወታደር
በቄሳር ሰገነት ከማደር
ደም እምባ እያፈሰስኩ ለጌታ
ይሻለኛል ለእኔስ ጎልጎታ

ዘማሪ ታምራት ሃይሌ