Get Mystery Box with random crypto!

የአቡበክር አስ-ሲዲቅ (ረድየሏሁ ዐንሁ) ታሪክ የመጨረሻ ክፍል    የአል-ፋሩቅ መተካት የአ | የአረብ ገንዳ መስጂድ ወጣቶች

የአቡበክር አስ-ሲዲቅ (ረድየሏሁ ዐንሁ) ታሪክ

የመጨረሻ ክፍል
  
የአል-ፋሩቅ መተካት

የአቡበክር አስ-ሲዲቅ ሞት ምክንያት ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡፡ የሞቱት ከፍተኛ ቅዝቃዜ ባለው ውሃ በመታጠባቸው ምክንያት ብርድ በሽታ ታመው ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ የለም እርሳቸው የሞቱት አንድ አይሁዳዊ የተመረዘ ምግብ አብልቷቸው ለአስራ አምስት ቀናት ያህል ታመው ነው የሚሉም አሉ፡፡ ..

ይህ በእርግጥ ለአይሁዶች አዲስ አይደለም፡፡ ብዙ ነብያትን የመግደል ልምድ አካብተዋል፡፡ ሰይድ ኢሳን (ዐ.ሰ) ለመግደል ሞክረዋል፡፡ ነብዩን (ሰዐ.ወ) ሶስት ጊዜ ለመግደል ሞክረው አልተሳካላቸውም፡፡ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር አድርገው ለዑመር ቢን አል ኸጣብ፣ ለዑስማን ቢን ዓፋን ለጦልሃና ለዙበይር መገደል ምክንያት የሆኑት አይሁዳዊያን ናቸው፡፡

ሰይድ አቡበክር ላይ ሕመም በጠናባቸው ጊዜ ሶሃቦች በርሳቸው ቦታ ላይ ሰይድ ዑመርን እንዲተኩ እያማከሯቸው ነበር፡፡ አስ-ሲዲቅ ዓብዱራህማን ቢን ዓውፍን ስለ ዑመር ሲጠይቋቸው እንዲህ ሲሉ መለሱ፡፡ «አንቱ የረሱል ኸሊፋ ሆይ ዑመር ከምናስባቸው በላይ ጥሩ ሰው ናቸው።››

ዑስማንን ሲጠይቋቸው ደግሞ እንዲህ አሉ... “ከላያቸው በተሻለ ውስጣቸው ጥሩ እንደሆነ አስተምረውኛል፡፡” አቡበክር ሌሎችንም ታላላቅ ሶሃባዎችን ሲያማክሯቸው በጉዳዩ ላይ ተስማሙ።

አንዳንድ ስዎች ደግሞ እንዲህ አሏቸው “ዑመር ኃይለኛነት አለባቸው፡፡ አላህ እንዴት ኸሊፋ አደረግካቸው ብሎ ቢጠይቅዎ ምን ሊመልሱ ነው” አቡበክርም ተቆጡና እንዲህ አሉ... “ደግሞ በአላህ ታስፈራሩኛላችሁ... ወላሂ አላህ ቢጠይቀኝ ከምርጥ ሰዎችህ ምርጥ የሆነውን በእኔ ቦታ ተክቼዋለሁ ብዬ እመልስለታለሁ፡፡”

ከዚያም አቡበክር ዑስማን ቢን ዓፋንን(ረ.ዐ) አስጠሯቸውና እንደሚከተለው እንዲጽፉ አዘዟቸው፡፡... “ይህ ኑዛዜ ከዱኒያ ለመጨረሻ ጊዜ ሲሰናበት ወደ አኼራ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሄድ አቡበክር ቢን አቢ ቁሃፉ ያስተላለፈው ትዕዛዝ ነው። ሐሰተኞች እውነት እንዲናገሩ፣ አመጸኞች አደብ እንዲገዙ፣ ከሃዲዎች እንዲያምኑ ስል ይህን ትዕዛዝ አስተላልፌያለሁ... ተክቼላችኋለሁ...” የተኩትን ሰው በስም ሳይጠቅሱ ራሳቸውን ይስታሉ።

ሰይድ ዑስማን “ዑመር ቢን አል-ኸጧብን ተክቼላችኋለሁ...” የሚል ዓረፍተ ነገር ጻፉ። ዑስማን ይህን ያደረጉት አስ-ሲዲቅ የተኩትን ስው በግልጽ ሳይናገሩ ካለፉ በሙስሊሞች መካከል ውዝግብ ይፈጠራል ብለው ሰግተው ነው። በተጨማሪም አቡበክር( በርሳቸው ቦታ መተካት ያለበት ሰው ማን እንደሆነ መወሰናቸውን ዑስማን(ረ.ዐ) ስለሚያውቁ፡፡

አስሲዲቅ(ረ.ዐ) ትንሽ መለስ እንዳሉ ዑስማን(ረ.ዐ) የጻፉትን እንዲያነቡላቸው አዘዟቸው... “በእኔ ቦታ ዑመር ቢን አል-ኸጣብን ተክቼላችኋለሁ፡፡” የሚለውን አነበቡ። በዚህ ጊዜ ሰይድ አቡበክር እንዲህ አሉ... “አሏሁ አክበር! የተካሁትን ሰው በስም ሳልናገር ሕይወቴ ብታልፍ ሙስሊሞች ይጨቃጨቃሉ ብለህ ስግተህ ነበር ማለት ነው? ለእስልምና እና ለሙስሊሞች ለዋልከው ውለታህ አላህ መልካም ምንዳ ይክፈልህ ዑስማን”

ከዚያም አስ-ሲዲቅ ሶሃቦች እንዲሰባሰቡ አደረጉና እንዲህ አሏቸው... “እናንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ዱኒያን ተሰናብቼ ወደ አኼራ መጓዜ ነው፡፡ በዚህ ወረቀት ውስጥ እኔን የሚተካ ሰው ገልጬላችኋለሁ፡፡ እርሱን ስሙት ታዘዙትም፡፡ እኔ ለእናንተ የመረጥኩላችሁን ስው ትቀበሉታላችሁን?” ብለው ሲጠይቁ ሁሉም በህብረት “ተደስተናል” አሉ።

ዓሊይ ቢን አቢ ጧሊብ(ረዐ) ተነሱና እንዲህ አሉ... "ዑመር ካልተሾሙ በቀር አንደሰትም...” አስ-ሲዲቅ ፈገግ አሉና "የተሾመው ዑመር ቢን አል-ኸጣብ ነው፡፡ ስሙት ታዘዙትም። ወላሂ ስለርሱ መልካምን እንጂ ሌላ የማውቀው ነገር የለኝም”

     የወዳጆች መመሳሰል

አቡበክር ዛሬ ቀኑ ማነው” ሲሉ ጠየቁ፡፡ “ሰኞ ነው” አሏቸው “ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በምን ቀን ነበር ያለፉት" ሲሉ አከሉ፡፡ ሰኞ ቀን፡፡ አቡበክርም እንዲህ አሉ “እላህ ሆይ ሞቴን በዚችው ሌሊት አድርግልኝ ከዚያም እንዲህ ጠየቁ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የተከፈኑት በምን ዓይነት ከፈን ነበር” የተከፈኑበትን ነገሯቸው፡፡ “እኔንም በዚያው ዓይነት ከፍኑኝ፡፡ አስክሬኔንም ባለቤቴ አስማእ ቢንት ዑመይስ ትጠበኝ...”

      የአስ-ሲዲቅ ጉዞ
እሜቴ ዓኢሻ ወደ ቤት ገብታ ማልቀስ ስትጀምር አስ-ሲዲቅ ከለከሏት። ከዚያም አጠገባቸው ተቀምጣ ግጥሞችን ትገጥም ጀመር፡፡ አቡበክርም ዓኢሻን እሱን ተይና እንዲህ የሚለውን የቁርኣን አንቀጽ አንብቢ

وَجَاءَتْ سَكْرَةُ الْمَوْتِ بِالْحَقِّ ۖ ذَٰلِكَ مَا كُنتَ مِنْه تَحِيدُ (١٩) وَنُفِخَ فِي الصُّورِ ۚ ذَٰلِكَ يَوْمُ الْوَعِيدِ (٢٠)
"የሞትም መከራ እውነቱን ነገር ታመጣለች፡፡ (ሰው ሆይ)፡- «ይህ ያ ከርሱ ትሸሸው የነበርከው ነው» (ይባላል)፡፡ በቀንዱም ውስጥ ይንነፋል፡፡ ያ (ቀን) የዛቻው (መፈጸሚያ) ቀን ነው፡፡" (ቃፍ 19-20)

አስ-ሲዲቅ በመሞቻቸው ዕለት የተናገሯት የመጨረሻዋ ንግግር እንዲህ የምትል ነበረች... "ሙስሊም አድርገህ ግደለኝ፣ ከመልካሞቹም ጋር አስጠጋኝ፡፡" አቡበክር የሞቱት ሰኞ ሌሊት ነበር፡፡ በጀናዛቸው ላይ ያስገዱት ዑመር ቢን አል-ኸጣብ(ረ.ዐ) ናቸው፡፡ መላው የመዲና ከተማ በአቡበክር ሞት ምክንያት ስታነባ ዋለች፡፡ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ካረፉበት መካነ መቃብር አጠገብ ተቀበሩ፡፡ ዓሊይ ቢን አቢጧሊብ(ረ.ዐ) ወደ መቃብሩ ተጠጉና እንዲህ አሉ። “አቡበክር ሆይ አላህ ይዘንልህ፡፡ ወላሂ ከሙስሊሞች አንደኛ አንተ ነበርክ፡፡ በኢማን ጥልቀትና ጥንካሬ አንተን የሚያክል የለም፡፡ ረሱልን (ሰ.ዐ.ወ) በመንከባከብ፣ እስልምናን በመጠበቅ ወደር አልነበረህም፡፡ ለሙስሊሞች ሩህሩህ ነበርክ፡፡ ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ጋር በአፈጣጠርም፣ በስነምግባርም፣ በግርማ ሞገስም ተመሳሳይ ነበርክ፡፡ ለእስልምና እና ለረሱል (ሰ.ዐ.ወ) የከፈልከውን ውለታ አላህ በመልካም ይመልስልህ። ስዎች ረሱልን (ስ.ዐ.ወ) እምቢ ሲሏቸው ኣንተ አስተናገድካቸው። ተቀበልካቸው፡፡ ሲያገሏቸው አንተ አቀረብካቸው፡፡ ምን ጊዜም ከጎናቸው ነበርክ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) በመጽሐፉ እውነተኛ ብሎ ጠርቶሃል. “ያም በእውነት የመጣው በርሱ ያመነውም” ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ያመጡትን እውነት እውነት ብለህ የተቀበልከው አንተ ነህ፡፡ ወላሂ ለእስልምና ጋሻና መከታ፣ ለከሓዲያን ደግሞ ቅጣት ነበርክ፡፡ ጎርፍም ሆነ አውሎ ንፋስ የማያናጋው ተራራ ነበርክ፡፡ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ስለ አንተ እንደተናገሩት ሰውነትህ ለስላሳ ቢሆንም በአላህ ትዕዛዝ ላይ ግን ጠንካራ ነበርክ፡፡ ለራስህ የምትተናነስ ብትሆንም አላህ ዘንድ ግን ከፍ ያልክ ነህ፡፡ በምድር ላይ ኃያል፣ ሙስሊሞች ዘንድ ደግሞ ታላቅ ነበርክ፡፡ ለእኛ የዋልከውን ውለታ አላህ በመልካም ይመልስልህ፡፡ ባንተ ላይ ቂምም ሆነ ብሶት ያለበት ሰው የለም፡፡ ደካማ የድርሻውን እስካላገኘ ድረስ አንተ
ዘንድ ኃያል ነበር፡፡ ኃያሉ የሌሎችን ድርሻ እስኪሰጥ ድረስ አንተ ዘንድ ደካማ ነበር፡፡ ምንዳህን አላህ አይከልክለን፡፡ ካንተ በኋላም አያጥምመን፡፡”

  ረ ዲ የ ሏ ሁ  ዐ ን ሁ

ምስጋና ይገባው ለአሏህ ﷻ ይህን ታሪክ አስጀምሮ ላስጨረሰን
http://t.me//@arebgendamesjid
        እዚጋ  ተጠናቀቀ

የአረብገንዳ መስጂድ ወጣቶች የመረጃ ዘርፍ