Get Mystery Box with random crypto!

ዕብድም ብሆን ፍቅሩ በልቤ ትልቅ ቦታ አለው!' ዝርዝር ታሪኩ ውስጥ አልገባም። ከጥቂት ዓመታት በ | ናዝራዊ Tube

ዕብድም ብሆን ፍቅሩ በልቤ ትልቅ ቦታ አለው!"

ዝርዝር ታሪኩ ውስጥ አልገባም። ከጥቂት ዓመታት በፊት ካወቅሁትና አልፎ አልፎ እየተገናኘን ስለ ሕይወት ከምናወጋ፣ ጌታ ኢየሱስን አብዝቶ ከሚወድ፣ መናገር የፈለገውን የእግዚአብሔርን ቃል ያለ አንዳች መደነቃቀፍ በቃሉ ከሚወጣ፣ ቸርች በማዘውተር፣ ቃሉን በማንበብ፣ በመጸለይና በመዘመር ነፍሱን ከምትረካ አንድ የተወደደ ወንድም ጋር ከረጅም ጊዜ መጠፋፋት በኋላ ድንገት ተገናኘን። በቆይታችን ካወጋናቸው ቁም ነገሮች መካከል ልቤ የተነካበትን፣ ለእምነታችን ጽናት የሚቀሰም አንዳች ትምህርት ይገኝበታል ብዬ ያሰብኩትንና ከንግግራችንን ክፍል የቆነጠርኩትን ወዲህ አምጥቼዋለሁ።

እሱ፦ ...የማልክደው ነገር የአእምሮ በሽተኛ ነኝ። በየቀኑ ኪኒን እወስዳለሁ። አንዳንዴ ነርቨስ የምሆንበት አጋጣሚ ሲከሰት እንኳ ምን ማድረግ እንዳለብኝና እንደሌለብኝ አውቃለሁ። ከፍ ባለ ድምጽ ብቻዬን ስለፈልፍ አይተኸኝም ታውቃለህ። ብዙ ጊዜ እንደዛ ዓይነት ስሜት ውስጥ ሆኜ ሳገኝህ የምታሳየኝን ፊት ፈጽሞ አልረሳውም። ዕብድም ብሆን ያለሁበትን ሁኔታ ማን እንደሚረዳኝና እንደማይረዳኝ አውቃለሁ።

...በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆኜ እግዚአብሔርን አስበዋለሁ፣ በቃሉ እደገፋለሁ። ዕብድም ብሆን መንገዴን አልስትም፣ ዕብደቴ ኢየሱስን ከመውደድና ከመከተል አላገደኝም። ፍቅሩ በልቤ ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው። ስላገኘሁህ ደስ ብሎኛል፤ እወድሃለሁ።

እኔ፦ (ስሙን በቁልምጫ ጠርቼ) እኔም እወድሃለሁ። አንተ እያለፍክበት ባለው መንገድና ያንን ፈተናህን እያስተናገድክ ባለበት የእግዚአብሔር ፀጋ፣ ጠንካራ መንፈሳዊ ሕይወትህና ብስለትህ ሁሌም እደነቃለሁ። በጠቀስካቸው ስሜቶች ውስጥ ስትሆን የምትሰጠኝ "የብቻዬን ተወኝ" ምልክት ይገባኝ ነበር። አንተ በምንም ሁኔታ ውስጥ የጌታ ነህ። ራስህን "ዕብድ ነኝ" በሚል ቃል ባትገልጽ ደስ ይለኛል። ማንኛውም ሰው የተለያየ የሰውነቱን ክፍል አሞት መድኅኒት እንደሚወስድ ያንተም ችግር እንዲሁ ነው።

እሱ፦ ሽሜ፣ "ዕብድ ነኝ" ያልኩት ህመሜ ከአእምሮ ጋር የተያያዘ ስለሆነ እንጂ በእርግጥም ሙሉ በሙሉ ያበድኩ ዓይደለሁም። ማን ያውቃል ይኼ ነገር እግዚአብሔር በእኔ ላይ ያጠለቀው ሕይወቴን የሚገራበት ልጓም ሊሆን ይችላል። እኔ እንደዛ አድርጌ ነው የማስበው። የሆነብኝን ነገር በክርስቶስ ኢየሱስ ካገኘሁት ዘላለማዊ ድኅነት ጋር ሳስተያየው ምንም እንዳልሆነ አስባለሁ። ያለ ጌታ በሰው ሀገር ያሳለፍኩትን ከባድ ሕይወት አጫውቼሃለሁ ....

አምላኬን እወደዋለሁ፤ ሁሌም እጸልያለሁ። አሁን እናቴን ትንሽ አሟት ልጠይቃት መጥቼ ነው እንጂ እህቴጋ ነው ያለሁት። ሳንተያይ የቀረነው ለዚያ ነው። እዚህ ከነበርኩበት ጊዜ ይልቅ እህቴጋ በነጻነት ድምጼን አውጥቼ የመጸለይ ዕድል አግኝቻለሁ። እናቴም ብትሆን እንዳልጸልይ አትከለክለኝም ነበር። አሁን ጥሩ ሁኔታ ላይ ነኝ።
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨

እንዲህ ዓይነቱ የእምነት ጽናትና የመንፈሳዊ ሕይወት ብርታት በዚህ ዘመን የአየር ክልሉን ከተቆጣጠሩት "ሁሉ በእጄዎች" እና "መልስ በኪሱዎች" የተሰወረ የመንፈሳዊ ከፍታ ሚስጥር ነው። በጤንነት እና በብልፅግና መኖር የእግዚአብሔር ህላዌ ማረጋገጫ እንደሆነ ተደርጎ በሚሰበክበት በዚህ ዘመን እምነትን በሌላ ገፁ የሚያሳዩን፣ እንደዚህ ወንድሜ እንደ ደመና የከበቡን ብዙ ምስክሮች ስላሉን በዚህ ደስ ይለኛል።

ሽመልስ ይፍሩ
@nazrawi_tube