Get Mystery Box with random crypto!

ወንጌል ምንድን ነው? (ከቴብል ወግ ፌስቡክ ፔጅ የተወሰደ) በዶ/ርበርክ ፓርሰንስ የአሥራ ዘጠ | ናዝራዊ Tube

ወንጌል ምንድን ነው? (ከቴብል ወግ ፌስቡክ ፔጅ የተወሰደ)
በዶ/ርበርክ ፓርሰንስ

የአሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፕሪንስተን የሥነ መለኰት ሊቁ ቻርለስ ኾጅ፣ "ወንጌል ትናንሽ ልጆች ሊረዱት የሚችሉት በጣም ቀላል ሲሆን፤ በአንጻሩ ደግሞ ምጡቅ የሆኑት የሥነ መለኰት ጠቢባን በውስጡ ያለውን ሀብት ጨርሰው ሊያውቁት የማይችሉት ነገር ነው" ብሏል። ወንጌል አምነናል ብለን ለምንላቸው ነገሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ መሠረታዊ ነገር ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የክርስቲያንነታችን ምንነት እና ማንነት ማዕከላዊ እምብርት ነው። ነገር ግን፣ ብዙ አማኝ ክርስቲያኖች "ወንጌል ምንድን ነው?" ለሚለው ቀላል ጥያቄ መልስ ለመስጠት ይቸገራሉ። በማስተማር ላይ ሆኜ ተማሪዎቼ ወንጌል ምን እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ትክክለኛ ማብራሪያ መስጠት ኣለመቻላቸው በጣም ይገርመኛል። ከዚህም ባለፈ፣ ወንጌል ምን እንዳልሆነም መግለጽ ይቸግራቸዋል። ወንጌል ምን እንደሆነ ካላወቅን፣ እኛ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ በጣም የምናሳዝን ምስኪኖች ነን። ምክንያቱም ወንጌልን የማስረዳት አቅም ከሌለን፣ በምስክርነት ወንጌሉን ሰብከን ምናልባት ኃጢአተኞች ደኅንነትን ያገኙ ዘንድ ማድረግ ኣንችልም ማለት ነው። እንዳውም እኛው እራሳችንም እንኳን ደኅንነትን ላናገኝ እንችል ይሆናል።

በጊዜያችን ለቊጥር የሚታክቱ ሐሰተኛ ወንጌሎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥም ሆነ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ አሉ። በክርስቲያን ቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና በክርስቲያን የመጻሕፍት መደብር መደርደሪያዎች ላይ ያሉት ብዙዎቹ ነገሮች ወንጌልን ሙሉ በሙሉ የሚያጨልሙ ናቸው። በዚህም፣ እነዚህን ነገሮች ጭራሽ ወንጌል ያልሆኑ ልዩ ወንጌል ያደርጋቸዋል። ሰይጣን ወንጌልን ሊያጠፋው ስለማይችል፣ ጄሲ ራየል እንደጻፈው "በመደመር፥ በመቀነስ ወይም በመተካት ብዙ ጊዜ ጠቃሚነቱን ዋጋ ቢስ ያደርገዋል።" አንድ ሰባኪ ስለ ኢየሱስ፣ ስለ መስቀሉ እና ስለ መንግሥተ ሰማያት ስለተናገረ ብቻ ወንጌልን እየሰበከ ነው ማለት እንዳልሆነ ማስተዋል በጣም አስፈላጊ ነው። እንደዚሁም ሁሉ፣ በየጥጋ ጥጉ ቤተ ክርስቲያን ስላየንም በየጥጋ ጥጉ ወንጌሉ እየተሰበከ ነው ማለትም ኣይደለም።

በመሠረቱ ወንጌል ዜና ነው። የምሥራች፣ መልካም ዜና ነው—የምስራቹም ሥሉሱ አምላካችን በጸጋ ለሕዝቡ ስለ አከናወነው ሥራ ነው። እርሱም፦ አብ ወልድን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሥጋ የለበሰው አምላክ መላኩ፤ እርሱም በፍጹምነት መኖሩ፣ ሕግን መፈጸሙና መሥዋዕት ሆኖ መሞቱ፤ ለኃጢያታችን ስርየትን ማድረጉ፣ በዘላለማዊ ሞት እንዳንጠፋ በላያችን የነበረውን የእግዚአብሔርን ቊጣ እንዲከልከል ማድረጉ፣ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከሞት መነሣቱ ነው። ወንጌል እግዚአብሔር ኃጢያተኞችን እንደሚያድን አመልካች የድል አዋጅ ነው። ምንም እንኳን የኢየሱስ ጥሪ “መስቀሉን ተሸክመህ ተከተለኝ”፣ “ንስሐ ግባ እንዲሁም እመን”፣ “እራስህን ካድ”፣ “ትእዛዛቴን ጠብቁ” የሚሉት የወንጌሉን አዋጅ በቀጥታ የሚከተሉ ትእዛዛት ቢሆኑም፤ እነዚህ ግን በእራሳቸው ኢየሱስ ያከናወነው የምሥራች ኣይደሉም። ወንጌል እግዚአብሔር እኛ ጋር ለመድረስ እንዴት ሁሉን ነገር ለበጎ እንዳደረገው የሚያሳይ ታላቅና ክቡር መልእክት እንጂ—እግዚአብሔር ጋር ለመድረስ በብርታት እንድንጥር ጥሪን የሚያቀርብ ኣይደለም። ወንጌል ጥሩ ዜና የምሥራች ነው እንጂ ጥሩ ምክር ኣይደለም። ጄ ግራሻም ማከን እንዲህ ብሎ ጽፏል፦ "ከሁሉ በፊት የሚያስፈልገኝ ነገር ወንጌሉ እንጂ ልባዊ ምክር ኣይደለም። እግዚአብሔር እንዴት እንዳዳነኝ እንዳውቅ እንጂ፣ ራሴን እንዴት እንደማድን መመሪያን ማግኘቴ ኣይደለም። አንዳች የምስራች አለህን? የምጠይቅህም ጥያቄ ያንን ነው።”

@nazrawi_tube