Get Mystery Box with random crypto!

የእግዚአብሔር የመስቀል ማሕተም! ሐዋርያው ዮሐንስ የፍቅር እርግጠኝነትን የሚያስረዳው ፍቅር በእኔ | ናዝራዊ Tube

የእግዚአብሔር የመስቀል ማሕተም!

ሐዋርያው ዮሐንስ የፍቅር እርግጠኝነትን የሚያስረዳው ፍቅር በእኔ መውደድ ሳይሆን በእግዚአብሔር መውደድ እንደሆነ በማሳየት ነው (1ዮሐ 4፥10)። የእግዚአብሔር መውደድ ደግሞ ልጁን የኅጢአት ማስተሰረያ ይሆን ዘንድ በመስቀል ላይ በሚኖር መከራ አዋለው።

መቼም ለፍቅር መስቀልን መምረጥ ከሚከስተው መጥፎ ምስል አንጻር ትክክል አይመስልም። ሮማውያን በመስቀል መሰቀልን በራሳቸው ዜጎች ላይ እንዳይፈጸም በህግ ከልከለዋል። ከዜጎቻቸው ሕሊና ምስሉን ለማራቅም ይተጉ ነበር። መስቀል በጣም ዘግናኝ የመግደያ መንገድ ነው። የሚፈጥረው ስቃይና ጣር ከፍተኛ ነው። ጣሩ ብቻ ሳይሆን መሰቀያ ቦታው ራሱ የሞት ድባብ የሚያደባበት ነበር።

እግዚአብሔር ፍቅሩን በዚህ መንገድ ገለጸ። «መድቀቁና መሠቃየቱ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፤ እግዚአብሔር ነፍሱን የኀጢአት መሥዋዕት ቢያደርገውም እንኳ» (ኢሳይያስ 53:10)። ልጁን አሳልፎ ለመስቀል ሞት ሰጠው። በዘመኑ በነበረው የመጨረሻው የጭካኔ ግድያ ክርስቶስ ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ። በኢየሱስ ስቃይና ጣሩ ውስጥ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አሳየ። አለም ደካማ ባለችው መንገድ እግዚአብሔር ፍቅሩንም ጽድቁንም እውን አደረገ።

የእግዚአብሔር ትድግና አንድያ ልጁን በመስቀል በመስጠት ተገለጠ። ትድግናውን በአጀብ ሳይሆን በውርደት መስቀል ላይ ፈጸመ። በኅጢአቱ አመጽ የተመታው አለም አመጹን በሙሉ ክርስቶስ ላይ በማኖር የማስተሰርያ መስዋእት አድርጎ አቅርቦታል (ሮሜ 3፥25)። በደካማው መንገድ ብርቱው ጠላት ተረታ፥ ድነትና ትድግናም ተበሰረ።

በመስቀሉ ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ታረቅን፣ ቀረብን፣ ተቀባይ ሆንን። ፍቅሩንም ጽድቁንም እግዚአብሔር ገለጠልን! እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ላይ በሰራው ስራ ርቀን የነበርነውን ታርቆናል!

በክርስቶስ ኢየሱስ፣ አምላክ-ሰው ስቃይና ህማም በኩል የጸጋውን ባለጠግነት ተገልጧል። ለእኛ ለምናምን መስቀሉ የእግዚአብሔር መውደድ ማህተም ነው!

አማኑኤል አሰግድ
@nazrawi_tube