Get Mystery Box with random crypto!

የኢየሱስ የመስቀል ላይ ንግግሮች፣ በአማኞች ወደ መስቀሉ የሚደረጉ ጸሎቶች ናቸው! 1. የመጀመሪያ | ናዝራዊ Tube

የኢየሱስ የመስቀል ላይ ንግግሮች፣ በአማኞች ወደ መስቀሉ የሚደረጉ ጸሎቶች ናቸው!

1. የመጀመሪያው የኢየሱስ የመስቀል ላይ ንግግር

ሉቃስ፡23፡ 33-34፤ ቀራንዮም ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ በዚያ እርሱን ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኝ ሁለተኛውንም በግራ ሰቀሉ። 34፤ ኢየሱስም። አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ።

ጸሎት፦ ምን ብለን እንጸልይ ጌታ ሆይ እኛም እያወቅን በድለን እነርሱም እያወቁ በደሉን፣ ለነገሩ የሁላችን እውቀት ጥላቻ ነው እንጂ ፍቅር የለበትም። ለገዳይ ማላጅ መሆን ካንተ የሚሰጥ ስጦታ ነው፣ ለእስጢፋኖስ ሰጠኸው እባክህ ለእኛም ስጠን፣ “የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” እንድንል፣ በቁም ለሚሰቅሉን ይቅር ማለትን አስተምረን። መጀመሪያ ስታስተምረን “እኛ” ብለን እንድንጸልይ እንዳስተማርከን “የበደሉንን ይቅር እንደምንል” ብለን ስንጸልይ ድምጻችን እንዳያንስ የበደሉን እስኪሰሙን የበደልናቸውንም እስክንሰማ በቂ የይቅርታ ድምጽ ስጠን! አሜን እንበል!

2. ሁለተኛ የኢየሱስ የመስቀል ላይ ንግግር

ሉቃስ 23: 39 - 43 ከተሰቀሉት ከክፉ አድራጊዎቹም አንዱ። አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን ብሎ ሰደበው። 40፤ ሁለተኛው ግን መልሶ። አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? 41፤ ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም ብሎ ገሠጸው። 42፤ ኢየሱስንም። ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው። 43፤ ኢየሱስም። እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው።

ጸሎት፦ በአንተ ፊት ኃጢአት በተባለ ወንጀል የማንጠየቅ የለንም፣ ካንተ ካገኘነው ውጪ የተሰማን ነጻነት ካለ ፈትሸን፣ በመስቀል ጎዳና እለት እለት አብረንህ ስንሰቀል አንተ የእኛ ዓይነት እንዳልሆንክ እንድናውቅ እንደዚህ አብሮ ተሰቃይህ ዓይነት ሰው፣ ፈጣን ጸሎት አስተምረን፣ እኛ በኃጢአታችን፣ አንተ ለጽድቃችን፣ መሰቀልህን አውቀን “ዛሬ በመንግሥትህ አስበን” እንድንል እርዳን! አሜን እንበል! ።

3. ሶስተኛ የኢየሱስ የመስቀል ላይ ንግግር

ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር። 26፤ ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን። አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት። 27፤ ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን። እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት። ዮሐ. 19:26-27

ጸሎት፡ እናትነት መውለድ ብቻ ሳይሆን ከሥራ ሁሉ የሚበልጥ ሥራ ነው ፣ ይህንን ለእናቶች ስለ ሰጠህ እናመሰግንሀለን፣ አቤቱ ለእናቶች ጸጋን ስጥ! “ይህችን እናትም እነሆ” መባልም ከውርስ የሚበልጥ አደራ ነው፣ አቤቱ ለልጆች የእናትዬን ዐደራ እንዳይበሉ ጸጋን ስጥ። ለሁላችን የቤትህ ሥራ የዐደራ ሸክም ይክበድብን፣ ጌታ ሆይ ዐደራን የሚበላውን ክፉ ሐሳባችንን የአንተን ራስ የወጋው እሾህ ይውጋው፣ አደራ መቀበልን ከዮሐንስ አስተምረን፣ ማሪያም በስሟ ሳይሆን በስራዋ እንደተጠራች እኛንም በሥራችን ጥራን፣ ያን ጊዜ አደራችን ይገባናል፣ አሜን እንበል!
4. ዐራተኛ የኢየሱስ የመስቀል ንግግር
ማቴ. 27 45፤ ከስድስት ሰዓትም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። 46፤ በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም። አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው። 47፤ በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው። ይህስ ኤልያስን ይጠራል አሉ።
ጸሎት፦ ሁሉን የምትገዛ ያለኽ የነበርህ እውነተኛና ጻድቅ የሆንህ ጌታ እግዚአብሔር ፣ ሊመለስ በማይችል የመስቀል መከራ ውስጥ ስናልፍ፣ ወደማይመለከተው እንዳንጸልይ እርዳን፣ ሁላችን ስለ ክርስቶስ ይህንን የመስቀል ጽዋ ስናልፍበት “አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ብሎ መጸለይ ካንተ ጋር መነጋገሪያ መክፈቻ ቃል እንጂ ማጉረምረም እንዳልሆነ ይግባን። አሜን እንበል!

5 አምስተኛ የኢየሱስ ንግግር
ዮሐ.19:28 “ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አሁን ሁሉ እንደተፈጸመ አውቆ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ። ተጠማሁ አለ። 29፤ በዚያም ሆምጣጤ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው በሁሶፕም አድርገው ወደ አፉ አቀረቡለት።”

ጸሎት፦ ጌታ ሆይ እኛ ቢጨምቁን የሚወጣን ሆምጣጤ ነው፣ የሕይወትን ውሃ በልባችን አብዝተህ ካላፈሰስክ ሌላም የለን፣ ይህን ለማለት እንኳ ኩራታችን ይተናነቀናል፣ አንተ የሕይወት ምንጭ ሆይ ፍለቅ፣ እባክህ ፍለቅ ከሆምጣጤ እንድንላቀቅ! አሜን እንበል!
6. ስድስተኛ የኢየሱስ የመስቀል ላይ ንግግር

ዮሐ. 19፡ 30፤ ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ። ተፈጸመ አለ፥

ጸሎት፦ እንደ ሔሮድስ አንተን ስናይ ደስ የሚለን ምልክትህን ፈልገን እንዳይሆን፣ ዝም ስትል እንዳንዘብትብህ፣ ስንፈልግህ ልትፈጽም የመጣኸውን ፈልገን እንከተልህ፣ የአንተ መንገላታት አንተ ለሌለህበት አጀንዳ አንዳይሆንብን እርዳን፣ በፈጸምከው ሥራ ላይ የእኛን ሥራ ስንደርት እንዳንገኝ ባሪያዎችህን በተፈጸመው ስራህ ውስጥ ማረፍን አስተምረን! አሜን እንበል!

7. ሰባተኛ የኢየሱስ የመስቀል ላይ ንግግር

ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፥ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፥ ፀሐይም ጨለመ፥ 45፤ የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ። 46፤ ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ። አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ። 47፤ የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። 48፤ ይህንም ለማየት ተከማችተው የነበሩ ሕዝብ ሁሉ፥ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ።

ጸሎት፡ - ሁሉ ባለቀ ጊዜ የከበረው ነገራችንን ራሳቸውን ማዳን ለማይችሉ አሳልፈን እንዳንሰጥ እርዳን - አቤቱ ላንተ ኖረን በመሞት ስለአንተ ሞተን መኖርን አስተምረን፡ ጌታ ሆይ እንኳን ስንሞት አሁን በሕይወት እያለን ነፍሳችንን በእጅህ አደራ እንሰጣለን፡፡ አሜን እንበል!

ሰለሞን ጥላሁን
@nazrawi_tube