Get Mystery Box with random crypto!

ሪቫይቫል ምንድን ነው? ምንስ አይደለም? ከተስፋዬ ሮበሌ (ከ4 ዓመታት በፊት የተለጠፈ) (1) | ናዝራዊ Tube

ሪቫይቫል ምንድን ነው? ምንስ አይደለም?
ከተስፋዬ ሮበሌ (ከ4 ዓመታት በፊት የተለጠፈ)

(1) "የሪቫይቫል" ቀዳማይ ግብ፣ የሕይወት ለውጥና የነፍሳት ድነት እንጂ፣ ልሳንና ተኣምር አይደለም! የጸጋ ስጦታዎችም ቀዳማይ ግብ፣ እውነተኛ የሕይወት ተሐድሶና የሰዎች ድነት (ሰዎች ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኛቸውና ጌታቸው መቀበላቸው) ነው!

(2) "ሪቫይቫል" ነገን እውን ይሆናል ብለን የምንጠብቀው ክሥተት ሳይሆን፣ ዛሬን የምንተገብረውና የምንኖረው ክርስቲያናዊ ሕይወት ነው! እውነተኛ የሕይወት ለውጥና የነፍሳት ድነት ባለበት ቦታ ሁሉ "ሪቫይቫል" አለ:: ይህ በሌለበትም ቦታ "ሪቫይቫል" የለም!

(3) ዛሬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በልዩ "በሪቫይቫል" ውስጥ ነች የሚሉ ሰዎችን አስተሳሰብ በጭራሽ አልጋራም:: ምክንያቴም አንደኛ እነርሱ "ሪቫይቫል" የሚሉትን ሁካታ መጽሐፍ ቅዱስ "ሪቫይቫል" ስለማይለው:: ሁለተኛ ከየትኛውም የታሪክ ጊዜ ይልቅ የክርስቶስ ወንጌል የተነቀፈበት ይህ ወቅት "ዘመነ ሪቫይቫል" ሊሆን አይችልም (በእኔ የድነት ዘመን ማለቴ ነው):: ሦስተኛ በርካታ ሰዎች ወደ ትክክል ወዳልሆነ ሃይማኖትና ወደተሳሳተ እምነት እየጎረፉ ያሉበት ወቅት በመሆኑ::

(4) "ሪቫይቫል" የመጻኢ ዘመን ክሥተት ነው ብለው ያስተማሩ ሰዎች ጎዳና ስተው ሕዝብን አስተው የተገኙት "ሪቫይቫል" የመጻኢ ዘመን ክሥተት ነው በሚለው ጠማማ አስተሳሰባቸው ምክንያት ነው!

(5) ሐዲስ ኪዳን "በመጨረሻው ዘመን" መንፈሳዊ ተሐድሶ ይሆናል ሲለን፣ ዘመነ ሐዲስን በጥቅሉ የሚጠቅስ እንደ ሆነ ልብ ይሏል! ስለዚህ ነገ "ሪቫይቫል" ይሆናል የሚለው አስተሳሰብ ለአውሬውና ለአባይ ነባዮቹ እየዳረገን እንደሚገኝ ልብ ይሏል! (according to Historical Premillennialism OR Dispensationalism Theology ከሺህ ዓመቱ በፊት ያለው መጻኢ ዘመን ብሩህ አይደለም)::

(6) እግዚአብሔር አምላክ ለኢትዮጵያውያን ብቻ አመጣለሁ ያለው "ሪቫይቫል" የለም! አምላክ ሕዝቦችን ሁሉ የሚያውቀው በክርስቶስ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ አማካይነት ብቻ ነው! በዚህ አግባብ ኢትዮጵያውያንና ኬኒያውያን ወይም የግብፅ ክርስቲያኖች አንዳችም ልዩነት የላቸውም:: ኢትዮጵያ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ተደጋግማ መጠቀሷ ጥንታዊት አገር መሆኗን እንጂ በክርስቶስ ቤዞታዊ ሥራ ውስጥ ልዩ ቦታ እንዳላት ሊያሳይ አይችልም! "ለማርያም በዐሥራት የተሰጠች ነች" ወይም "ኢትዮጵያውያን ልዩና ምርጥ ሕዝቦች ናቸው" የሚለው አስተስሰብ መንፈሳዊ ዘረኝነት ነው (መንፈሳዊ "ወያኔነት" ነው)! በቅዱሳት መጻሕፍት ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከተጠቀሰው በላይ ባቢሎን፣ ግብፅ፣ ሮም ፣ ግሪክ...የሚሉ ስሞች በስም ተጠቅሰዋል:: በብዛት መጠቀሳቸው በክርስቶስ ድነታዊ ውጀት ውስጥ ልዩ ጥቅም ወይም ቦታ እንዳላቸው በጭራሽ አያሳይም! ያለመጠቀስም ከድነት አያጎድልም—ለምሳሌ አገረ አሜሪካንን ይመለከቷል:: አልተጠቀሰችም ግን የጠንካራ ሚስዮናውያን እናት ምድር መሆኗን ማን ይክዳል? (ለበለጠ ማብራሪያ "አባይ ነባይ" መጽሐፍን ይመለከቷል)::

(7) ሁሌም ተኣምራት ሰዎችን ወደ መንፈሳዊ ለውጥም ሆነ ብስለት ያደርሳሉ ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም:: ተኣምራት እውን ስለሆነ ብቻ ነፍሳት ዳኑ የዳኑትም ታነጹ ማለት አይቻልም:: ለምሳሌ ከግብፅ የወጣው የእስራኤል ሕዝብ በተኣምር ባሕር ሲከፈል ማየቱና ሰማያዊ መና መብላቱ የጥጃ ጣዖት ሠርቶ ከግብፅ ባርነት ዐርነት ያወጣኝ ይህ ጥጃ ነው ከማለት አላቀበውም:: "ከሙታን መኻል አንዱ ሄዶ ክርስቶስን ቢሰብክላቸው ቤተሰቦቼ ያምኑ ነበር" ያለውን ሰው፣ ስብከተ ወንጌልን የማያምን ሰው፣ ተኣምራትን ሊያምን እንደማይችል ወንጌል በግልጽ ነግሮታል:: ስለዚህ ተኣምራት ባለበት ቦታ ሁሉ የነፍሳት ድነትና የሕይወት ለውጥ አለ የሚለው አስተሳሰብ ትክክል አይደለም::

(8) "ሪቫይቫል" በአምላክ በጎ ፈቃድና እርሱን ከልብ በመሻት እውን የሚሆን እንጂ፣ በሰዎች ክህሎትና በግርግር የሚፈጠር አይደለም! ያልሆነን ሆነ ብሎ ማውራት የሐሰት ምስክሮች እንጂ የወጌል ዐርበኞች አያደርገንም::

(9) "ሪቫይቫል" በእግዚአብሐር መንፈስ ረዳኢነት እውን ክሥተት በመሆኑ ምክንያት፣ በመንፈስ ቅዱስ ነጂነት (አፊዎትነት) እውን የሆኑትን የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት የሚያስወድደን እንጂ፣ እርሱን ጥለን ነባዮችን እንድናሳድድ የሚያደርገን አይደለም! እንግዲያው ቅዱሳት መጻሕፍትን ማጥናትና ማስጠናት "የአእምሮ ሰው" የሚያሰኝ "ሪቫይቫል" ጤናማ ሊሆን በጭራሽ አይችልም:: በውኑ አምላክ ያሰበልንን ነባዮች ያስቀሩብናልን? ያላሰበልንንስ እጅ ጠምዝዘው ሊሰጡን ይችላሉ? እንግዲያው መንቀዥቀዡ ከምን የመነጨ ይሆን?

በአጭሩ እነዚህን ዘጠኝ ነጥቦች ያለማወቅና በዚህ እንጻር ያለመኖር:- (1) በአባይ ነባዮች ይስበላል! (2) ተኣምራት ናፋቂ ያደርጋል (3) ቅዱሳት መጻሕፍትን እያነበቡና እይተነተኑ ከመኖር ይልቅ በአባይ ነባዮች የውሸት ትንቢትና መገለጥ እንድንዳረግ ያደርጋል (4) መንፈሳዊ "ወያኔነት" (ዘረኝነት) እንዲጣባን ዕድል ይሰጣል:: ወዘተና ወዘተ

ይህ እኔ ስለ "ሪቫይቫል" ያለኝ አንቀጸ ሃይማኖት ነው! ይህን ሐቅ እንደ አሸንክታብ ዐንገቴ ላይ አንጠልጥዬው እንደምኖር፣ እንደምሰብከው፣ እንደማስተምረው... ታቅፌው እንደምሞት ዓለም ይወቅልኝ!

ሠናይ ውእቱ