Get Mystery Box with random crypto!

“የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን።” (የሐዋ. 21፥14) ይሄን ጥቅስ ታክሲ ላይ ወይም ቤት | ናዝራዊ Tube

“የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን።” (የሐዋ. 21፥14)

ይሄን ጥቅስ ታክሲ ላይ ወይም ቤት ውስጥ ተለጥፎ ማየት ብርቅ አይደለም። የሰርግ ካርድ ላይ ተጽፎ ማንበቤን ግን መቼም የምረሳው አይመስለኝም። የሰርጉ ጠሪዎች የሙሽሪት ወላጆች ናቸው፤ በባል ምርጫዋ እንዳልተስማሙ በጨዋ መንገድ እየነገሩን ነበር።

ይህ ጥቅስ፣ ከሐዋርያው ጳውሎስ የኢየሩሳሌም ጉዞ ጋር የተገናኘ ነው። አንዳንዶች ጳውሎስ ለእስር የተዳረገው የመንፈስ ቅዱስን ምሪት አልቀበል ብሎ፣ የወዳጆቹን ምክር ንቆ፣ መከራ ናፍቆ ወይም በጀብደኛነት ይመስላቸዋል። እውነቱ ግን ከዚህ የራቀ ነው። ነገሩ እንዲህ ነው፦

ቅዱስ ጳውሎስ በዐለ አምሳን በኢየሩሳሌም ለማሳለፍ ጥድፊያ ላይ ነበር (የሐዋ. 20፥16)። በዚህ ጥድፍያው ላይ ሳለ የኤፌሶንን ሽማግሌዎች ለስንብት አስጠራቸው። በስንብት ንግግሩ ውስጥ፣ “አሁንም፣ እነሆ በመንፈስ ታስሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፤ በዚያም የሚያገኘኝ ምን እንደ ሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ፦ እስራትና መከራ ይቆይሃል ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰክርልኛል” የሚል ሐሳብ ነበረበት (20፥22-23)። በዚህ ስፍራ፣ “በመንፈስ ታስሬ” የሚለውን ሌሎች የአማርኛ ትርጉሞች፣ “በመንፈስ ቅዱስ ታዝዤ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዴ ነው” (አት)፤ “መንፈስ ቅዱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንድሄድ ግድ እያለኝ ነው” (አ.መ.ት) ብለውታል።

ከዚህ እንደምንረዳው፣ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ እየጎተጎተው ያለው መንፈስ ቅዱስ ነው። በኢየሩሳሌም ምን እንደሚገጥመው ርግጠኛ ባይሆንም፣ እስራትና እንግልት እንደሚጠብቀው በሄደባቸው ከተሞች ሁሉ ወገኖች ሲነግሩት ነበር። ከዚህ በመነሣት ጳውሎስ ከእስራትም በላይ ሞትም ሊገጥመው እንደሚችል ያስብ እንደ ነበር የምንገነዘበው ለስንብት የጠራቸውን ሽማግሌዎች፣ ከዚህ በኋላ ፊት ለፊት እንደማይተያዩ ሲነግራቸው ነው (ቁ. 25)።

ከዚህ ሁለት ነገሮችን እንወስዳለን። በመጀመሪያ፣ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ መንፈስ ቅዱስ ግድ ብሎታል። ከዚያም፣ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ በሚያልፍባቸው ከተሞች የሚያገኛቸው ወገኖች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው እስራትና መከራ እንደሚጠብቀው ይነግሩት ነበር። (ነቢዩ ኤልያስ እንደሚነጠቅ በየከተማው ያሉ የነቢያት ልጆች ያውቁ እንደ ነበር፣ ስለ ጳውሎስ እስር አይቀሬነት በየከተማው ያሉ ወገኖች በመንፈስ ተረድተው ነበር!) ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለት ከተሞች የገጠሙት ተመሳሳይ ጉዳዮች በሚቀጥለው ምዕራፍ ተጠቅሰዋል።

የመጀመሪያው፣ በጢሮስ ከተማ የገጠመው ነው። በዚያ ያገኛቸው ወገኖች፣ “ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ በመንፈስ አሉት” (21፥4)። ማለትም፣ “በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ጳውሎስን ‘ወደ ኢየሩሳሌም አትሂድ!’ ብለው ነገሩት (አት)። “በመንፈስ ሆነው ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ነገሩት” (አመት)። እዚህ ጋ ያለው ሐሳብ ለትርጉም አስቸጋሪ ቢሆንም፣ እንደሚከተለው ብንቀበለው ተገቢ ይሆናል፤ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ምን እንደሚገጥመው መንፈስ ቅዱስ ለእነዚህ ወገኖች ገልጦላቸዋል። ጳውሎስ ወደዚያ እንዳይሄድ የሰጡት ምክር ግን የወዳጅነት ምክር እንጂ፣ የመንፈስ ቅዱስ ሐሳብ አልነበረም። ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ ግድ ያለው መንፈስ፣ በእነርሱ በኩል ደግሞ “አትሂድ” ሊለው አይችልምና። ምክራቸው ጥሩ ምክር ነበር፤ ጥሩ ምክር ግን የእግዚአብሔር ሐሳብ ላይሆን ይችላል!

ሐዋርያው ጳውሎስ እነርሱን ተለይቶ ከተጓዘ በኋላ ወደ ቂሳርያ ደረሰ። በቂሳርያ ደግሞ አጋቦስ የሚባል ነቢይ፣ ጳውሎስ በአይሁድ ተይዞ በአሕዛብ (በሮማውያን) እንደሚታሰር በድራማዊ መንገድ ለሁሉ ገለጠ (21፥10-11)። አጋቦስ ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበለውን ትንቢት ተናገረ እንጂ፣ “ወደ ኢየሩሳሌም አትሂድ” የሚል ምክር ለጳውሎስ አላቀረበም። ይህ ብስለት ነው! የአጋቦስን ትንቢት የሰሙ ወገኖች ግን፣ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ በልቅሶ ለመኑት። ከመካሪዎቹ መካከል ወንጌላዊ ወዳጁ ሉቃስም ነበረበት። ጳውሎስ ግን እንኳን እስራት ሞትም ቢጠብቀው ወደ ኢየሩሳሌም ከመሄድ እንደማይታቀብ ቁርጡን ነገራቸው (ቁ. 12-14)። ያኔ፣ “የጌታ ፈቃድ ይሁን” በማለት ዝም አሉ፤ በቅሬታ። የሆነውም ይኸው ነው!

ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም የሄደው መከራን ስለ ናፈቀ ወይም የሰዎችን ምክር ስለማይቀበል አልነበረም። ምክንያቱም ወደ ኢየሩሳሌም ከደረሰ በኋላ፣ ከአይሁድ የሚቀርብበትን ተቃውሞ የሚያለዝብበት ምክር በቅዱስ ያዕቆብና በኢየሩሳሌም የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሲቀርብለት ተቀብሎ ተግብሯልና (የሐዋ. 21፥17-26)። ስለዚህ ነገሩ እንዳይከር ይፈልግ ነበር ማለት ነው፤ የሰዎችን ምክርም ይቀበል ነበር። ነገር ግን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ መንፈስ ቅዱስ የሰጠውን ምሪት ግን ከመቀበል ወደ ኋላ የሚል ሰው አልነበረም!

በአገልግሎት መንገዳችን ላይ ችግር እንደሚገጥመን እግዚአብሔር አስቀድሞ የሚናገረው ከስፍራው እንድንሸሽ ሳይሆን፣ ችግሩን አስበንና ተዘጋጅተን እንድንጋፈጠውም ሊሆን ይችላል።

አንዳንዴ ይህንም ማሰብ ያስፈልገናል!

@PaulosFekadu
@nazrawi_tube