Get Mystery Box with random crypto!

በጎጃም የተደረገው ሕግ ማስከበር ውጤታማ መሆኑን የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ እና የምስራቅ ዕዝ ዋና አ | Natnael Mekonnen

በጎጃም የተደረገው ሕግ ማስከበር ውጤታማ መሆኑን የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ እና የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ አረጋገጡ ።

የጎጃም ኮማንድፖስት የመጋቢት ወር የስራ አፈፃፀም ግምገማ በፍኖተ ሰላም ከተማ ባካሔደበት ዕለት ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ እንደተናገሩት ፣ በወሩ ውስጥ የተከናወኑት የኦፕሬሽን ፣ የማዳበሪያ ስርጭት ፣ የጸጥታ ሀይል የማደራጀት እና ሌሎች ተግባራት ለውጥ አስገኝተዋል ።

በመጋቢት ወር በጎጃም በሚገኙ 66 ወረዳዎች የተሰማራው ሠራዊት እና የአማራ ክልል የፀጥታ ሀይል 594 ጽንፈኞችን በመደምሰስ ፣  232 አቁስሏል በርካቶች ደግሞ እጃቸውን በሰላም ሰጥተዋል ።

በማዳበሪያ ስርጭት ፣ በምዕራብ ጎጃም 105 ሺህ ኩንታል ፣ በምስራቅ ጎጃም 223 ሺህ 761 ኩንታል ፣ በሰሜን ጎጃም 281 ሺህ 971 ኩንታል ፣ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደርም 157 ሺህ 252 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መከፋፈሉ በግምገማው ተገልጿል ።

የፀጥታ ሀይል በማደራጀት በኩልም በወሩ ውስጥ 11 ሺህ 151 ሰላም አሰከባሪ ፣ ሚሊሺያ እና የፖሊስ ሀይል በአራቱም የጎጃም ዞኖች ተሰልፎ የሕግ ማስከበሩ አካል እንዲሆን ተደርጓል ።

በዚሁ ወርሃዊ ግምገማ ላይ የተሳተፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶክተር) እንዳሉት ፣ ኮማንድፖስቱ ያከናወናቸው የሰላም ተልዕኮዎች ለግብርናውም ሆነ ለሌሎች ዘርፎች ስኬታማነት ቁልፍ ሚና ነበራቸው ።

በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ  አቶ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው ፣ የዕቅድ አፈፃፀሙ ውጤት የሕዝባችንን የሰላም ጥያቄ እየመለሰ የመጣ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ።

ኮማንድፖስቱ በቀጣይ ወረዳዎችን ማጠናከር ፣
የሚደረጉ ስምሪቶች ደምሳሽ እንዲሆኑ ፣ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት እንዲቀላጠፍ ፣ ፖሊስ እና ሚሊሺያ የማደራጀቱ ስራ የበለጠ እንዲጠናከር አቅጣጫ አስቀምጧል ።

በዚሁ የግምገማ መድረክ ላይ የሁሉም ዞኖች ኮማንድፖስት ከፍተኛ አመራሮች እና የከተማ ከንቲባዎች ተገኝተዋል ።