Get Mystery Box with random crypto!

ከጉግል ውጭ መጠቀም የምንችላቸው ‘የመረጃ ማሰሻዎች’ እንዳሉ ያውቃሉ? በአንድ ቀን ስንት ጊዜ ‘ | አዋጅ – Awaje News

ከጉግል ውጭ መጠቀም የምንችላቸው ‘የመረጃ ማሰሻዎች’ እንዳሉ ያውቃሉ?

በአንድ ቀን ስንት ጊዜ ‘ጉግል’ ያደርጋሉ? ጉግል በእያንዳንዱ ሰከንድ 63 ሺህ ጥያቄዎች እንደሚጠየቅ በገጹ ጽፏል። በቀን ውስጥ ወደ 5.6 ቢሊዮን ገደማ ጥያቄዎች ያስተናግዳል።

ብዙዎቻችን ከቃላት ትርጉም አንስቶ ስለማንኛውም ጉዳይ ‘አማካሪያችን’ ጉግል ከሆነ ቆይቷል።

የመረጃ ደኅንነት ባለሙያዎች ግን ጉግል መረጃ ሲሰጠን በምላሹ የእኛን መረጃ እየወሰደ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

የእኛን ማንነት፣ ምን እንደምንወድ፣ ምን እንደምንጠላ፣ ምን ማድረግ እንደምንፈልግ፣ ምን ያህል ገንዘብ ማውጣት እንደምንችል፣ የት መሄድ እንደምናዘወትር ወዘተ ይመዘግባል።

ስለእኛ የሚከማቸው የተደራጀ መረጃ ለማስታወቂያ ድርጅቶች ወይም የተለያየ ምርት ለሚሸጡ ተቋሞች ይሸጣል።

መረጃው የሚሰበሰበው የኢሜይል መገልገያውን ጂሜይልን እና ዩቲዩብን ጨምሮ ከሁሉም ከጉግል ጋር የተያያዙ ገጾች ነው።

ይህ መረጃ፣ የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች በፍላጎታቸው፣ በዘራቸው፣ በዕድሜያቸው፣ በጾታቸው እንዲሁም በሌሎች የማንነት መገለጫዎቻቸው ልክ የተሰፋ ማስታወቂያ (targeted ad) ሰለባ እንዲሆኑ ያደርጋል የሚለው አንደኛው ትችት ነው።

ሁለተኛው ደግሞ የግል መረጃ ለሦስተኛ ወገን ከተላለፈ በኋላ ሰዎች የት እንዳሉ፣ ከማን ጋር ምን እንደተነጋገሩ፣ ምን እንደሸመቱ እና ሌሎችም መረጃዎች በምስጢር አለመያዛቸው ነው።

ትችቶቹ የሚሰነዘሩት ጉግል ላይ ብቻ አይደለም። ሌሎች መረጃ ማሰሻ (search engine) አቅራቢዎች እና የማኅበራዊ ሚዲያ ባለቤቶች ላይም ነው።

ጉግል ግንባር ቀደሙ እና በርካታ ተጠቃሚ ያለው መረጃ ማሰሻ ስለሆነ ነው በትችቱ በዋነኛነት የሚነሳው።

ጉግል ከግል መረጃ አጠባበቅ ጋር በተያያዘ የሚሰነዘርበትን ወቀሳ ተከትሎ ‘የተሻለ አማራጭ አለን’ የሚሉ ሌሎች መረጃ ማሰሻ አቅራቢዎች ወደ ገበያው ገብተዋል። እነሱስ ምን ያህል ይታመናሉ? ሌላ ጥያቄ ነው።

ባለንበት ፈጣን የመረጃ ዘመን የግል መረጃን ምን ያህል ምስጢራዊ አድርጎ መቀጠል ይቻላል? የሚለው አጠያያቂ ነው። ቢያንስ ግን የግል መረጃችንን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በተሻለ ደረጃ የሚጠብቁ ከጉግል ውጭ ያሉ መረጃ ማሰሻዎችን በዚህ ዘገባ እንመለከታለን።

ስለ አማራጭ መረጃ ማሰሻዎች እንዲነግረን የጠየቅነው የአይኮግ ላብስ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ጌትነት አሰፋን ነው። ከ200 በላይ ፕሮግራመሮች ያለው ተቋሙ ላለፉት አሥር ዓመታት ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) እንዲሁም ተያያዥ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ይሠራል።