Get Mystery Box with random crypto!

አላህ አንዳንድ ነገሮችን ድብቅ ያደረጋቸው ለምክንያት እንደሆነ በፅኑ አምናለሁ። ጌታዬ ጥበቡ እና | ABX

አላህ አንዳንድ ነገሮችን ድብቅ ያደረጋቸው ለምክንያት እንደሆነ በፅኑ አምናለሁ። ጌታዬ ጥበቡ እና ዕውቀቱ ፍፁም ነዉና። እሱ የሸፈነው ነገር እንደተሸፈነ ሲኖር ደስ ይላል። በጀሊሉ ሥራና ጥበብ ዉስጥ ሁሌም ጎልቶ የሚነበበብ ትልቅ ትምህርት አለ።

በተፈጥሮ አላህ የደበቃቸዉን ነገሮችን ቀድሞ ለማወቅ መጣር ኋላ ላይ ያን ነገር አሰልቺ እና ጣዕም አልባ ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ። ቴክኖሎጂ ግን ከፀሐይ በታች አዲስ የለም አለና ሁሉን ነገር ገላልጦ አረፈው። የዘመኑ ሰዉም እሱን ተከተለና ነገሮችን ቀድሜ ካላወቅኩ አለና በገዛ እጁ ራሱን በራሱ ረበሸ።
ለምሳሌ - አላህ ልጅ የሠጣቸው ወላጆች በርግዝና ፀጋ የባረካቸዉን አምላካቸዉን በብዙ ከማመስገን ይልቅ የፅንሱን ምንነት ለማወቅና ሽፍኑን ለመግለጥ የሚጣደፉበት ዘመን ላይ ነን። ደስ ቢላቸዉም ባይላቸዉም አላህ የከተበዉን ላይቀይሩ ነገር። ገና አራት ወር ላይ ያለን ፅንስ ፆታው ምንድነው? ብሎ ወላጆችን መጠየቅም የጤና አይመስለኝም።

ዉሃን ሰብስቦና ዘርን አዋህዶ ፅንስን የሚፈጥር፣ በእናቱ ሆድ ዉስጥ ተንከባክቦ የሚያሳድግ፣ ቀኑን ጠብቆ በሰላምም ወደ ምድር እንዲመጣ የሚያደርግ አላህ ነው። የኛ ድርሻ ታላቅ በረከቱን አመስግኖ መቀበል ነው። ወደ ዱንያ መንገድ የጀመረን ልጅ አላህ በሰላምና ጤና ያምጣው። የምንጠቀምበት እንጂ የምንፈተንበት አያድርገው።

የልጅ ፆታን በአልትራሳዉንድ አይተው ካወቁ በኋላ በከፍተኛ ደስታም እና በቀዘቀዝ ስሜት ዜናዉን የተቀበሉ ሰዎችን አየሁ። ከማወቁ በፊት እና በኋላ በወላጆች ላይ የሚታይ ስሜት አንድ እንዳልሆነም ታዘብኩ። ቀዝቃዛው ስሜት የአላህን ፀጋ ማንኳሰስ ነው።

ስለሆነም ከአላህ ስጦታ አንፃር እይታችን መስተካከልና እኩል መሆን አለበት ብዬ አሰብኩ። ልጅን የሚሰጥ አላህ ብቻ ነው። አይደል እንዴ?!። ምንም ይሁን ምን አላህ የሰጠው ነገር ዋጋው መቀነስ የለበትም። የአላህ ስጦታ ግራዉም ቀኝ፣ ቀኙም ቀኝ ነው። በረከቱ ትንሹም ትልቅ፣ ትልቁም ትልቅ ነው። የሱ ሁሉም ፀጋው የሚመሰገን እንጂ አስተያየት የሚሰጥበት አይደለም።

በማኅፀን ያለ ልጅ ተጠቅልሎ የተቀመጠ የአላህ ስጦታ ነው። ስጦታዉን በእጅ ላይ በደረሰ ጊዜ መክፈት የበለጠ ደስ ይላል ወደማለት።

ወላድ ሁሌም በሞገስና በድባብ ትሂድ።

ጧበት ለይለትኩም።


http://t.me/MuhammedSeidABX