Get Mystery Box with random crypto!

የነገ አገር ተረካቢ ህጻናት ላይ መስራት አገርን መገንባት ነው - አቶ ገዛኸኝ ታምሩ ማክሰኞ ነ | M.O.R East Addis Ababa Branch

የነገ አገር ተረካቢ ህጻናት ላይ መስራት አገርን መገንባት ነው - አቶ ገዛኸኝ ታምሩ

ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም (ምስራቅ ገቢዎች)በገቢዎች ሚኒስቴር የምስራቅ አዲስ አበባ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በህፃናት ማቆያ ማዕከሉ ከየካቴት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ሲንከባከባቸው የነበሩ ህፃናትን እድሜያቸው ለትምህርት በመድረሱ ምክንያት የአሸኛኘት መርኃግብር አካሄዷል፡፡

የህፃናት ማቆያ ማዕከሉ በቅ/ጽ/ቤት ደረጃ መገንባቱ የሚያጠቡ እናቶች ልጆቻቸውን በቅርበት እንዲከታተሉ፣ የሴት ሠራተኞችን ጫና በመቀነስ ሙሉ ጊዜቸውን በሥራ ላይ በማዋል ለገቢ አሰባሰቡ አወንታዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ማስቻሉን የቅ/ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ታምሩ በንግግራቸው አመላክተዋል፡፡

ህጻናት አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያገኙና ንቁ ሆነው እንዲያድጉ የህጻናት ማቆያ ማዕከሉ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ የነገ አገር ተረካቢ ህጻናት ላይ መስራት አገርን እንደመገንባት ይቆጠራል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ልጆቻቸውን በማዕከሉ የሚያውሉ ሰራተኞች በሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ወቅት በሰጡት አስተያየት ማዕከሉ በሚሰጠው አገልግሎት ደስተኛ እንደሆኑና የልጆቻቸው በእንክብካቤ መቆየት ስራቸውን በተረጋጋ መንፈስ እንዲሰሩ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል፡፡

ለሰራተኞች ውጤታማነት እና ለልጆች ጤንነት ማዕከሉ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በቅ/ጽ/ቤቱ የሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ድጋፍና ክትትል ቡድን አስተባባሪ ወ/ሮ ኑሪያ አሊ ናቸው፡፡

ማዕከሉ ከስድስት ወር እስከ አራት ዓመት ያሉ 13 ህፃናትን ተቀብሎ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የገለፁት ወ/ሮ ኑሪያ ከእነዚህ መካከል እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሦሥት ህፃናት መሸኘታቸውን አክለዋል፡፡
የህፃናት ማቆያው የካቲት 20 ቀን 2012 ዓ.ም በይፋ ተመርቆ ለ5 ህፃናት አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ከ20 በላይ ለሆኑ ህፃናት አገልግሎት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡