Get Mystery Box with random crypto!

ኦሪት ዘፍጥረት 2፥8-10 8.“እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም | ምክረ አበው

ኦሪት ዘፍጥረት 2፥8-10
8.“እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው።”

#በምሥራቅ :- ፀሐፊው (ነቢዩ ሙሴ) ካለበት አቅጣጫ ማለትም ከሲናይ ወደ ምስራቅ

#በኤደን :- ኤደን የኤፍራጥስና ጢግሪስ ተፋሰስ ሃገራት ሶርያና ኢራቅ እስከ የፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚያጠቃልል ቦታ ነው (ሜሶፖታሚያ)።

#ገነትን ተከለ : - በኤደን የተለየ የአትክልት ስፍራን(garden) ኣደረገ።

9.“እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፥ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፥ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ።”

በምድር ሁሉና በዚያች የተለየች የኣትክልት ስፍራ(ገነት) በአንድነት የተደረገን የእጽዋት ተፈጥሮን ያሳየናል።ምክንያቱም እጽዋት የተፈጠሩት በሶስተኛው ቀን እንደ መሆኑ፥ "አበቀለ" ማለቱም በዚያን ቀን(በሶስተኛው) እንደሆነ ልብ በል።

#የሕይወት _ዛፍ :- የተባለችው አዳም እርሷን ከበላ ሕያው የሚሆንባት ዛፍ ናት።ሕያው የሚሆነውም ስጋና ነፍስ እንዳይለያዩ ስለምታደርግ ነው ምክንያቱም ስጋና ነፍስ የሚለያዩት ስጋ በጉዳት አልያም በዕድሜ ብዛት ለመቆም ብቁ ባልሆነ ጊዜ ስለሆነ ይህች ዛፍ ደግሞ ስጋን አድሳ ሕያው ታደርገዋለች ነፍስን ግን አይደለም ነፍስ ከእግዚአብሔር ባሕርይ እንደመከፈሏ በራሷ ሕያው ናትና።

#መልካምንና_ክፉን_የሚያስታውቀውንም_ዛፍ :- ይህ ዛፍ በውስጡ የዕውቀት ሐይል ኖሮት አይደለም።ነገር ግን ባይነካው ፍጥረታት ሁሉ መልካም እንደሆኑ የተፈጥሮን መልካምነት ብቻ ያውቃል ቢበላው ደግሞ መቀጣትን መጎስቆልን ይቀምሳል ስለዚህ ዛፉ የሚያስታውቀው ኑሮን ነው ከመታዘዝ በፊትና በኋላ ያሉ መልካምና ክፉ ኑሮዎች በዛፉ ላይ በሚፈፀሙ ድርጊቶች ይወሰናል።ለምርጫ የተዘጋጀ ዛፍ ነው።

10.“ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፤ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር።”

ወንዙ ከኤደን ፈልቆ ገነትን ኣጠጥቶ ሲወጣ ወደ አራት ወንዞች ይከፈላል

ልብ በል:- ወንዞቹ ለአራት ተከፍለው የሚኖራቸውን ፍሰት በመፅሓፉ የተፃፈውና ኣሁን ያለው ጂኦግራፊያዊ የግዛቶቹ ኣቀማመጥ የተለያየ ነው በምዕራፍ 1፥9 ላይ
“⁹ እግዚአብሔርም፦ ከሰማይ በታች ያለው ውኃ #በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ አለ፤ እንዲሁም ሆነ።¹⁰ እግዚአብሔርም የብሱን #ምድር ብሎ ጠራው የውኃ መከማቻውንም #ባሕር አለው፤”
ብሏል ስለዚህ የብሱ እንዳሁኑ ክፍለዓለማት ተብሎ በባሕር ያልተከፋፈለ አንድ የብስ ነበረ ባሕሩም በአንድ የተሰበሰበ ውሃ ነበር ማለት ነው።እንዲህ ከነበረ የምድሪቱ ገፅታ እንዴት ሊቀየር ቻለ ካልን በኖህ ዘመን የነበረው የጥፋት ውሃ የብሱ መጀመርያ ላይ አንድ ከነበረበት ገፅታ እየተሰነጣጠቀና እየተንሸራተተ በመሃሉም ባህር እየፈጠረ አሁን ላይ ያለውን በኣህጉር የተከፋፈለ መልክአ ምድር እንዲይዝ ኣድርጎታል።