Get Mystery Box with random crypto!

ፍላጎትህን አቃና! ቀላል ህይወት እንዲኖርህ ከፈለክ፣ ቀላል የህይወት መርህ ያስፈልግሃል። አንደኛ | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

ፍላጎትህን አቃና!

ቀላል ህይወት እንዲኖርህ ከፈለክ፣ ቀላል የህይወት መርህ ያስፈልግሃል። አንደኛውም መርህ ከሰዎች የምትጠብቀውን ነገር ይዳስሳል። ማንም መወደድን የሚጠላ፣ ተቀባይነትን የሚጠየፍ፣ መከበርን የሚገፋ ሰው የለም። ነገር ግን ፍላጎቱ ስህተት መሆን የሚጀምረው ያየው ሰው ሁሉ እንዲወደው፣ ስራውን የተመለከተው ሰው ሁሉ እንዲያደንቀው፣ የሰማው ሁሉ እንዲከተለው መፈለግ የጀመረ እለት ነው። ይህን መርህ ይዘህ ከህመም በቀር ምንም ልታተርፍ አትችልም። ምክንያቱም አንተ እራስህ የማትተገብረውን ነገር ከሰዎች እየጠበክ ነውና ነው። ማንም ብትሆን የእራስህ ስሜትና ፍላጎት አለህና ሁሉንም ሰው ልትወድ፣ ሁሉም ሰው የሚናገረውን ልታዳምጥ፣ የሁሉም ሰው አድናቂና ተከታይ ልትሆን አትችልም። የምትወደው ሰው እንደመኖሩ የማይመችህና ምርጫህ ያልሆነ ሰው አለ። ይህም በሰውነቱ ሳይሆን በተግባሩ ነው።  ስለዚህ ከፍላጎትህ ጋር የሚሄደውን፣ ለአላማህ የሚጠቅምህን፣ ንግግሩ ፍሬ ነገር የሚሰጥህን ሰው ትሰማለህ፣ ትወዳለህ፣ ትቀበላለህ ሌላውን ትተዋለህ።

አዎ! ጀግናዬ..! ፍላጎትህን አቃና! ምኞትህን ፈር አስይዝ፤ የህይወት መመሪያህን ከአቋምህ ጋር አስኪድ፤ ከተግባርህ ጋር አጣጥም። አንተ የማትፈፅመውን ተግባር ሌሎች እንዲፈፅሙልህ አትጠብቅ፤ እራስህ የማትሆንላቸውን ገፀባህሪ እነርሱ እንዲሆኑ አታስገድዳቸው። አንተ ስትፈልግ ቀላልና መደረግ ያለበት ግዴታ፣ ሌሎች ሲፈልጉ ደግሞ በፍላጎትህ ልክ በምርጫ የምታልፈው ነገር የለም። ከሌሎች የምትጠብቀውን ነገር ሌሎች ካንተ እንደሚጠብቁ ብታውቅ ምንያክል ልታደርግላቸው ዝግጁ እንደሆንክ እራስህን ጠይቅ። እራስህ ባስቀመጥከው ሚዛናዊ ያልሆነ መርህ አትሸነፍ፤ መልሶ አንተኑ በሚያጠቃህ አቋም እራስህ አትገድብ።

አዎ! ለደስታህ ሲባል መርሆችህ በሙሉ ደጋፊህና ከገሃዱ አለም እውነታ ጋር የሚሔዱ ሊሆኑ ይገባል። ሰዎች እንደማያደርጉልህ እያወክ ስለምን ደጋግመህ እነርሱን እየጠበክ እራስህን ትሰብራለህ? በፍላጎቶችህ ከደብ ማጣት ስለምን ለጭንቀትና ብሶት እራስህን ታጋልጣለህ? ከውጭ የምትፈልገው ነገር ቢኖር ቅድሚያ ውጥህ እንደሌለና ለእራስህ እንዳላደረክ እርግጠኛ ሁን። እግዚአብሔር ከሚሰጥህ፣ አምላክ ከሚያድልህ ነገር በቀር አንዱም ከሰዎች የሚመጣ ነገር አብሮህ አይቀርም። ውጫዊ መሻትህን ገድብ፤ ከእራስህ የምትጠብቀው ነገር ላይ አተኩር፤ መሬት ላይ ባለው ተጨባጭ እውነታ አንፃር ህይወትህን ቀለል አድርገህ ኑር።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q